ቅዱስ ጊዮርጊስ የፌዴሬሽኑን ውሳኔ አክብሮ ለተጫዋቾች እና ሠራተኞቹ የደሞዝ ክፍያ እንደሚፈፅም አስታወቀ

በኮሮና ወረርሺኝ ምክንያት ውድድሮች መሠረዛቸውን ተከትሎ ክለቦች የተጫዋቾቻቸውን ውል አክብረው ተገቢውን ደሞዝ እንዲፈፅሙ የሊግ ኩባንያው ማሳወቁ ይታወቃል። ለዚህ ምላሽ የሰጠው ቅዱስ ጊዮርጊስ በይፋዊ የፌስቡክ ገፁ ካሰፈረው መረጃ መካከል ስለ ደሞዝ ጉዳይ ይሄን ብሏል።

“ይህ ጊዜ ለሀገራችን እግር ኳስ ክለቦች እጅጉን ከባዱና ፈታኙ ወቅት እንደሆነ እናምናለን፡፡የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበርም ህዝባዊ ክልብ እንደመሆኑና ከመንግስት የሚያገኘው ምንም አይነት ድጎማ ባለመኖሩ በዚህ ከባድ ፈተና ውስጥ እየተፈተኑ ካሉት ክለቦች መካከል አንዱ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ምንም እንኳን ወቅቱ ለስፖርት ማህበራችን እጅግ ፈታኝና አስቸጋሪ ቢሆንም ማህበራችን ችግሮቹን ተቋቁሞ ህልውናውን ለማስቀጠል ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

” ቅዱስ ጊዮርጊስ የስፖርት ማህበር የዋናው የወንዶች ቡድን፣የሴቶች ቡድን፣ከ20 አመትና ከ17 አመት በታች የታዳጊና የተስፋ ቡድን እንዲሁም የክብደት ማንሳት ቡድኖች ባለቤት ነው፡፡በተጨማሪም የስፖርት ማህበሩን በልዩ ልዩ የሙያ መስኮች የሚያገለግሉ በርካታ ከፍተኛና መካከለኛ ባለሙያዎች አሉት፡፡ማህበራችን ይህ ፈታኝ ጊዜ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ ለማወቅ ቢቸገርም አላፊ መሆኑን ግን በሚገባ ይገነዘባል፡፡ስለሆነም በቻለው አቅም ሁሉ ከተጫዋቾቹ በተጨማሪ በዋናው ጽህፈት ቤት፣ በስፖርተኞች ሆስቴል፣በክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ የታዳጊዎች ማሰልጠኛ አካዳሚ ለሚገኙ ሰራተኞቹ ወርሃዊ ደሞዛቸውን ሳጓድል በመክፈል ሃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ ይገኛል፡፡ በዚሁ አጋጣሚ በተጫዋችነትም ሆነ ልዩ ልዩ የሙያ መስኮች ተሰማርታችሁ የስፖርት ማህበራችን እያገለገላችሁ የምትገኙ በሙሉ በተረጋጋ መንፈስ ስራችሁን እንድትቀጥሉ ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡መላው የክለባችን አባላትና ደጋፊዎቻችንም እንደተለመደው ከታላቁ ክለባችሁ ጎን በመቆም ይህን ጊዜ በመደጋገፍ እንድናሳልፈው ጥሪያችንን ለማቅረብ እንወዳለን፡፡ ”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ