“የፊርማ ገንዘብ እና ቅዥቱ… የአሰልጣኝ አሥራት ኃይሌ የማሸነፍ ፍላጎት” ትውስታ በመስፍን አህመድ (ጢቃሶ)

በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ ትልቅ ሥም ካላቸው አሰልጣኞች መካከል አሥራት ኃይሌ አንዱ ናቸው። ከውጤታማነታቸው በተጨማሪ ቁጣ የተቀላቀለበት ቆፍጣና የተጫዋቾች አመራር ዘይቤያቸው በብዙዎች ዘንድ ይመሰከርላቸዋል። ይህ የ”ጎራዴው” ዘይቤ አተገባበር እስከምን ድረስ ነበር? በአሰልጣኙ ስር የተጫወተው መስፍን አሕመድ በግል የፌስቡክ ገፁ ያቀረበውን ፅሁፍ ፍቃድ በመጠየቅ እና ተጨማሪ ሀሳቦችን እንዲያካትትበት በማድረግ ” በትውስታ ” አምዳችን እንዲህ አቅርበነዋል።

እግርኳስ ባለውለታዬ ነው። ከምወደው መድን የአራት ዓመት ቆይታ በኋላ በ1997 ወደ መከላከያ በወቅቱ ትልቅ በሚባል የፊርማ ገንዘብ 20 ሺ ብር ተከፍሎኝ አመራሁ። በጊዜው አሰልጣኝ የነበረው ታላቁ አሰልጣኝ አሥራት ኃይሌ (ጎራዴው) ነበር። በመከላከያም በተቀላቀልኩበት ጊዜ ሌሎች ስመጥር የሚባሉ ጠንካራ ተጫዋቾች የነበሩበት በመሆኑ ትልቅ ፈተና እንደሚጠብቀኝ አስባለው። ይህ ክለብ ትልቅ ታሪክ ያለው ክለብ በመሆኑ መሸነፍን አምርረው የሚጠሉ ተጫዋቾችም ሆኑ ደጋፊዎች ያሉበት ክለብ ነው። አሰልጣኝ አሥራት መሸነፍን አምርሮ የሚጠላ ተጫዋቾቹም ላይ ይህንን ባሕርይ የሚያሰርፅ አሰልጣኝ ነው። ከእሱ ጋር ስትሰራ ለማልያ ፍቅር እዲኖርህ፣ የለበስከው ማልያ ጨርቅ ብቻ እንዳልሆነ እና ማልያ ክብር እዳለው ትረዳለህ። ሁሌም ሲናገር “ማሸነፍ የሚገነባው በሚሰጥህ የማበረታቻ ገንዘብ (ኢንሴንቲቭ) አይደለም። ከውስጥህ የሚመነጭ ስሜት ነው። ሁሌም ደሞዝ ለሚከፍልህ ቡድን እንዲሁም ለምትወዳት ኳስ ክብር ይኑርህ፤ ህይወትህን የምትመራው በእርሷ ነው” እያለ በከፍተኛ የሥነ ልቦና ሁኔታ ተጫዋቾችን ያነሳሳል፣ ሽንፈትን እድንጠላ ያደርጋል።

የዝግጅት ጊዜያችንን ጨርሰን የፕሪምየር ሊግ ውድድሩም ወቅቱን ጠብቆ ተጀመረ። የመጀመርያ ጨዋታችን በአቻ ውጤት ተለያየን፤ አሥራት ደስተኛ አልነበረም። ሁለተኛው ጨዋታም እንደ መጀመርያው ሁሉ በአቻ ውጤት ተጠናቀቀ። ግምገማው በዛ፤ የአሥራት ቁጣም ጨመረ። ለሦስተኛው ጨዋታ በከፍተኛ ሁኔታ ተዘጋጀን ይህንን መሸነፍ የለብንም። አሸንፈን መውጣት አለብን በሚል ስሜት ሁላችንም የጨዋታውን ቀን መጠበቅ ጀመርን። ግን የሆነው ሌላ ነው። አብዛኞቻችን የሚጠበቅብንን ሜዳ ውስጥ ማድረግ ባለመቻላችን በሙገር 2-1 ተሸነፍን። አሥራትን ገና ወደ ካምፕ ሳንሄድ ሜዳ ውስጥ ሆነን ስናየው በጣም ያስፍራል። ከሜዳ መውጣት ከበደን፣ ፈራን፣ መሸነፍ ከአቅም በላይ ሲሆን ምንም አይደለም። አቅምህን አውጥተህ መጫወት አቅቶህ ስትሸነፍ ግን ያማል። አሥራትም ያ ስሜት ነው የተሰማው። ወደ መልበሻ ክፍልም እንገባን የአሥራት ቁጣ ጀመረ። እንደ መብረቅ እየጮኸ “እያንዳድህ የወሰድከውን ብር ትመልሳለህ። የወታደሩን ብር ነው የምትበላው፣ ደም ነው የምትጠጣው።” እያለ እንደ ዕብድ እየጮኸ እና ግድግዳ እየመታ ይናገራል። ሁላችንም አንገታችንን ደፍተን መስማት ነው። በጭንቀት የአብዛኞቻችን አዕምሮ ተወጥሯል። ከመልበሻ ክፍል ወጥተን በወቅቱ ወደ ምንኖርበት ገነት ሁቴል አመራን። እራት በልተን ወደ ክፍላችን አመራን። አብሮኝ አንድ ክፍል የሚጋራኝ ፎቶ ላይ ያለው ታደሰ ይባላል የደሴ ልጅ ነው። “ኧረ ይህ ሰውዬ ሊገለን ነው። ደግሞ ብሩን መልሱ ይላል፤ ለአባቴ ልኬያለው ከየት ነው የማመጣው።” ይላል። እኔም ለእናቴ ሰጥቼ ግማሹ ጠፍቷል እየተባባልን የባሰ ጭንቀት በጭንቀት ሆንን። ሰዓቱም እየመሸም ስለነበር ወደ አልጋችን አመራን ትንሽ እንደተኛው በእንቅልፍ ልቤ “ያዘው… ያዘው…” የሚል ድምፅ ሰማሁ። ዞር ስል አራት የፌደራል ልብስ የለበሱ መሳርያ ታጥቀው የፊርማ የወሰድከውን ብር መልስ ብለው ማባረር ጀመሩ። እኔም መጮህ ጀመርኩ። በእንቅልፍ ልቤ አብሮኝ የተኛውም ታደሰ ምን መጣ ብሎ እየጮኸ ያዘኝ። ሲይዘኝ እነሱ የያዙኝ ስለመሰለኝ በበቦክስ መታሁት። እሱም ኡኡኡ እያለ ከኔ የበለጠ መጮህ ጀመረ። እኔ መጡ መጡ እያልኩ ከግድግዳ እየተጋጨው እጮሀለሁ። እሱ ደሞ “እነማን ናቸው…?” እያለ ይጮሀል። እኔ አልነቃሁም እሺ የእሱ ይለያል በዚህ መሀል ከጎናችን የነበሩት ተጫዋቾች እነ አንተነህ አላምረው ምድነው ብለው ወደ ክፍላችን መግባት ፈርተው የፀሎት መፀሀፍ በበሩ ቀዳዳ ያስገባሉ። እንደምንም ነቅተን መብራት በርቶ ስንተያይ ሁለታችንም ፊታችን አብጧል። እሱ በቦክስ እኔ በግድግዳ … የማያልፍ የለ ነጋና የብዙዎች መማርያ ሆነ።

አሰልጣኝ አሥራት ኃይሌ ለማልያ ክብር እንድንሰጥ የመከረኝ እና ያስተማረኝ ነገር ውስጤ ገብቶ ይኸው ከዛ በኋላ ለለበስኩት ማልያ ያለኝን አቅም ሳልሰስት በትጋት ሰጣለሁ። ከቡድን ጓደኞቼም ጋር በመሆንም ከመከላከያ ጋር የጥሎ ማለፍ ዋንጫን ማንሳት ችያለሁ። ይህ የእኔ የህይወት ተሞክሮ ለዛሬ ወጣት እና ታዳጊዎች ትልቅ ትምህርት ነው። ለምትለብሱት ማልያ ትልቅ ክብር ይኑራችሁ። ደጋፊዎች ከእናንተ ድልን ይፈልጋሉ፤ ታታሪ መሆን አለባችሁ። ድልና ውጤት ያለ መስዋዕትነት አይገኝም። አሰልጣኞችም ተጫዋቾቻችሁን ካለ ማበረታቻ ገንዘብ በስነ ልቦና ማጠንከር አለባችሁ። ይህ ከሚሰጠው ብር በላይ ኃይል አለው። በቀላሉም አይሰበርም ይህ የኔ ጥቂት ልምድ ነው።

“ጢቃሶ” በሚል ቅፅል ስም በይበልጥ የሚታወቀው መስፍን መሐመድ በዘጠናዎቹ ከተመለከትናቸው ጥሩ አጥቂዎች መካከል አንዱ ነው። በአየር ኃይል፣ ኢትዮጵያ መድን፣ መከላከያ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ1994–2007 ድረስ መጫወት ችሏል። ከኢትዮጵያ መድን (1994) እና መከላከያ (1998) ጋር የጥሎማለፍ ዋንጫ ያነሳ ሲሆን በኢትዮጵያ ታዳጊ፣ ኦሊምፒክ እና ዋናው ብሔራዊ ቡድን መጫወትም ችሏል። ከጉዳት ጋር በተያያዘ እግርኳስን ካቆመ በኋላ በአሁኑ ወቅት ወደ አሰልጣኝነቱ ጎራ በመቀላቀል በትውልድ ከተማው ሻሸመኔ “ሻሼ የታዳጊዎች አካዳሚ” በመክፈት እያሰለጠነ ይገኛል።

* በቀጣይ ተመሳሳይ ለአዲሱ የእግርኳስ ትውልድ አስተማሪ ሊሆኑ የሚችሉ መሰል ተሞክሮዎችን ማጋራት አልያም ጥቆማ ማቅረብ ለምትፈልጉ የዝግጅት ክፍላችን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኑን ለመግለፅ እንወዳለን።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ