የ2011 ኮከቦች የገንዘብ ሽልማት በዚህ ሳምንት ተግባራዊ ይሆናል ተባለ

ተደጋጋሚ ቅሬታ በተሸላሚዎቹ ዘንድ ሲነሳበት የቆየው የ2011 የሊጎቹ ኮከቦች ሽልማት ከወራቶች መጓተት በኃላ ከዚህ ሳምንት ጀምሮ የገንዘብ ሽልማቱ መከፈል ይጀምራል፡፡

በ2011 በወንዶች ከአንደኛ ሊግ እስከ ፕሪምየር ሊግ በሴቶች ደግሞ የፕሪምየር ሊግ እና ሁለተኛ ዲቪዚዮን፣ በተጨማሪም ከ20 ዓመት በታች ወንዶች ፕሪምየር ሊግ ላይ በከፍተኛ ግብ አግቢነት፣ ኮከብ ተጫዋችነት፣ ኮከብ ግብ ጠባቂነት፣ ኮከብ አሰልጣኝነት፣ ምስጉን ዋና እና ረዳት ዳኛ ተብለው በመስከረም ወር ላይ በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል በተዘጋጀ የሽልማት ስነ-ስርአት የገንዘብ እና የዋንጫ ሽልማት መበርከቱ ይታወሳል፡፡ ሆኖም የገንዘብ ሽልማቱን ለተሸላሚዎቹ በወቅቱ ፌድሬሽኑ ከሳምንት በኃላ ሸልማለው ቢልም ያ መሆን ሳይችል ረጅም ወራቶችን አስቆጥሮ ተሸላሚዎቹም ተደጋጋሚ ቅሬታን እያሰሙ መዝለቃቸው ይታወቃል።

ሶከር ኢትዮጵያ ከፌድሬሽኑ ጊዜያዊ የፅህፈት ቤት ኃላፊ እና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ ኮከቦቹ በቀጣይ ቀናት የሽልማት ገንዘባቸውን ይወስዳሉ። “አሁን ተዘጋጅቷል፤ ለሽልማት የሚሆነውም ቼክ ተፈርሟል። የሚቀረው ኮከብ የተባሉት በማንኛውም ሰዓት ቢሮ መጥተው መውሰድ ብቻ ነው። ይህን ያደረግነው ከወቅቱ ጋር በማገናዘብ በዚህ ሰዓት መድረስ አለበት ብለን በማሰብ ነው የ። ስለዚህ ሁሉም መጥቶ መውሰድ ይችላል።” ያሉ ሲሆን በክለብ ደረጃ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ለወጡ ክለቦች ይሰጥ የነበረው ገንዘብ ግን ከዚህ ሽልማት በመቀጠል በቀጣይ የሚፈፀም ይሆናል ሲሉ አያይዘው ተናግረዋል፡፡

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ