ተስፈኛው የመስመር ተጫዋች – ዘነበ ከድር

ከእግር ኳሱ ቤተሰብ ጋር በደንብ የተዋወወቀው አምና በደቡብ ፖሊስ ነበር። በሁለቱም መስመሮች የማጥቃትም ሆነ የመከላከል ኃላፊነት ተሰጥቶት በመጫወት በክለቦች ዓይን ውስጥ የገባው ከትምህርት ቤት ውድድር የተገኘነው ዘነበ ከድር የዛሬው የተስፈኛ አምዳችን ትኩረት ሆኗል።

ትውልድ እና ዕድገቱ በወርቅ ምርቷ ብዙዎች በሚያውቋት በሻኪሶ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ እንደአብዛኞቹ የሀገራችን ተጫዋቾች በሠፈር ኳስን በመጫወት ጅማሮውን ያደረገ ሲሆን በግል ጥረቱ እና ከቤተሰቡ በሚያገኘው ተጨማሪ ድጋፍ የእግር ኳስ መንገዱን ስራዬ ብሎ መጀመር ችሏል፡፡ ጅማ ላይ በተዘጋጀ የኦሮሚያ ትምህርት ቤቶች ውድድር ላይ ትውልድ ከተማውን ወክሎ በመጫወት ከቡድን አጋሮቹ ጋር የዋንጫ ባለቤት ሆኗል፡፡ ተጫዋቹ ባሳየው ምርጥ እንቅስቃሴ ለኦሮሚያ ትምህርት ቤቶች ቡድን ተመርጦ ወደ ባህር ዳር የመጓዝ ዕድልም አግኝቷል። በውድድሩም ወክሎ የሄደበትን ክልል አሁንም ከቡድን አጋሮቹ ጋር በመሆን ባለ ድል ያደረገ ሲሆን በብዙ ክለቦች ተፈላጊነቱ እየጨመረ ሊመጣ ችሏል። 2007 ላይ ወደ ገላን ከተማ አምርቶም በክለቡ ሁለት ዓመታትን አሳልፎ በናፍቆት ሳቢያ ለቤተሰቡ ቅርበትን በመፈለግ የነገሌ ቦረና ክለብን በመቀላቀል በ2009 እና 2010 ከተጫወተ በኃላ ነው ይበልጥ ጎልቶ ወደታየበት ደቡብ ፖሊስ ያቀናው።

እግር ኳስን በአጥቂ ስፍራ በመጫወት የጀመረው እና በአሁኑ ሰዓት በአሰልጣኞች ተለዋዋጭ ታክቲክ በግራ እና ቀኝ ማለትም በመስመር አጥቂነት እንዲሁም በተከላካይነት የሚጫወተው ወጣቱ ዘነበ ከድር አምና በፕሪምየር ሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ ከደቡብ ፖሊስ ጋር በመሆን በመጫወት ያሳለፈ ሲሆን በአብዛኛውም በቋሚነት ተሰልፏል፡፡ ተጫዋቹ አምና በክረምቱ የዝውውር መስኮት በሌሎቹ የሊጉ ክለቦች ኢትዮጵያ ቡና ፣ ሀዋሳ ከተማ ፣ አዳማ ከተማ እና ስሑል ሽረ የእናስፈርምህ ጥያቄ ቢደርሰውም ከቢጫ ለባሾቹ ጋር ቀሪ የአንድ ዓመት ውል ስላለው በከፍተኛ ሊግ ከክለቡ ጋር ሊቀጥል ችሏል፡፡ በተለይም አምና በኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ በጥብቅ ሲፈለግ የነበረው ይህ ተጫዋች ስለ ወደፊት ዕቅዱ ይህን ብሏል።

“የግል ጥረቴ ነው እግር ኳስ እንድጫወት ያደረገኝ ፤ የቤተሰቤ ድጋፍ ቢኖርበትም ትልቁን ቦታ ግን ፈጣሪ ይወስዳል። የራሴ ጥረት እና የፈጣሪ ዕርዳታ ነው እዚህ ያደረሰኝ። ከዚህ በኃላ ያለኝ ዕቅድ ከፈጣሪ ጋር ጠንክሬ ሰርቼ የተሻለ ቦታ ለመድረስ ነው። የምፈልግበትም ለመድረስ በደንብ ተዘጋጅቻለሁ። የእኔ ምኞት ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ መጫወት አይደለም ፤ እዛ ለመድረስ ግን ጥንካሬ ያስፈልጋል። ምንም የሚከብደኝ ነገር የለም ፤ ፕሪምየር ሊጉንም አምና አይቼዋለሁ። ዕድሜዬ ገና ነው ፤ በምገባባቸው ክለቦች ለመቀመጥ ሳይሆን ራሴን ለማሳደግ ስል የሚገድበኝ እና የምፈራው ነገር ስለሌለ ያሰብኩትን አሳካለው”።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ