የሀዋሳ ከተማ እና የደቡብ ፖሊስ ክለብ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች የቁሳቁስ ድጋፍ እና የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ዛሬ አከናወኑ፡፡
ዛሬ ከጠዋቱ 12:00 ላይ የሁለቱ ክለብ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች እንዲሁም ደግሞ ሌሎች በከተማዋ ውስጥ ያሉ ተጫዋቾች ማኅበረሰቡ በእጅ መታጠብ ግንዛቤው እንዲጎላ የእጅ ማስታጠብ ስራን እስከ እኩለ ቀን ድረስ በከተማዋ በተለያዩ አቅጣጫዎች ላይ ሲሰሩ የነበረ ሲሆን ከሰዓት ደግሞ ሁለቱም ክለቦች ለአቅመ ደካማ አረጋዊያን የሚሆን የቁሳቁስ ድጋፍን አድርገዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የሀዋሳ ከተማ ክለብ በክለቡ አባላት ስም ከ150 ሺህ ብር ላይ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ ከተጫዋቾቹ፣ አሰልጣኞቹ እና የደጋፊ ማኅበሩ በተሰበሰበ ገንዘብ ለዚሁ አላማ የሚውል የእህል እና የምግብ ግብዓቶችን አበርክተዋል። የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ግሩም ባሻዬም በግሉ ካደረገው ስጦታ ባሻገር ከእግር ኳሱ ውጪ ያሉ ጓደኞቹን በማስተባበር ልገሳን አድርጓል፡፡ ከሀዋሳ ከተማ በተጨማሪ በከፍተኛ ሊጉ እየተወዳደረ የሚገኘው ደቡብ ፖሊስም እንደ ሀዋሳ ከተማ ሁሉ የእህል እና እህል ነክ ነገሮችን ከተጫዋቾቹ በተሰበሰ ገንዘብ ገዝተው ለተቋቋመው ኮሚቴ አስረክበዋል፡፡ ከሁለቱም ክለብ ባሻገር በርካታ ስፖርተኞችን በህክምና ሙያ እያገለገለ የሚገኘው ብሩክ ደበበ እና የኢትዮጵያ ቡናው አማካይ ፍቅረየሱስ ተክለብርሃን በግላቸው ድጋፍን አድርገዋል፡፡
በድሬዳዋ ከተማ እና በሰበታ ከተማ በፕሪምየር ሊግ ክለቦች የተጀመረው የደም ልገሳ ስራም በዛሬው ዕለት ከተሰጠው የቁሳቁስ ድጋፍ ባሻገር የሁለቱን ክለቦች ጨምሮ ደጋፊዎች እና በግል ፍቃደኛ የሆኑትን በማካተት የደም መለገስ ተግባርም ተከውኗል፡፡
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ