በኢትዮጵያ እግርኳስ እስካሁን ምትክ እንዳልተገኘለት የሚነገርለት የዘጠናዎቹ ኮከብ አንጋፋው የመሐል ሜዳው ንጉስ ሙላዓለም ረጋሳ (መካኒኩ) ማነው?
ኳስሜዳ ካፈራቻቸው ፈርጦች አንዱ ነው። በ1989 ነበረ ለዓመታት የነገሰበትን የቅዱስ ጊዮርጊስን ታዳጊ ቡድንን መቀላቀል የቻለው። በወቅቱ የፈረሰኞቹ ቁልፍ ተጫዋቾች ለብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ትራንዚት ለማድረግ ጣልያን ገብተው በመጥፋታቸው ለአንድ ዓመት ቆይታ ብቻ ካደረገበት የታዳጊ ቡድን በፍጥነት ወደ ዋናው ቡድን በ1990 እንዲያድግ አጋጣሚ ሆኖለታል። ሙሉዓለም ረጋሳ እስከ 2002 ድረስ ሜዳ ላይ መስጠት የሚገባውን ነገር እያደረገ ያለ አቋም መዋዥቅ ቅዱስ ጊዮርጊስን ለአስራ አራት ዓመታት በትጋት ማገልገሉ ይታወቃል። ሜዳ ውስጥ ብዙ ዓይን አለው የሚሉት አማካይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ዘጠኝ የፕሪምየር ሊግ፣ ሁለት የጥሎ ማለፍ እና ስድስት የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን አንስቷል። በ1994 በግሉ የፕሪምየር ሊጉ ኮከብ ተጫዋችነት ክብርም አግኝቷል። እስካሁንም በቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ዘንድ በቦታው ምትክ ያልተገኘለት ተጫዋች ይሉታል። “መሐል ሜዳውን ፈትቶ ይገጥመዋል” በሚል “መካኒኩ” የሚል ቅፅል ስም ያወጡለት ሙሉዓለም “ብቻውን ቅዱስ ጊዮርጊስ፤ ብቻውን ብሔራዊ ቡድን ሆኖ ተጫውቷል” ይሉታል። ተጫዋቹ ለ13 ዓመታት ከቆየበት ክለብ ከአሰልጣኝ ሚቾ ጋር በነበረ አለመግባባት ምክንያት በ2002 ነበር የተለያየው።
በመቀጠል ወደ ሰበታ ከተማ አምርቶ ከተጫወተ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መድን በማምራት ከአሳዳጊው አሰልጣኝ አሥራት ኃይሌ ጋር በመሆን ኢትዮጵያ መድን ወደ 2005 ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እንዲያድግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል። ከመድን ቆይታው በኋላ ከሚወደው እግርኳስ ሁለት ፈታኝ ዓመታትን ክለብ አልባ ሆኖ ቢቆይም በብቃቱ የተማመኑት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ለሀዋሳ ከተማ እንዲጫወት አድርገውታል። ከሀዋሳ በመቀጠል ለደቡብ ፖሊስ የተጫወተ ሲሆን ካለፈው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ በስሑል ሽረ እየተጫወተ ይገኛል።
ለ23 ዓመታት በኢትዮጵያ እግርኳስ እንደ ማገልገሉ የሚገባውን ክብር፣ ዕውቅና እና ጥቅም አላገኘም የሚባልለት ሙሉዓለም በ1989 ለታዳጊ ቡድን መጫወት ሲችል ብዙም ሳይቆይ ለዋናው ብሔራዊ ቡድን እስከ 1999 ድረስ በመጫወት ሀገሩን በሚገባ ማገልገል ችሏል። በብሔራዊ ቡድን ቆይታውም በ1994 እና በ1998 ኢትዮጵያ የሴካፋ ዋንጫን ስታነሳ የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች ነበር። የ98 ድል ላይ ቡድኑን በአምበልነት መምራትም ችሏል።
በእግርኳስ ሁሌም የሚደሰትበት ገጠመኝ የ1995 የመጨረሻ ሰዓት ዋንጫ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያነሳበት ወቅት እንደሆነ የሚናገረው ሙሉዓለም በእግርኳስ ህይወቱ ከታዳጊነቱ አንስቶ አሁን እስከሚጫወትበት ዘመን ድረስ በሁሉም ነገር ደስተኛ ቢሆንም በእርሱ የስኬት ዘመን ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ዋንጫ አለማለፏ እንደሚቆጨውም ይናገራል። ” እግርኳስ የቡድን ጨዋታ በመሆኑ አንድ ሰው ምንም ማድረግ አይችልም። በእኔ ወቅት ለአፍሪካ ዋንጫ አለማለፋችን ያስቆጨኛል ።” ብሏል። በሌላ በኩል ደግሞ “በቅዱስ ጊዮርጊስ ረጅም ዓመት በመቆየቱ እንደፈላጭ ቆራጭ አድርገው አስበው የሚያስወሩ ቢኖሩም ይሄን ሰምተው ከሩቅ ሆነው ይፈሩኝ የነበሩ እንደነ ጌቱ ተሾመ፣ ኤፍሬም ዘሩ እና ደብሮም ሀጎስ የመሳሰሉ ተጫዋቾች ቅዱስ ጊዮርጊስ ለመጫወት ሲመጡና ቀርበው ሲመለከቱኝ እንዴ ሙሉዓለም አንተ ፍፁም ዝምተኛ ነህ። ስለ አንተ ሲወራ የሰማነውና ቀርበን የተመለከትነው ምንም የማይገናኝ ነው በማለት ተናግረዋል። እውነት በጊዜ ሂደት ቢገለጥም እኔ የማውቀው ዝምተኛ መሆኔን ነው። ” ሲህ ስለባህርዩ ይናገራል። “በግልፅ የማውቀው ቅፅል ስም ባይኖረኝም ደጋፊዎች በተለያዩ ጊዜያት የሚያወጡልኝ ቅፅል ስሞች ይኖራሉ። መካኒኩ የሚለውም ስም ሆነ ሌሎች ስያሜዎችን አውጥተውልኝ ሊጠሩኝ ይችላሉ። ” ሲል ስለ ቅፅል ስሙ ይናገራል።
ለረጅም ዓመት እግርኳስን እስካሁን ለመጫወቱ ሚስጢሩ “ምንም የተለየ ነገር አድርጌ አይደለም፤ እግርኳስን ስለምወድ ብቻ ይሆናል። ወደ ፊትም አቅሜ እስከፈቀደ ድረስ ጠንክሬ እጫወታለሁ።” የሚለው ሙሉዓለም ከባለቤቱ የሦስት ልጆች (የ7፣ የ5 እና የ3 ዓመት ወንድ ልጆች) አባት ሲሆን ሦስቱም ልጆቹ “ኳስ የሚነካኩ፣ አብረውኝ ሜዳ እየወጡ ልምምድ የሚሰሩ ናቸው.. ወደ ፊት ወይ አንደ አባታቸው የማይችሉ ተጫዋቾች ይሆናሉ (እየሳቀ) ወይም ወደ በሌላ መስክ ይሰማራሉ የሚለውን ገና ልጆች ስለሆኑ ከጊዜ በኃላ የምናየው ነው።” ብሏል።
ለ23 ዓመት በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ የሚገኘው አንጋፋው አማካይ ሙላዓለም ረጋሳ በአሁኑ ወቀት ለሱሑል ሽረ በአስገራሚ ብቃት እየተጫወተ ይገኛል።
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ