ተስፈኛው ወጣት ዊልያም ሰለሞን

በከፍተኛ ሊግ እየተሳተፈ ለሚገኘው መከላከያ ከተስፋ ቡድን ወደ ዋናው ቡድን ባደገበት ዓመት እጅግ አስገራሚ እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኘው ዊልያም ሰለሞን በተስፈኛ አምዳችን የዛሬ እንግዳችን ነው።

ዊልያም ሰለሞን ይባላል። በምስራቅ ሐረርጌ ተወልዶ ያደገው ዊልያም ከፕሮጀክት ምዘና ውድድር ባሳየው መልካም እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ በመግባት ለተወሰነ ዓመት ቆይቶ በማድረግ ሳይጨርስ ወጥቷል። በዚህም ተስፋ በመቁረጥ እግርኳስ አቁሞ የነበረ ቢሆንም የልጁን አቅም ተረድቶ ይከታተለው የነበረው አሰልጣኝ ዳግመኛ ወደ እግርኳስ ተመልሶ ዘንድሮ ለመከላከያ በከፍተኛ ሊግ እየተጫወተ ይገኛል። በሚያደርገው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ የብዙዎች አድናቆትን እያገኘ የሚገኘው የመስመር አጥቂ፣ አማካይ ሆኖ መጫወት የሚችለው ዊልያም ለኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ጥሪ ቀርቦለት በቅርቡ መጫወት ችሏል። ቀልጣፋ፣ ፈጣን ኳስን መጫወት የሚችል ደፋር ተጫዋች የሆነው ዊልያም በዚህ እድሜው የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በርትቶ እና ጠንክሮ በመስራት እድገቱን ጠብቆ መዝለቅ ከቻለ በቅርቡ ትልቅ ተጫዋች የመሆን ዕድሉ አለው። በዛሬው ተስፈኛ አምዳችን ከዊልያም ጋር ያደረግነውን አጭር ቆይታ ይዘን ቀርበናል።

” የተወለድኩት ሐረር ከተማ ነው። ዜድ ዩናይትድ የሚባል ቡድን በ13 ዓመቴ በመቀላቀል እግርኳስን መጫወት ጀምሬያለው። ከሐረር ተመርጠን የ15 ዓመት በታች የኦሮምያ ታዳጊዎች ውድድር ወደ አዳማ መጥቼ ባሳየሁት መልካም እንቅስቃሴ ተመርጬ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ለመግባት ችያለው። ከ2008-10 ድረስ አካዳሚ ከቆየው በኋላ በአንዳንድ ምክንያቶች ከአካዳሚ ወጥቼ ወደ ሐረር ተመልሼ ነበር። በዚህም ተስፋ ቆርጬ ለአንድ ዓመት ልምምድ መስራት አቁሜ ከእግርኳስ ርቄ ነበር። ሆኖም እንደ አሰልጣኝም እንደ አባት የማየው እስክንድር ‘ለምን አንተ ትልቅ አቅም እያለህ ወደፊት ትልቅ ደረጃ መድረስ እየቻልክ እግርኳስን ለምን ታቆማለህ’ ሲለኝ ምን ላድርግ ኳሱን ያቆምኩት ቁጭ ከምል እናቴን መርዳት ስለምፈልግ የግል ስራ እየሰራው ነው አልኩት። ‘ለምን? አንተ ተስጥኦ ያለህ ተጫዋች ስለሆንክ ስራ’ ሲለኝ ወደያው ልምምድ መስራት ጀመርኩኝ። አዳማ ላይ በተካሄደው ከ17 ዓመት በታች የኦሮምያ ታዳጊ ውድደር ባሳየሁት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ እስከ ፍፃሜ ደርሰን ነበር። ብዙ ክለቦችም ሊወስዱኝ ፈግው የነበረ ቢሆንም ለአካዳሚ ገብቶ የነበረ በዚህ ውድድር እንዴት ትጠቀማላቹ ብለው አወዳዳሪው አካል እኔን፣ ቡድን መሪውን እና አሰልጣኙን ለአንድ ዓመት ከማንኛውም ውድድር አግደውኝ በድጋሚ ተስፋ ቆርጬ በጣም ተረብሼ በቃ እግርኳስ መጫወት ላልችል ነው ብዬ ነበር። ሆኖም መከላከያ ‘ና እኛ ነገሮችን እናስተካክላለን’ ብለውኝ ወደ አዲስ አበባ መጥቼ በ2011 መከላካያ ከ20 ዓመት በታች ቡድን መጫወት ጀምሬያለው። ዘንድሮ ደግሞ ወደ ዋናው ቡድን አድጌ ከፈጣሪ ጋር ጥሩ ጊዜ እያሳለፍኩ እገኛለው። መከላከያ ባለኝ ነገር ሁሉ ደስተኛ ነኝ፤ ባለውለታዬም ነው። ከሁሉም ጋር የመግባባት ተፈጥሮ ስላለኝ ከአመራሩም፣ አብረውኝ ከሚጫወቱ እና ግቢ ውስጥ ካሉ ጋር ባለኝ ግኑኝነት ደስተኛ ነኝ። መከላከያን ከዚህ በላይ ወደ ፊት ማገልገል እፈልጋለው። ራሴንም ትልቅ ደረጃ ለማድረስ ከዚህ በላይ ጠንቅሬ እየሰራው ነው። ከልጅነቴም ጀምሮ ሲጫወት እያየሁት እና እያደነቅኹት ያደኩት ለእኔ አርዐያ የመጣሁበት አካባቢ ልጅ አቤል ከበደ ነው። ከልጅነቴ እርሱን መሆን እየፈለኩ ነው ያደኩት እና ለእርሱ አክብሮት አለኝ። ለእኔም እዚህ ደረጃ መድረስ ትልቅ አስተዋፆኦ ላደረጉልኝ በሙሉ አመሰግናለው።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ