የፍሬው ገረመው የቀብር ስነ-ስርአት ዛሬ ተፈፀመ

(መረጃውን የላከልን ክለቡ አርባምንጭ ከተማ ነው)

በድንገት ሕይወቱ ያለፈው የአርባምንጭ ከተማው ግብ ጠባቂ ፍሬው ገረመው የቀብር ስነ-ስርዓት ዛሬ በትውልድ ከተማው አርባምንጭ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል፡፡

ፍሬው ገረመው ከአባቱ ገረመው መገርሳና ከእናቱ ከወ/ሮ አከላት አማረ በ1985 ዓ.ም በአርባምንጭ ከተማ ድልፋና ቀበሌ ተወለደ። እድሜው ለትምህርት ሲደርስ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በቀድሞው ሳርማሌ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ከ1ኛ እስከ 3ኛ ክፍል ተምሮ ከ4ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ በኩልፎ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማረ እንደሆነና ከ9ኛ እስከ 10ኛ ክፍል ድረስ ያለውን ትምህርት ደግሞ በአርባምንጭ መሰናዶ ትምህርት ቤት በመከታተል አጠናቋል፡፡ በአዲሱ የትምህርት ፖሊሲ መሰረት የ10ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ብሄራዊ ፈተና በመቀበል በአርባምንጭ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በማሽን ኦፐሬተርነት በዲፕሎማ ተመርቋል፡፡

ወጣቱ ግብ ጠባቂ ፍሬው ገረመው በሀገራችን በእግር ኳሱ ዘርፍ የነበረውን የግብ ጠባቂ ችግር ለመቅረፍ በማለም በአርባምንጭ ከተማ ተስፋ ቡድን በ2006 ለመጫወት ተቀላቅሏል ፡፡ ከአርባምንጭ ተስፋ ቡድን በመቀጠል ወደ ጊዶሌ ከተማ ክለብ በ2007 አምርቶ የተጫወተ ሲሆን 2008 ደግሞ በጂንካ ከተማ አሳልፏል፡፡ 2009 ጂንካን ከለቀቀ በኃላ ወደ ደቡብ ፖሊስ ተጉዞ የተጫወተ ሲሆን ከዛ በመቀጠል ደግሞ በሀድያ ሆሳዕና የግማሽ ዓመት ቆይታን አድርጓል፡፡ የተጠናቀቀውን የውድድር ዓመት በደቡብ ፓሊስ በፕሪምየር ሊጉም ጭምር ሲጫወት ከቆየ በኃላ ህይወቱ እስካለፈችበት ጊዜ ድረስ ደግሞ ለትውልድ ሀገሩ አርባምንጭ በመጫወት ላይ ይገኝ ነበረ፡፡

ከሰሞኑ በእግሩ ላይ ዕጢ ወጥቶበት ለማስወጣት ወላይታ ሶዶ በሚገኘው ክርስቲያን ሆስፒታል ህክምና ላይ እያለ ረቡዕ ማለዳ በተወለደ በ27 ዓመቱ ህይወቱ በድንገት ማለፉ ይታወሳል፡፡

የተጫዋቹ አስክሬን ወደ አዲስ አበባ ተልኮ ምርመራ ከተደረገለት በኃላ ትላንት አመሻሽ አርባምንጭ ከተማ የገባ ሲሆን ዛሬ ረፋድ 4:00 ቤተሰቦቹ፣ ጓደኞቹ፣ የክለብ አጋሮቹ፣ አሰልጣኞች፣ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች የስፖርት ወዳጆች የሀይማኖት መሪዎች እና ሌሎች በርካታ አካላት በተገኙበት በአርባምንጭ ደብረ መንክራት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ሰርአተ ቀብሩ ተከናውኗል፡፡

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ