አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ከተለያዩ ድረ-ገጾች ያገኛቸውን የእግርኳስ ታክቲክ ንድፈ-ሐሳቦችን የተመለከቱ ጥልቅ ትንተናዎች፣ የሥልጠና መመሪያዎች እና መጻህፍትን ከእንግሊዘኛ ወደ አማርኛ በመተርጎም ሌሎች አሰልጣኞችና አንባቢን ይጠቅም ዘንድ ጥቅም ላይ ለማዋል ይሞክራል፡፡ ከዚህ በታች የቀረበው ፅሁፍም አንዱ አካል ነው፡፡
እግር ኳስ በቅርብ ዓመታት በከፍተኛ እድገት ውስጥ እያለፈ ነው፡፡ይህም በአብዛኛው አየተከሰተ ያለው ከጨዋታው ኡደት የተነሳ ነው ፡፡የጫወታ ዘይቤ ከፍ ባለው የአውሮፓ እግር ኳስ እየተለዋወጠ ቢሆንም ዝንባሌው ግን በግልፅ ይታያል፡፡የማጥቃት ጨዋታ ጠንካራ መሆን አሰልጣኞች አዳዲስ የመከላከል ፈጠራዎችን እንዲፈልጉ በማድረግ መከላከል ከፍ እንዲል አድርጎታል፡፡ በተቃራኒው መከላከል ሲያድግም አሰልጣኞች አዳዲስ የማጥቃት መንገዶችን በዚያው ልክ ይፈጥራሉ፡፡
መከላከል በማጥቃት ይጀምራል
እግር ኳስ በ 4 ደረጃዎች ሊከፈል ይችላል
- ማጥቃት
- ከማጥቃት ወደ መከላከል ሽግግር
- መከላከል
- ከመከላከል ወደ ማጥቃት ሽግግር
እነዚህ የጨዋታ ሂደቶች በፍፁም ተነጣጥለው ሊታዩ አይገባም ፡፡እያንዳንዱ ጥቃቅን ጉድለት ሌላኛውን ነገር ይጎዳል፡ የአንድ ቡድንየማጥቃት ዘይቤ ቡድኑ እንዴት እንደሚከላከልና ውጤታማ ይሁን ወይም አይሁን ይገልፀዋል፡፡ነገር ግን ይህንን በሌላ እይታም ማየት እንችላልን ፡- ወደ መከላከል ትክክለኛ ሽግግር ማድረግ በሚያስችለው መንገድ ለማጥቃት ቡድኑ እንዴት መከላከል እንዳለበት ማስታወስ አለበት፡፡
መከላከልን ለማቅለል ቡድኑ መጠቅጠቅ አለበት ፡፡ይህ ማለት በማጥቃት ጊዜ ተጫዋቾች በአግድሞሽ እና በቁመት አንዱ ከአንዱ ብዙ ክፍተት እንዳይተው መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል፡፡ተጠጋግተው መቆየት ከቻሉ ተቃራኒ ቡድን ኳስን ከነጠቀ በኋላ በመልሶ ማጥቃት እንዲያጠቁ እድል አይሰጡትም፡፡ቡድኑ ትኩርት የሚያደርገው በትንሽ ቦታ ላይ ነው፡ ይህም ኳስ መቆጣጠርን ቀላል ያደርገዋል ፡፡(እንደምናውቀው ደግሞ ተቃራኒ ቡድን ኳስን ካላገኘ እውነተኛ አደጋ መፍጠር አይችልም ) ኳስን መልሶ ለማግኘትም ቀላል ነው ፡፡ወደ መከላከል ቅርፅ ለመቀየርም ቀላል ነው፡፡
መልሶ-ፕረሲንግ (counter pressing)
- ይህ ማለት መልሶ ማጥቃትን ጫና ማድረግ ማለት ነው፡፡
- እንዲህ ተብሎ ሊገለፅ ይችላል፡፡ቡድን ኳስን እንዳጣ ተቃራኒ ቡድን ቶሎ ሽግግር እንዳያደርግና የሚከላከለው ቡድን እራሱን ለማደራጀት ጊዜ እንዲያገኝ ቡድኑ ላይ ጫና ማድረግ ፡፡እንደውም በተሻለ መንገድ የሚያጠቃው ቡድን መሀል ሜዳ ሳይደርስ መንጠቅ ያስችላል፡፡
- ከላይ እንደተገለፀው ለመልሶ መከላከል በማጥቃት ላይ እያለን በትክክለኛ አቋቋም በመቆም መዘጋጀት ይኖርብናል፡፡ተጠጋግቶ መቆም ብቻውን ምርጥ ነገር አይደለም ፡፡በጣም አጥብቦ መቆም ትልቅ ክፍተት ከተከላካዮች ጀርባ ይተዋል ፡፡ይህም በቀላሉ በተቃራኒ ቡድን በረጅም ኳስ መጠቀሚያ ሊሆን ይችላል፡፡
- የመልሶ ፕረሲንግ ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥረው ሌላው ነገር መደራጀት ነው፡፡ በቦታ ብቻ ሳይሆን በሚናም ጭምር ኳስ ላይ በድንገት የሚደረገው ጫና ከባድ እንቅስቃሴ እንደመፈለጉ ተጫዋቾች በብዙ ጫና ውስጥ ይሰራሉ ፡፡ይህ ከባድ ጫና የአካል ብቃት ችግር ስለሚፈጥር ተጫዋቾች በመጀመሪው ግማሽ እንዲደክሙና ሁለተኛው ግምሽን በብቃት መጫወት እንዳይችሉ ያደርጋል፡፡
- ለዚህ ነው አሰልጣኞች የት? እና በምን አይነት ጫና? እና ለምን ያህል ጊዜ? መልሶ መከላከልን መጠቀም እንዳለበት ዝርዝር እቅድ ያስፈልገዋል፡፡ለምን ያህል ደቂቃ የሚለውን ጋርዲዮላ ለምሳሌ የ “5” ሰከንድ ህግ አለው፡፡ይህም በብዙ የአውሮፓ ቡድኖች ጥቅም ላይ ይውላል ፡፡ይህም ኳስ በቀጠለ ቁጥር ተጫዋቾች ቦታቸውን እንዳይለቁ እና ቅርፃቸውን እንዲጠብቁ ያደርጋል፡፡
- ስለ ፕረሲንግ ስናወራ ግን እንደሌሎቹ የመከላከል ዘዴዎች ይህም ተቃራኒ ቡድንን ወደ ማይመች ቦታ ይህም ውጤታማ ማጥቃት እንዳያደርጉ ወደሚያደርግ ቦታ ይገፋቸዋል፡፡ይህንንም ለማድረግ ምርጡ መንገድ መሀል ሜዳውን እና የመከላከል ሲሶውን የመሃል ክፍል (half space) መያዝ ነው ፡፡ይህንን ማድረግ ከተቻለ ተቃራኒ ቡድን በመሀል ሜዳ መጫወት አይችልም ይህም ተቃራኒ ቡድን ወይ ወደ ጎን ወይም ወደ ኋላ እንዲጫወት ያስገድደዋል፡፡
- ይህም ወደ ፊት የሚደረግን የኳስ ማቀበያ መስመሮችን በመዝጋት ኳስ የያዘው ተጫዋች ላይ ከተለያየ ማዕዘን ጫና በማሳረፍ ሊደረግ ይችላል፡፡
የተለያዩ ዓይነቶች የመልሶ ፕረሲንግ አቀራረቦች አሉ፡፡
- ሰው በሰው
- ቀላሉ ግን ደግሞ ደካማው መልሶ መከላከል ነው
- አንዱ ተጫዋች ብቻ ኳስ የያዘው ተጫዋች ላይ ጫና ሲያደርግ ሌሎች አጠገባቸው ያሉትን ተጫዋቾች ይይዛሉ ፡፡
- የዚህ ፕረሲንግ ዓይነት ዋናው ችግር ሌሎች ተጫዋቾች ሰው ለመያዝ ሲሸሹ ኳስ ላይ ጫና የሚያደርገው ቦታ ላይ 1 ለ 1 ግንኙነት ይፈጠራል ይህም ኳስ የያዘው በቴክኒክ ጥሩ ተጫዋች ከሆነ አስቸጋሪ ሁኔታ ይፈጥርባቸዋል፡፡
የቀዩ ቡድንተጫዋቾች ኳሱ ባለበት አካባቢ ሰው በሰው መያዝን ይጠቀማሉ፡፡
- ቀጠና ላይ ያተኮረ
- ይህ የተሻለ የፕረሲንግ ዓይነት ነው
- ይህ በዓለም አቀፍ ገገን ፕረሲንግ ተብሎ የሚታወቀው የመከላከል መንገድ ነው ፡፡
- የርገን ክሎፕ በዶርትሙንድ ጥቅም ላይ አውለውት በዚህ መከላከል ዘዴ በመታገዝ ለቻምፒየኝስ ሊግ ፍፃሜ ደርሰዋል፡፡
- መሰረት ያደረገው በጋለ ስሜትና በፈጣን ጫና ኳስ የያዘውን የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋች ላይ ጫና ማድረግ ነው ፡፡
- አንዳንድ ጊዜ ሙሉ ቡድኑ ኳስ የያዘውን ተጫዋች ሲያሳድድ እናያለን
- ከጀርባ ያሉትን ተጫዋቾች በጥላቸው ይሸፍናሉ፡፡
- ኳስ ማቀበያ መስመር ላይ ያተኮረ
- በተለይ ጋርዲዮላ ከተጠቀመበት በኋላ ታዋቂ የሆነው የፕረሲንግ ዘዴ ነው፡፡
- በዚህ ዘዴ ኳስ የያዘው ተጫዋች ላይ ጫና አይደረግም ፡፡ኳስ የያዘውም ለጓደኛው ማቀበል የሚችል ይመስለዋል ፡፡ነገር ግን የሚነጥቀው ቡድን የኳስ መስመሮችን ይዘጋል፡፡
- ይህን ማድረግ ካልቻሉ ወደ ሰው በሰው መከላከል ዘዴ ይቀይራሉ፡፡
መልሶ-ተጭኖ መጫወት ለምን ይጠቅማል ? የሚል ጥያቄ ልትጠይቁ ትችላላችሁ፡፡
- ቡድኑ እያጠቃ ኳስ ከተነጠቀ አደጋ ውስጥ ይገባል
- የተከላካዩክፍል አልተደራጀም
- ቶሎ ወደ መከላከል ለመሸጋገር እድል የለም
- እነዚህን ችግሮች የሚቀርፈው መልሶ ፕረስ ማድረግ ነው ፡፡
- መልሶ ማጥቃቱ ላይ ጫና በማድረግ ለቡድን አጋሮች እንዲደራጁ ጊዜ መስጠት
- በዚህም ተቃራኒ ቡድን ግማሽ ሜዳ ሳይደርስ ኳስን የመንጠቅ እድል ይፈጥራል፡፡
በተጨማሪም
መልሶ ፕረስ ማድረግ ማጥቃትንም ያሻሽላል፡፡
- ተቃራኒ ቡድን ለማጥቃት ሲሞክር ተከላካዩ ያልተደራጀ ይሆናል ፡፡ይህም ጫና በሚያደርገው ቡድን ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል ፡፡እናም ኳሱ በተቃራኒ ቡድን የሜዳ ግማሽ እያለ ወዲያው ጎሉን ማጥቃት ያስችላል፡፡ይህም ማጥቃትን ለማስጀመር ኳስን ለመመስረት ጊዜ እንዳይኖር ያደርጋል፡፡
ፕረሲንግ
- ስለ ፕረሲንግ ስናወራ መጠቅጠቅ/ጥግግት (comapactness) ዋነኛው ነገር እንደሆነ መርሳት የለብንም ፡፡
- ተጫዋቾች ተቃራኒ ቡድን በመስመሮች መካከል ሰፊ ቦታ እንዳያገኝ በሜዳው ቁመትና ስፋት በጠበበ አደራደር መቆም አለባቸው፡፡
- ምክንያቱም በተጫዋቾች መካከል በሚኖር ጥሩ ግንኙነት ተቃራኒ ቡድንን ወደዳር መግፋት ይችላል፡፡
- ተቃራኒ ቡድን በመስመር ብቻ መጫወቱ አንድ ቡድን በጥሩ ሁኔታ ፕረስ እያደረገ ነው ማለት አይደለም፡፡በዚህ ቦታ ላይ ተጫዋቾች 180ዲግሪ ማቀበያ ዕድል ብቻ ስላላቸው ፕረስ የሚያደርገው ቡድን ፕረስ ለማድረግ የተሻለ ዕድል ስለሚኖረው መሀል ሜዳ ላይ ከሚያደርጉት በላይ በዚህ ቦታ ላይ ማድረግ አለባቸው፡፡
የተለመዱ የፕረሲንግ አይነቶች የትኞቹ ናቸው. ?
ፕረሲንግን ለመተንተን ቡድኖች ከሚጠቀሙት አጥቂዎች ቁጥር መነሳት የተለመደ ነው፡፡በአብዛኛው የምንጠቀመው ፕረሲንግ አይነት የአጠቂዎቹን ብዛት ይወስናል ፡፡ስለ ፕረሲንግ ስናወራ ፈጣን ፕረሲንግ(active pressing) እና ፍዝ ፕሬሲንግ(passive pressing) ብለን ቡድኑ ኳስን ማጥቃት ከሚጀምርበት ቦታ በመነሳት መለየት እንችላልን፡፡
ትንተናውን በአንድ አጥቂ ፕረሲንግ በመጀመር እሱንም በሁለት እንከፍለዋልን፡፡
- 4-1-4-1 በአብዛኛው እየተዘወተረ ያለ ነው ፤ምክንያቱ ደግሞ ምናልባት ከ4-4-2 ይልቅ አደጋው ዝቅተኛ ስለሆነ ነው ፡፡
- ቡድኑ የጨዋታ ምስረታውን ፕረስ ማድረግ ከፈለገ ከፍተኛ የመከላከል መስመርን መጠቀም አለበት
- በዚህ ቅርፅ ግን የተከላካይ አማካዩ ተከላካዮች በጥልቀት እንዲቆዩ እድል ይፈጥራል፡፡ ምክንያቱም የእሱ ቦታ መያዝ በመስመሮች መካካል ያለውን ቦታ ይሸፍናል፡፡የተከላካይ አማካዩ በመስመሮች መካካል ይቆያል፡፡
-በጨዋታ አሰላለፍ በተለያዩ መንገዶች ፕረስ ማድረግ ይቻላል፡፡ቀድመን መነቃቃት የሌለውንወይም ፍዝ የሆነውን ፕረሲንግ (passive pressing) እንመልከት ፡፡በዚህ ጫና አደራረግ ጫናው ኳስ በያዘው ላይ ሳይሆን በጥሩ አቋቋም በመሆን ወደ ፊት የሚደረጉ ኳስ መቀባበሎችን መዝጋት ነው፡፡ለዚህ ደግሞ የሽፋን ጥላን መጠቀም በጣም አስፈላጊ ይሆናል፡፡
“ተጫዋቾችንእግር በእግር አትከታተል፤ ይልቁንም በሁለት ተጫዋቾች መሀል ያለውን ክፍት ቦታ ሸፍን፡፡” ፔፕ ጓርዲዮላ
- ይህ ማለት አጥቂው ሰው- በ-ሰው የተከላካይ አማካዩን ከያዘ ተከላካዩ ከኳሱ ጋር በመጠጋት ከጥልቀት ሊያደራጅ ይችላል ፡፡ በጥላው መሸፈንን ሳይጠቀም ወደ ተከላካዩ ከሮጠ ደግሞ ለተከላካይ አማካዩ ሰፊ ቦታ በማግኘት ኳስን በነፃነት ይቀበላል፡፡
በትክክለኛ አቋቋም በመሆን ወደፊት የሚደረግ የኳስ ቅብብልን በቀላሉ ማስቆም ይችላል፡፡
- በዚህ ዓመት (2016) በፕረሲንግ ሲጫወት ይህንን አሰላለፍ የተጠቀመው የኡናይ ኢምሬ ፒኤስ ጂ ነው ፡፡የፈረንሳዩ ክለብ 4-1-4-1 ተቃራኒ ቡድንን በአግድሞሽ በመዝጋት በከፍተኛ ደረጃ ፕረስ ያደርግ ነበር ፡፡ከላይ በተብራራው መንገድ የተከላካይ አማካዩ ኳስን እንዳያገኝ በመሸፈን በዚያው ሰዓት የመስመር ተከላካዮች በመስመር ወደፊት እንዲሄዱ ያደርጋሉ፡፡የመስመር አጥቂዎቹ የተቃራኒ ቡድንን የመስመር ተከላካዮች ኳስን እንዳገኙ ጫና በማድረግና ወደ መሀል እንዳያቀብሉ የሚወጡት ሚና አስፈላጊ ነው፡፡
አሁን በ4-1-4-1 ፈጣን ፕረሲንግን (active pressing) ማየት እንችላለን፡፡
ይህ አቀራረብ ሁለት ዓይነት አለው
የመጀመሪያው አሰላለፍ እንዳለ ሲሆን እና ሁለተኛው ወደ 4-4-2 ሲቀየር
- በመጀመሪያው በሁለት መንገድ ፕረሲንግን መጠቀም እንችላለን፡፡ አንደኛው በመሀል ተጫዋች ፕረስ ማድረግ ሲሆን ሁለተኛው በመስመር ተጫዋች ፕረስ ማድረግ ነው፡፡
- የመጀመሪያውን መጠቀም ቀላል ነው ምክንያቱም የመሀል ተጫዋቹ የሚተወውን ክፍተትበቀላሉ በተከላካይ አማካዩ መሸፈን ይቻላል፡፡
- በመስመር አጥቂ ፕረስ ማድረግ በጣም አስቸጋሪ ነው ፡፡ ምክንያቱም ቡድኑ እንዳለ ውስብስብ እንቅስቃሴማድረግ ይኖርበታል፡፡በሜዳው የተወሰነ ቦታ ላይ ያለ ቁጥጥርን ማጣትና ነገሮችን ማደበላላቅ ካልፈለጉ በመስመር ያለውን ክፍተት መሙላት አለባቸው፡፡ጠንካራው ጎኑ አንዱ የመሀል ክፍልተጫዋች ወደ መስመር መጠጋት ይኖርበታል፡፡ በዚህ ጊዜ የተከላካይ አማካዩ የዚህን ተጫዋች ቦታ ለመተካት ይጠጋል፡፡በአጠቃላይ የመሀል ክፍሉ በተመሳሳይ አቅጣጫ ይጠጋል፡፡
ይህንንዘዴ አትሌቲኮ ማድሪድ በ2015 ተጠቅሞበታል፡፡
ፈጣን ፕረሲንግ (active pressing) በ 4-1-4-1 ይህንን ይመስላል
- አጥቂው የመሀል ተከላካዩን በሀይል ያጠቃል፡ዞሮ በመሮጥ አጠገቡ ላለው የመሀል ተከላካይ እንዳይሰጥ ያደርገዋል ፡፡በዚህ ጊዜ የተከላካይ አማካዩ በመሀል ተጫዋቾች መያዝ ይኖርበታል፡፡ይህ አንዳንድ ጊዜ በጋርዲዮላ ማንችስተር ሲቲ ይተገበራል፡፡አጥቂው ተከላካዩን ወደ መስመር እንዲያቀብል ያስገድደዋል፡፡ከዚያም ፈጣን ጫና ኳስ የያዘው የመስመር ተከላካይ ላይ በማድረግ ቀጠናውን መሸፈን ፡፡
ሌላው የፕረሲንግ ወጥመድ ማዘጋጀት ነው ፡፡ይህ ወጥመድ በሚከላከለው ቡድን ስህተት የሠራ በማስመሰል ለተቃራኒ ቡድን ኳስ የማቀበያ መስመር ይከፍታሉ፡፡ግን ኳስ ልክ ሲሰጥ ኳስ ተቀባዩ ላይ ከፍተኛ ጫና ይደረጋል፡፡ቡድኑ በሌላኛው ግማሽ ኳስን መንጠቅ ከፈለገ በአብዛኛው የፕረሲንግ ወጥመድ ያዘጋጃል፡፡ምክንያቱም በተለመደው ፕረሲንግ ቡድኑ ረጅም ኳስ እንዲያደርግ ያስገድዳሉ፡፡በዚህ ግን በሜዳው ክፍል ኳስን እንዲነጥቁ ያስችላል፡፡
በሁለት አጥቂዎች ፕረስ ማድረግ
4-4-2 እና 4-2-2-2
- በዚህ አሰላላፍ ፍዝ ፕረሲንግ (passive pressing) ይህንን ይመስላል፡፡የሁለቱ አጥቂዎች ዋና ስራቸው ከተቃራኒ ቡድን የተከላካይ አማካይ አጠገብ መገኘት ነው፡፡ይህም ወደ መሀል ክፍሉ የኳስ ማቀበል እንዳይኖር ያደርጋል፡፡በዚህ ጊዜ የመሀል መስመሩ በአግድሞሽ መጠቅጠቅ ይኖርበታል ወደ መስመር ወደ መስመር ለሚደረግ ኳስ ማቀበል ቶሎ ምላሽ መስጠት አለባቸው ፡፡
- 4-2-2-2 ትም በመሀል ክፍሉ ላይ ያተኩራል ፡፡ከፊት ያሉት ስድስት ተጫዋቾች በ ጎነ-ስድስት ምስል (hexagon) በሚወከሉ ጫፎች ላይ ይቆማሉ፡፡በዚህ አቋቋም ሌላ አሰላለፍ ሊሰጥ የማይችለውን መሀል ሜዳው ላይ ሰፊ ቦታ መሸፈን ያስችላል፡፡
በስዕሉ እንደምትመለከቱት በዚህ አሰላለፍ መሀል ሜዳው ላይ ጥቅጥቅ ስለሚል ተቃራኒ ቡድንን ወደ ክንፍ ይገፋሉ፡፡ በዚህ ቦታም ኳስን መንጠቅ ቀላል ይሆናል፡፡
በ 4-4-2 ኃይል ላይ ያመዘነ ፕረሲንግ (aggressive pressing)
በዲያጎ ሲሞኒ ጥቅም ላይ የዋለ ፕረሲንግ ነው ፡፡
- ይህ ባሕላዊውን ሰው በሰው የመያዝ መከላካል በመተው ትኩረታቸውን በጥላ መሸፈን ላይ ያደርጋል፡፡ይህ ማለት ኳሱን የያዘው ተጫዋች ምንም የማቀበያ እድል እንዳያገኝ የማቀበያ መስመሮችን በመዝጋት ረጅም ኳስ እንዲመታ ማስገደድ፡፡
- ይህ ተግባር ላይ የሚውለው ኳስ ባለበት አካባቢ ያሉ ክፍት ቦታዎችን በመቀነስ ወደክፍት ቦታዎቹ ኳስ የማቀበል እድል እንዳይኖር በማድረግ ነው፡፡ይህ የፕረሲንግ አይነት በአብዛኛው ውጤታማ የሚሆነው ሁለት የመሀል ተከላካይ እና አንድ ተከላካይ አማካይ በሚጠቀም ቡድን ላይ ነው፡፡ለምሳሌ ባርሴሎና
- በዚህ ፕረሲንግ ሁለቱ አጥቂዎች እንቅስቃሴያቸውንከጥልቀት ይጀምራሉ፡፡አንደኛው ከተከላካይ አማካዩ ጎን ይቆማል ሌላኛው ኳስ የያዘውን ለማጥቃት ዞሮ ይጠጋል፡፡
- በዚህ ጊዜ የመህል ተጫዋቾች ክፍት ቦታዎችን ይሸፍናሉ፡፡ኳስ ወደ ጎን ሲሰጥ ብቻ ወደመስመር ይወጣል ፡፡ሲንቀሳቀሱ እንደቡድን ይንቀሳቀሳሉ፡፡ በዚህም ከተቃራኒ ቡድን ፊት ያለውን ከፍት ቦታ ይቀንሳሉ፡፡
- በዚህ አቀራረብም የፕረሲንግ ወጥመድን መጠቀም ይቻላል፡፡ይህንን በመስመር መጠቀም ይቻላል፡፡ሁለት አቀራረብ አለው፡፡ የጎን መስመር ላይ የማቀበያ ክፍተት በመተው ወይም ኳስ የያዘው ተጫዋች ወደ መሀል እንዲያቀብል በመፍቀድ ነው፡፡
3-5-2
- ይህኛው ለፕረሲንግ ሁለት አጥቂዎች የሚጠቀም የጫወታ ዘዴ ነው
- ይህ ዘዴ ልክ እንደ 4-2-2-2 ዋነኛው ትኩረቱ መሀል ክፍሉ ላይ ይሆናል፡፡
- ፎርሜሽኑ በመሀል ክፍሉ ላይ 5 ተጫዋቾች ስለሚኖሩት መሀል ላይ የበላይነት ለመውሰድ በማስቻል የተቃራኒ ቡድንተጫዋቾችን ወደ መስመር ይገፋል፡፡
- በፍዝ ፕረሲንግ በግልፅ እንደሚታየው በፊተኛው መስመር ያሉት 5 ተጫዋቾች በመሀል ያለውን ቦታ ሲሸፍኑ የመስመር ተመላላሾቹ የተጋጣሚ መስመር አጥቂዎችን ይይዛሉ፡፡
- በ3-5-2 የመስመር ተከላካዮችን በመጠቀም በፈጣን ፕረሲንግ መጫወትም ይቻላል፡፡በእነርሱ ምክንያት ሙሉ የተከላካይ መስመሩ ቦታ መቀየሩ አላስፈላጊ ስለሆነ ይህንን ስራ ራሳቸው እየተወጡ የተቃራኒ ቡድን መስመር አጥቂዎችን ይይዛሉ፡፡
በሦስት አጥቂ ፕረስ ማድረግ
- አሁን አሁን ይህ ብዙም ጥቅም ላይ የማይውል የፕርሲንግ አይነት ነው ፡፡ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ለሁለት መሀል ተከላካዮች 3 ተጫዋቾችን በመጠቀም ፕረስ ማድረግ አላስፈላጊ ስለሆነ ነው፡፡
- አሁን አሁን ከኋላ በ3 ተጫዋየመከላከል ዘዴን በአውሮፓ እግር ኳስ የተለመደ ስላልሆነ ይህንን አቀራረብ ብዙም አንመለከተውም ፡፡
- አጠቃቀሙ ከላይ እንደቀረቡት የፕሬሲንግ ዘዴዎች በተመሳሳይ የሽፋን ጥላን በመተግበር ነው ፡፡
- ስለዚህ በሦስት አጥቂ ፕረስ ማድረግ በሁለት አጥቂዎች ከመጠቀም ሰፋ ያለ ነው፡፡
በራስ ሜዳ መከላከል
- የማንኛውም ቡድን የመጨረሻ ግብ በሚገነባው ቡድን የተረጋጋ የጨዋታ መሰረት መፍጠር ነው ፡፡
- ይህ መሰረት የተለያየ ሊሆን ይችላል ፡፡በአብዘኛው ግን ጥሩ መከላከልዋናው ነው ፡፡
“ኳስ ስንነጠቅ እንደ ትንሽ ቡድን እንሆናለን፡፡በጣም የምወደውም ይህንን ነው” ፔፕ ጓርዲዮላ
- የጋርዲዮላ ሃሳብ በእግር ኳስ መከላከልን የሚገልፅ እውነታ ነው ፡፡በከፍተኛ ሁኔታ የሚያጠቃ ቡድን ሊኖረን ይችላል፡፡ የተቃራኒ ቡድን ማጥቃትን ለመከላከል እንደትንሽ ቡድን መጫወት ይኖርብናል ፡፡
- ስለዚህ በደንብ ለመከላከል ምን ማድረግ ይኖርብናል?
የመጀመሪያው ህግ፡-ሰው በሰው አትያዝ፡፡
አንዳንድ ቡድኖች አሁንም ሰው በሰው መያዝን ለውጤታማነታቸው ፣ሁሉንም ችግር እንደሚፈታላቸው አድርገው ያዩታል፡፡
- ይህ አቀራረብ በትልቅ ደረጃ ላሉ ቡድኖች መፍትሄ አይደለም
- ይህ ዘዴ በግል ችሎታና በጥሩ የቡድን ስራ መጠቀሚያ ሊሆን ይችላል
- በዚህ ዘመን ያለ እግር ኳስ ቦታን ስለመቆጣጠር ነው ፡፡ስለዚህም ሰውን ይዘህ በሄደበት ሁሉ ከተከተልከው የሚፈልጉትን ትሰጣቸዋለህ ፡
ስለዚህ ምርጡ መከላከል የቀጠና መከላከል ነው፡፡
የቀጠና መከላከል በሦስት ይከፈላል
- ቦታ ተኮር(space oriented)
- ተጫዋች ተኮር (man oriented)
- ኳስ ተኮር (ball oriented)
- ቡድኖች በአብዛኛው እነዚህን አቀናጅተው ይጠቀማሉ
- በመጀመሪያው አቀራረብ ተጫዋቾች በጋራ በመንቀሳቀስ የቡድናቸውን ቅርፅ በተመሳሰይ መንገድ ይጠብቃሉ፡፡
- በሁለተኛው አቀራረብ የተቃራኒ ቡድን ቦታ አያያዝ የተጫዋቾችን እንቅስቃሴ ይወስናል ይህ ማለት አጥቂው ወደ አንተ ከቀረበ በቀጠናህ ጠጋ ትለዋለህ ግን አትይዘውም፡፡
- በዚህ አሰላለፍ መደበኛነቱ ይቀንሳል፡፡ ኳስ ተቆጣጥሮ ለሚጫወት ቡድን እንዲንቀሳቀስ ማድረግ፡፡
ሦስተኛው አማራጭ ኳሱ ያለበት ቦታ ላይ ያተኩራል ፡፡ኳሱ ባለበት ቀጠና ላይ በቁጥር ብልጫ ለመውሰድ ይሞክራል፡፡ ነገር ግንይህን ተጫዋቾች በጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው፡፡ ይህን በከፍተኛ ሁኔታ ከተገበሩ ሰፊ ክፍተት ይተዋሉ፡፡
- እንደ ሁሉም የጨዋታ ደረጃ መጠጋጋት (መጠቅጠቅ) በጣም አስፈላጊ ነው ፡፡ ጥቅጥቅ ብሎ ከሚቀርብ ቡድን ጋር ስንጫወትበመስመሮች መካከል ለመቀባበል በጣም አስቸጋሪ ይሆንብናል ፡፡ስለዚህ በመስመር መጫወት አስፈላጊ ነው ፡፡ይህም ሙሉ ቡድኑ ከተከላካይ እስከ አጥቂው ከፍተኛ ቅንጅት እንዲኖረው ያስፈልጋል፡፡የአጥቂዎቹ ስራ ኳሶችን ወደ መስመር እንዲያቀብሉ ማድረግና ተቃራኒ ቡድን እዚያ እንዲቆይ ማድረግ ነው ፡፡በተጨማሪም ለተከላካይ አማካዩ ኳስ እንዳይሰጥ ማድረግአስፈላጊ ይሆናል ፡፡በዚህ ጊዜ የመሀል ተጫዋቾችና ተከላካዮች ከሳጥኑ ፊት ያለውን ቦታ ይይዙታል፡፡በአብዘኛው ቀጠና 14 የሚባለውን ማለት ነው፡፡
የጽሁፉ ተርጓሚ አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ነው፡፡ አሰልጣኙ ባለፉት አስር ዓመታት በበጎ ፍቃድ ታዳጊዎችን በማሰልጠንና ለበርካታ ክለቦች በማበርከት እውቅና ባተረፈው የአስኮ እግር ኳስ ፕሮጀክት ሲያሰለጥን ቆይቷል ፡፡ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአፍሮ-ፂዮን እግር ኳስ ክለብ ከ17 ዓመት በታች ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡