ተመስገን ተክሌ የት ይገኛል?

ከአዲሱ ሚሌኒየም ወዲህ በኢትዮጵያ እግርኳስ ብቅ ካሉ ጥሩ አጥቂዎች አንዱ የነበረው ተመስገን ተክሌ አሁን የት ይገኛል?

በፌዴራል ፖሊስ፣ ደደቢት፣ ሀዋሳ ከተማ እና ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተጫወተው ተመስገን በጉዳት ምክንያት የሚጠበቀውን ያህል መጫወት ሳይችል በቶሎ ከዕይታ ጠፍቷል። ያለፉትን አምስት ዓመታት ከሜዳ መራቁን ተከትሎ አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ተጫዋቹን አግኝተን ጠይቀን የሚከተለውን ብሎናል።

“አሁን አዲስ አበባ ነው እየኖርኩ ያለሁት። ጀሞ አካባቢ በግሌ አንዳንድ ሥራዎችን እየሰራሁ እገኛለሁ። መቼም ሰው ነኝና ዝም ብዬ አልቀመጥም፤ ትንሽም ብትሆን እሯሯጣለሁ። በዚህ ሁኔታ ላይ እገኛለሁ፡፡

“እውነት ለመናገር ወደ እግር ኳስ የመመለስ ፍላጎት ውስጤ በጣም አለ። ኳስ ሱስ ነው ለኔ። ሱሱ ደግሞ አልወጣልኝም። ነገር ግን የመጫወት ነገሩ ከውስጤ ወጥቷል። አሁንም ህመሙ አለ። እኔ አሁን ስለመጫወት ሳይሆን ጤነኛ ስለመሆን ብቻ ነው የማስበው፡፡ ለጠየከኝ ጥያቄ ለመመለስ ያህል ግን ነገ ሙሉ ለሙሉ ቢሻለኝ መጫወት እፈልጋለሁ። የተሻለ ሆኜ እቀርባለሁም ብዬ አስባለሁ፤ መጫወት ፈልጋለሁ።”

በተጫዋቹ የእግርኳስ ሕይወት ዙርያ ያደረግነውን ቆይታ በቀጣይ ይዘን የምንቀርብ መሆኑን ከወዲሁ ለመግለፅ እንወዳለን።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ