የትግራይ ስታዲየም የመጨረሻው ዙር የግንባታ ሒደት ተጀመረ

ላለፉት በርካታ ዓመታት በግንባታ ላይ የነበረውና በ2009 መጨረሻ ወራት በተሻለ የግንባታ ደረጃ ጨዋታዎች ማዘጋጀት የጀመረው የትግራይ ስታዲየም በመጨረሻው የግንባታ ደረጃ ደርሷል።

በዓመቱ መጀመርያ መቐለ 70 እንደርታ የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ ከማከናወኑ በፊት መጠነኛ ግንባታዎች የተደረገለት ይህ ስታዲየም በዚህ ወቅት የበርና መስኮት ሥራዎች፣ የድህንነት ካሜራ፣ የሽንት ቤት እና መታጠብያ ቤት ስራዎች እና ሌሎች ተጨማሪ ስራዎች እየተሰሩለት ሲገኙ በቀጣይ ወራትም ሌሎች ግንባታዎች እንደሚኖሩ ከትግራይ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ወ/ሮ ካሕሱ ዜናዊ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል።

እንደ ወ/ሮ ካሕሱ ዜናዊ ገለፃ በመጨረሻ ከሚሰሩት የጥላ እና ወንበር ገጠማ ውጪ ያሉት አጠቃላይ ሥራዎች በቀጣይ ወራቶች ለማጠናቀቅ እየተሰራ እንደሆነ ገልፀው በኮሮና ቫይረስ ምክንያት እንደተፈለገው በፍጥነት መሰራት እንዳልተቻለም ተናግረዋል። “እስከ መጨረሻ ላለው ግንባታ ውል አስረናል፤ አሁን ከዚህ ቀደም መጠናቀቅ እየነበረባቸው ያላለቁ ስራዎች በመስራት እንገኛለን። የመፀዳጃ ቤት እና የድህንነት ካሜራ ስራዎች በመሰራት ይገኛሉ። የተቀሩት ስራዎች እንዳይጠናቀቁም የኮሮና ቫይረስ ምክንያት የምንፈልጋቸው እቃዎች በጊዜው ማግኘት አልቻልንም። በቀጣይ የተጀመሩት የመኪና ማቆምያ እና የሦስት በአንድ ትንሿ ስታዲየም እንዲሁም የአጥር ሥራዎች ይሰራሉ። ሌላም ካፍ በሰጠን መመርያ መሰረት ደረጃውን የጠበቀ የመጫወቻ ሜዳ መብራት እንገጥማለን። ” ብለዋል።

ወ/ሮ ካሕሱ አክለውም ስታዲየሙ ካፍ ባስቀመጠው መመርያ መሰረት እየተሰራ መሆኑን ገልፀው የመጨረሻው ምዕራፍ A እና B በሚል የግንባታ ምዕራፎች ከፍለው ለመጨረስ በመንቀሳቀስ እንደሚሆኑ ገልፀዋል።

በሀገሪቱ ከሚገኙ ምቹ የመጫወቻ ሜዳ ካላቸው ስታዲየሞች አንዱ የሆነው የትግራይ ስታዲየም በዚህ ወቅትም መጠነኛ ጥገናዎች እየተደረጉለት ይገኛሉ።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ