“የ1984 የውድድር መሰረዝ ታሪክ” ትውስታ በገነነ መኩርያ (ሊብሮ)

በ1983 የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ በነበረው አለመረጋጋት ሲካሄድ የነበረው የውስጥ ውድድር መሠረዝ እና ሀገራዊ ሻምፒዮናው አለመካሄድን በትውስታ አምዳችን ማቅረባችን ይታወሳል። በዛሬው መሰናዷችን በቀጣይ ዓመት (1984) ያጋጠመውን ተመሳሳይ የውድድር መሠረዝ አስመልክቶ ከገነነ መኩሪያ (ሊብሮ) ጋር ያደረግነውን ቆይታ ይዘን ቀርበናል።

በ1983 የአዲስ አበባ ሻምፒዮና የ17ኛ ሳምንት ተጠናቆ የ18ኛ ሳምንት ጅማሮ ላይ በመንግሥት ለውጥ ምክንያት ቀሪ ውድድሮች መሰረዛቸውና ቀጥሎ ሊካሄድ የነበረው የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ሳይካሄድ መቅረቱ ይታወቃል። በወቅቱ በተወሰነው ውሳኔ የአዲስ አበባ ውድድር ቻምፒዮንም ሆነ ወራጅ ቡድን እንዳይኖር ተደርጎ መሰረዙን መግለፃችን የሚታወስ ነው። የ1984 ውድድር ሲጀመር የ1983 ውሳኔ ተፅዕኖ የፈጠረውን ውዝግብ በማስተናገድ ነበር። ገነነ መኩርያ ስለ ወቅቱ ሁኔታ በዚህ መልኩ ያስታውሰናል፡-

“የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን የ1984 ውድድር ለመጀመር ዓምና (1983) ከነበሩት 12 ቡድኖች መካከል ወረጅ መኖር ስላለበት ሜታ ቢራ እና ባህር ኃይልን ወደታች በማውረድ በከፍተኛ ዲቪዚዮን እንዲትጫወቱ በምትካቸውም ፊናንስ እና አግሮ ኢንደስትሪ አንዲያድጉ ውሳኔ ወስኖ ነበር። ሆኖም ሁለቱም ቡድኖች (ሜታ ቢራ እና ባህር ኃይል) ‘አንወርድም፤ በከፍተኛ ዲቪዝዮንም አንጫወትም’ በማለት ከወቅቱ “ከሠላምና መረጋጋት” ኮሚቴ በውድድሩ ይሳተፉ እንዳይወርዱ የሚል ደብዳቤ ይዘው በመምጣትቸው ሳይወርዱ ቀሩ። ከታችኛው ዲቪዚዮን ያሉት ፊናንስ እና አግሮ ደግሞ ‘እኛ ማደግ አለብን’ በማለት እነሱም ደብዳቤ ይዘው መጡ። በነገራችን ላይ በወቅቱ ማንም ከፈለገበት ቦታ ደብዳቤ ይዞ ከመጣ ይፈፀምለት ነበር። በዚህ ምክንያት የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን አስታራቂ ሀሳብ ብሎ የ1984 ውድድርን በ14 ቡድኖች መካከል እንዲካሄድ በማለት ህዳር 6 ቀን 1984 ውድድሩን ጀምሯል።

በዛን ዓመት በዓላት እጅጉን በዝተው ነበር። ለምሳሌ የኦሊምፒክ ሳምንት፣ ግንቦት 20 እና የተለያዩ የፌስቲቫል ጨዋታዎች ክልል ላይ በዝተው ስለነበር ክለቦቹ እየተጠሩ በመሄዳቸው ምክንያት ውድድሩ ሲቆራረጥ ቆይቶ እየተጓተተ ሰኔ ወር ላይ ለመድረስ ተገዶ ነበር። የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽንም ክረምት በመግባቱ ሜዳው መጨቅየት ውድድሩን ለመጨረስ እኖዲቸገር ምክንያት ሆኖታል። በጊዜው የኢትዮጵያ ወጣት ቡድን ከቶጎ አቻው ጋር ሊጫወት በሚዘጋጅበት ወቅት ሜዳው በጣም ጨቅይቶ ስለነበረ ቶጎዎች ‘በዚህ ሜዳ አንጫወትም’ በማለት መግለጫ መስጠታቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ‘እስከ ሰኔ 20 ውድድሩን እንድትጨርሱ’ በሚል ለአዲስ አበባ አሳውቆ ነበር። ይህን ባለ ማግስት ውድድሩ ስምንት ሳምንታት ሲቀሩት (20ኛው ሳምንት ላይ) የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በአዲስ አበባ ፌዴሬሽን የሚመራውን ውድድር አስቁሞ ውጤቱን ሙሉ ለሙሉ በመሰረዝ በአዲስ አበባ ስር የነበሩትን ከአንድ እስከ ስምንት የነበሩትን ስምንት ቡድኖች ብቻ ወደ ራሱ (ኢትዮጵያ ሻምፒዮና) ጠቅልሎ ለመውሰድ ውሳኔ አስተላልፏል። በውሳኔው መሠረትም ቅዱስ ጊዮርጊስ (አዲስ ቢራ)፣ ቡና ገበያ፣ መድን፣ ባንኮች፣ መብራት ኃይል፣ አየር ኃይል፣ ኪራይ ቤቶች እና አግሮ የኢትዮጵያ ሻምፒዮና አካል ሆኑ። የሚገርመው በወቅቱ ዘጠነኛ እና አስረኛ ደረጃ ላይ የነበሩት ክለቦች ስምንት ውስጥ የመግባት እድል ነበራቸው። ምክንያቱም ተስተካካይ ጨዋታ ይቀራቸው ስለነበረ ውድድሩ በመሰረዙ ምክንያት ስምንት ውስጥ ሳይገቡ ቀርተዋል። በዚህም ተጎጂ የሆኑት እርሻ ሠብል፣ ኦሜድላ እና መቻል ነበሩ። ይህ ሲሆን አዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን አቅም ስለሌለው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እንዳይቀጣው በመፍራት ቡድኖቹ ሲወሰዱበት ዝም ብሎ ተመልክቷል። የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽንም በ1985 በስምንቱ ቡድኖች መካከል የኢትዮጵያ ሻምፒዮን ውድድር ጀምሯል።

በ1984 በተቋረጠው ውድድር ወቅት ቅዱስ ጊዮርጊስ 28 ነጥብ በመያዝ አንደኛ ሲሆን ኢትዮጵያ መድን 27 ነጥብ ይዞ ሁለተኛ ደረጃ ቢይዝም አንድ ጨዋታ ፎርፌ አግኝቶ ሳይፀድቅለት እንዲሁም አንድ ቀሪ ጨዋታ ኖሮት ውድድሩ ተቋርጧል። በወቅቱም የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ሳይካሄድ በቀጥታ ከላይ በተቀመጠው የደረጃ ሠንጠረዥ መሠረት ቅዱስ ጊዮርጊስ በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ (በወቅቱ የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮና) ሲሳተፍ ኢትዮጵያ መድን በአፍሪካ ኮፌዴሬሽን ካፕ (በወቅቱ ካፍ ካፕ) ተሳታፊ በመሆን ያን ትልቅ ታሪክ መስራት የቻለበት አጋጣሚ ተፈጥሯል። መድን በውድድሩ የሩዋንዳው ራዮን ስፖርት፣ የሱዳኑ አልሜሪክ የናሚቢያው ያንግ ኦንስን፣ የኒጀሩ ዙማንታን አሸንፎ በኢትዮጵያ ክለቦች ታሪክ በውድድሩ ለግማሽ ፍፃሜ የበቃ ታሪካዊ ክለብ ለመሆን በቅቷል።

* በቀጣይ ትውስታ አምዳችን የኢትዮጵያ ሻምፒዮና በአዲስ መልክ ተፈጠረበትን ክስተት በትውስታ አምዳችን ከገነነ መኩርያ ጋር ያደረግነውን ቆይታ ይዘን እንመለሳለን።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ