የ2012 የፕሪምየር ሊግን ሙሉ በሙሉ የሰረዘው የሊግ ኩባንያ በውድድር ዓመቱ የተወሰኑና በቀጣይ ውሳኔያቸው ተግባራዊ ሊሆኑ የነበሩ የዲሲፕሊን ቅጣቶችን ይጨምራል ወይስ የሚል ጥያቄ እየተነሳ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት የኮረና ወረርሽኝ እንደ ሀገር መቆጣጠር እንደሚቻል ማወቅ አስቸጋሪ በመሆኑ የ2012 የሊግ ውድድሮች ሙሉ በሙሉ መሠረዙ ይታወቃል። ነገር ግን ይህ ውሳኔ በደፈናው የቀረበ በመሆኑ ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን አላካተተም። ውሳኔው ውጤትን መሠረት ያደረገ ብቻ ነው ወይስ በ2012 የውድድር ዘመን በተፈፀሙ የሥነ ሥርዓት ጥፋቶች ላይ የተወሰኑ ውሳኔዎችን ይጨምራል? (ለምሳሌ የክለቦች የገንዘብ ቅጣት፣ የሜዳ ላይ ጨዋታ ቅጣት፣ የተጫዋቾች ቅጣት፣ ወዘተ…) የሊግ ካምፓኒው በቅርቡ ባስተላለፈው ውሳኔ በግልፅ ያስቀመጠው ዝርዝር ነገሮች ባለመኖሩ ከተለያዩ አካላት በዚህ ዙርያ ጥያቄዎች እየቀረቡልን ይፈየገኛል። በጉዳዩ ዙርያ ምላሽ ለማግኘት ለተለያዩ የስፖርት ባለሙያዎች ስልክ በመደወል የሰጡንን ምላሽ እንዲህ ጠቅልለን አቅርበነዋል።
“አወዳዳሪው አካል የ2012 የሊግ ውድድሮች ሙሉ በሙሉ መሰረዝ፣ በየትኛውም ሊግ ሻምፒዮን እንዲሁም ወራጅ የሌለ በመሆኑ እና በፕሪምየር ሊጉ ከሚሳተፉ ቡድኖች ቀጣይ ዓመት በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ እና በኮንፌዴርሽን ካፕ ኢትዮጵያን የሚወክል ክለብ አይኖርም በማለት በግርድፉ ዝርዝር ነገሮችን በጥልቀት ሳይመለከት ውሳኔውን አሳውቋል። ይህ ውሳኔ ባለሙያዎችን ሳያማክሩ በጥድፊያ የወሰኑት ውሳኔ በመሆኑ እንደነዚህ ያሉ አሻሚ (አወዛጋቢ) ጥያቄዎች እንዲነሳ ያደርጋሉ። በመሠረቱ በዲሲፒሊን መመርያው ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው። የዲሲፕሊን ቅጣቶች የሚሻሩበት ምክንያት በማለት የተቀመጡት፡-
1. በይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ
2. የስፖርት ግልግል ፍርድቤት (ካስ)
3. አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በይቅርታ ህግ ነው።
ከዚህ ውጭ ጨዋታ በመቋረጥ (በመሰረዙ) ምክንያት የዲሲፒሊን ቅጣቶች በፍፁም አይቋረጡም፤ እንዳለ ይኖራሉ፣ ይቀጥላሉ (ተሻጋሪ) ይሆናሉ።
” ለምሳሌ አንድ ቡድን በሜዳው በሚያደርገው ጨዋታ የስፖርታዊ ጨዋነት ጥሰት (ረብሻ) ተከሰተ ተብሎ ሜዳው አንድ ወይም ሁለት ጨዋታ ከሜዳው ውጭ እንዲጫወት ቢቀጣ ወደፊት ከሚኖረው ጨዋታ ይቀጣል ካለ ወደፊት የትኛው ጨዋታ እንደሆነ አይታወቅም። ተቋርጦ ሲጀመር ሊሆን ይችላል። የሥነስርዓት ጥሰት ቢሆንም ለምሳሌ ዳኛ መማታት፣ ለመማታት መጋበዝ፣ ፀያፍ ስድብ ሌሎችም ውሳኔዎች ቢወሰኑ በቀጣይ ተግባራዊ ይሆናል ማለት ነው።”
በዚህ ዙርያ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ህዝብ ግንኙነት ዲፓርትመንት ኃላፊ እና ጊዛዊ ዋና ፀኃፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን የሚከተለውን ብለውናል…
“ጥያቄው ተገቢ ነው። ምንም እንኳን ውሳኔ በግልፅ ባያስቀምጠውም። የውድድሩ መሰረዝ ከዲሲፕሊን ቅጣቶች ጋር አይገናኝም። በዚህ የውድድር ዓመት ውሳኔ የተላለፈባቸው የትኛውም የዲሲፕሊን ቅጣቶች አይሻሩም (አይሰረዙም) ለቀጣይ ዓመትም ተሻጋሪ ሆነው ይቀጥላሉ።”
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ