የሐረር ከተማ እግርኳስ ባለውለታ የድጋፍ ጥሪያቸውን አቅርበዋል

በትንሿ ሐረር ከተማ ውስጥ ያለበቂ ድጋፍ የክልሉን እግርኳስ መስመር እንዲይዝ ባላፉት 20 ዓመታት ከፍተኛ ጥረት ካደረጉ ባለውለተኞች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት አቶ መሊዮን ዱባለ (ጋሽ መሊ) የስፖርት ቤተሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጥሪ አቅርበዋል።

በ1942 በሐረር ከተማ ልዩ ሥሙ ቀላዳንባ የተወለዱት ይህ ሰው ለስፖርት ሰው በተለይ ለእግርኳስ ሁለተናቸውን የሰጡ ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም። በእግርኳስ ተጫዋችነት በከፍተኛ-3 ፣ ወልዋሎ፣ መብራት ኃይል፣ ካራማራ፣ ድሬዳዋ ባቡር እንዲሁም ሐረር ቢራ በመሳሰሉ ክለቦች አሳልፈዋል። ከተከላካይ ስፍራ እየተነሱ በማጥቃቱ ላይ በነበራቸው ተሳትፎና ሙሉ ሜዳ በማካለል ብርታታቸው ይታወቁ የነበሩት (ጋሽ መሊ) ከተጫዋችነት ከተገለሉ ወዲህ በእግርኳስ ስልጠናው አይረሴ አሻራን በከተማው አሳርፈዋል።

በሀገራችን በ1990ዎቹ መጀመሪያ ከተቀጣጠለው የታዳጊዎች ፕሮጀክት እንቅስቃሴ ዓመታት በፊት ታዳጊዎችን በማሰልጠን በጀመረው የስልጠና ህይወታቸው ለረጅም ዓመታት ታዳጊዎች ላይ መጠነ ሰፊ ሥራን ከመስራታቸው በዘለለ በ1991 መቐለ ላይ በተደረገው የመጀመሪያው የታዳጊዎች (under-15) ውድድር ሐረሪ ክልልን የሁለት ዋንጫዎች ባለቤት ከማድረግ ባለፈ በ1994 ድሬዳዋ ላይ በተደረገው የሀገርአቀፍ የትምህርት ቤቶች ውድድር ሀረሪ ክልልን እየመሩ የብር ሜዳልያ ተሸላሚ መሆን ችለዋል።

ከከተማ አልፈው በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚገኙ ታላላቅ ክለቦች በመጫወት እስከ ብሔራዊ ቡድን ድረስ የደረሱት እነ አሰግድ ሰይፉ ፣ አምሃ በለጠ ጨምሮ እስከአሁኖቹ አቤል እንዳለ እና ሄኖክ መርሹ ድረስ ከከተማው የፈለቁ ተጫዋቾች በአንድም ሆነ በተዘዋዋሪ መልኩ የአሰልጣኝ መሊዮን ዱባለ አሻራ አርፎባቸዋል ቢባል ማጋነን አይሆንም።

አሰልጣኙ በወንዶች እግርኳስ ላይ ብቻ ሳይገደቡም በክልል ደረጃ የሴቶችን እግርኳስ በፈር ቀዳጅነት በማስጀመር በአሁኑ ወቅት በመከላከያ እግርኳስ ክለብ እና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የምናውቃት ሄለን ሰይፉን ጨምሮ በርካታ ተጫዋቾችን ማፍራት ችለዋል።

በአሰልጣኝነቱ የቢ- ላይሰንስ ባለቤት የነበሩት አሰልጣኙ ከእግርኳሱ በተጨማሪ በስካውት እንዲሁም በማስ-ስፖርት አሁን ድረስ በደማቁ የተፃፉ ታሪኮች ባለቤት የሆኑ ሲሆን ያለፉት ጥቂት ዓመታት ግን እንደ ቀደሙት ዘመናት ስራቸውን በትጋት እንዳይሰሩ እክል በሆነ የስኳር ህመም እየተሰቃዩ ይገኛል።

ታድያ ስኳር በሽታው ከእድሜ መግፋት ጋር ተዳምሮ ከዓመታት በፊት አንድ እግራቸውን ቢያጡም ከዚያ ስቃይ በኃላ እንኳን በሚወዱት እግርኳስ ላይ ፊታቸውን ማዞርን አልመረጡም ፤ ይልቁንም በክራንች እና በሰዎች ድጋፍ ውድድር ይደረግባቸው በነበሩ የከተማው ሜዳዎች ሁሉ አይጠፉም ነበር።

አሁን ደግሞ ከቀናት በፊት ሁለተኛ እግራቸውን በዚሁ በሽታ አጥተው አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ። አሰልጣኙ በጉዳዮ ዙርያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት አጠር ያለ የስልክ ቆይታ አንደተናገሩት ምንም እንኳን ሁለት እግራቸውን ቢያጡም አሁንም ቢሆን ከሚወዱት እግርኳስ ሜዳ የሚያመሩበት ቀንን እንደሚናፍቁ ይናገራሉ።

ለዚህም ይረዳቸው ዘንድ ለእንቅስቃሴ የሚረዳ የኤሌክትሪክ ሞተር ብስክሌት ድጋፍ ቢደረግላቸውም አሁንም ቢሆን ከሚወዱት እግርኳስ መራቅ እንደማይፈልጉ ገልፀዋል፤ በተጨማሪም በአሁን ወቅት ያለበቂ ድጋፍ በአንድ የቀድሞ ተማሪያቸው መልካም ፈቃድ እጅግ ጠባብ በሆነች አንድ ክፍል ውስጥ እየኖሩ የሚገኙት አሰልጣኙ የክልሉ መንግስት ሆነ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የመኖሪያ ቤት ችግራቸውን እንዲቀርፏላቸው ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።

አያይዘውም ሲናገሩ ምንም እንኳን በዚህ ወቅት ከእሳቸው በባሰ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ እርዳታን የሚሹ ሰዎች ቢገኙም ሰዎች የተቻላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

ታድያ ይህን የሐረር ከተማ የእግርኳስ ባለውለታን ለመርዳት በበጎ ፈቃደኝነት አራት አባላት ያሉት ስብስብ ተቋቁሙ ወደ ስራ የተገባ ሲሆን አሰልጣኙን ለመርዳት ሆነ ለማበረታት በ0933269998 በመደወል በቀጥታ ማግኘት የሚችሉ ሲሆን በተጨማሪም ድጋፍ ለማድረግ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በስሙ በተከፈተው ተከታዩ የሂሳብ ቁጥር ማለትም 1000084172417 ድጋፍ ማድረግ የምትችሉ ይሆናል።

በተጨማሪም የተቋቋመው የድጋፍ አስተባባሪ ስብስብ አባላትን ከስር በተቀመጠው ተንቀሳቃሽ ስልክ ቁጥራቸው በመደወል ድጋፍ ሊያደረጉ በሚችሉባቸው መንገዶች ዙሪያ መነጋገር እንደሚቻል አስተባባሪዎቹ ገልፀውልናል።

አሰልጣኝ ጌቱ ነጋሽ – 0920904123
ሰለሞን ተሰማ – 0910651994
ዳግም በለጠ – 0912140896
ግርማ ባልቻ – 0986810489

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ