ተጫዋቾች፣ አሰልጣኞች እና የክለብ አመራሮችን በቀላሉ የሚያገናኘው ይህ መተግበሪያ በኢትዮጵያውያን እየበለፀገ እንደሆነ ተሰምቷል።
ስፖርታዊ ክንውኖች በተቋረጡበት በዚህ ወቅት ተጫዋቾች በየቤታቸው ሆነው በተናጥል ልምምዶችን እየሰሩ ይገኛሉ። ከዚህ አልፎም አንዳንድ አሰልጣኞች ለተጨዋቾቻቸው በቴሌግራም አማካኝነት የስልጠና ምስሎችን እየላኩላቸው ልምምዶችን ሲያሰሩ እንደነበረ ሲነገር ቆይቷል።
ዛሬ ሶከር ኢትዮጵያ በደረሳት መረጃ ደግሞ ይህንን የተጫዋቾች ስልጠና የሚያቀላጥፍ መተግበሪያ (application) በሃገር በቀል ልጆች እየበለፀገ እንደሆነ ታውቋል። ኤክስ ፒ ኤስ (XPS) የተባለው ይህ መተግበሪያ የተጫዋቾችን መረጃ ፣ የስልጠና ምስሎችን እና ፕሮግራሞችን በተሟላ እና በተብራራ መልኩ የሚይዝ እንደሆነ ተነግሯል። መተግበሪያው በተለይ አሰልጣኞችን እና ተጨዋቾችን በጥሩ መንገድ የሚያቀራርብ እንደሆነ ተገልጿል። በተጨማሪም መተግበሪያው አሰልጣኞች የሚሰጧቸውን እና የሚያወጧቸውን የስልጠና እቅዶች በአግባቡ መዝግበው እንዲይዙ እንደሚያስችል ተጠቁሟል።
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የቴክኒክ ዲፓርትመንት እና መተግበሪያውን በሚሰሩት አካላት ግንኙነት እየበለፀገ የሚገኘው ይህ መተግበሪያ በሚቀጥለው ሳምንት ይፋ ሲሆን በቅድሚያ ለኢትዮጵያ ወንዶች እና ሴቶች ብሄራዊ ቡድኖች አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ተሰምቷል። በመቀጠል መተግበሪያውን የሚሰሩት ግለሰቦች ከክለቦች ጋር በሚፈጥሩት ግንኙነት መተግበሪያው አገልግሎት ላይ ይውላል ተብሏል።
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ