መብራህቶም ፍስሀ እና ያልተጠበቀው ሽግግር

ባለፈው ዓመት በዚህ ወቅት ላይ ሳይጠበቅ ስድስት ዓመታት የተጫወተበት ክለብ ባቀረበለት ጥያቄ መሰረት ጫማውን ሰቅሎ ወደ አሰልጣኝነት ሥራ ገብቶ ቡድኑን በረዳት አሰልጣኝነት እያገለገለ ይገኛል። በሜዳ ውስጥ በሚያሳያቸው ስሜታዊ ባህርያት እና ተጫዋቾች የሚመራበት መንገድ የብዙዎች ትኩረት ስቦ የነበረው እና በቅፅል ስሙ ‘ጉንዲ’ በመባል የሚታወቀው  መብራህቶም ፍስሀ ስላልተገመተው ሽግግሩ እና ስለገጠሙት ፈተናዎች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።

ከተጫዋችነት ወደ አሰልጣኝነት የተሸጋገረበት አጋጣሚ

ክለቡን ላለፉት ስድስት ዓመታት በአምበልነት መርቻለሁ። በተጫዋችነት በቆየሁባቸው የመጨረሻ ጊዜያት ጉዳት አስቸግሮኝ ነበር። ከዛ በኃላ በክለቡ በቀረበልኝ ጥያቄ ነው በአጭር ግዜ ወደ አሰልጣኝነት የተሸጋገርኩት። በስፖርት ሳይንስ በእግር ኳስ ዲግሪ አለኝ። ከእግር ኳሱ ላለመራቅ እና ክለቡን ለማዳን ነው ጥያቄውን የተቀበልኩት። ከዛ በኃላም የአሰልጣኝነት ስልጠናዎች ወስጄ ክለቡን በረዳት አሰልጣኝነት እያገለገልኩ ነው።

ጥያቄውን ለመቀበል አልተቸገርክም ?

ትምህርቱ አለህ ለክለቡም ቅርብ ስለሆንክ ለዚ ቦታ እንፈልግሀለን ሲሉኝ ሳላመነታ ነው ጥያቄውን የተቀበልኩት።

በዛ ሰዓት ጫማህን ለመስቀል አስበህ ነበር?

ቀሪ የመጫወቻ ግዜ ነበረኝ ፤ በቂ ህክምና ባገኝ የመጫወት ሙሉ አቅም ነበረኝ። ሌሎች አቅም ያላቸው ቡድኖች ላይ ብሆን ታክሜ በደምብ የምጫወትበት ዕድል ነበር። ግን ያ አልሆነም፤ ብታከም ግን ጫማዬን ለመስቀል አልወስንም ነበር። እየተጫወትኩ ክለቤን አገለግል ነበር።

በወቅቱ ስለነበሩ ፈተናዎች?

አንዱ ፈተና በመጀመርያው ዙር በተጫዋችነት የነበረው ደሞዜ ከግማሽ በላይ የሚሆን ቀንሼ ነው የአሰልጣኞች ቡድን የተቀላቀልኩት። በዛን ሰዓት ውል ቢኖረኝም የምወደው ክለብ በመሆኑ ለጥቅም ጉዳዮች ትኩረት አላደረግኩም። ሌላው ትልቅ ፈተና በዛ የክለባችን ፈታኝ ሰዓት ወደ ሞያው መግባት ነበር እሱም ከእግዚአብሄር ጋር ከሳምሶን አየለ እና ገብረኪሮስ አማረ በጋራ በመሆን ጥረታችን ሰምሯል።

ሌላ በግሌ ከነበሩት ፈተናዎች ስናይ ደግሞ ከተጫዋቾች ጋር የነበረው ነገር ነው። መጥፎ ነገር እያየው ዝም ማለት አልችልም። በዚህም ከተጫዋቾች ጋር አንገት ለአንገት እስከመተናነቅ እና እስከመጣላት እደርስ ነበር። ቡድኑ በሊጉ እንዲቆይ የምንችለው ሁሉ ለማድረግ ስለተስማማን ከሱ በተቃራኒው የሚሄድ ሰው ሳይ ዝም አልልም ነበር። ቅድም እንዳልኩህ አንገት ለአንገት እስከ መተናነቅ እደርስ ነበር እንደዛ ማድረግ ተገቢ ባይሆንም በዛን ሰዓት የነበሩ ሁኔታዎችና ፈተናዎች እንደዛ ለማድረግ ያስገድዱ ነበር። እንደዛ ስላደረግንም እቅዳችን አሳክተናል። አሁን እንደውም ከተጫዋቾቹ ጋር ግዜው ስናስታውሰው ጥሩ ትዝታ አለብን።

መጀመርያ ዙር ከጎንህ ሆነው በመጫወት ላይ የነበሩትን ተጫዋቾች በሁለተኛው ዙር ማዘዙ አልከበደህም ?

አምበል ሆኜ ብዙ ዓመት ስለመራው እሱ ጠቅሞኛል። ከዚ በፊት በተመሳሳይ ለማዘዝም ለመምራትም አልቸገርም ነበር። ሌላው ደግሞ አብዛኞቹ ተጫዋቾች ደስ የሚሉ ታዛዦች ነበሩ በተለይም ታዳጊዎቹ የሽረ ተጫዋቾች ብዙ ነገር አግዘውኛል።


 እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

 ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ