የተጫዋቾች ማኀበር ቅሬታ እና ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው ምላሽ

ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው በቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ ” እግርኳስ ተጫዋቾች ከሀገሪቱ ህዝብ ነጥለን ልናያቸው አንችልም መንግስት ከሌለው የለውም። እግርኳስ ተጫዋች ከማንም በላይ አይደለም። መንግስት አምነህ ክለቦችን አምነህ እንደፈለክ የምትዘረከረክ መሆን የለበትም ህዝብ እያለቀሰ ደሞዝ አይጠየቅም” በማለት በተጫዋቾች የደሞዝ ክፍያ ዙርያ ተገቢ ያልሆነ አስተያየት ሰጥተዋል በማለት የኢትዮጵያ ተጫዋቾች ማኀበር ሁለት ገፅ የያዘ የቅሬታ ደብዳቤ ለፌዴሬሽኑ ከሰሞኑ ማስገባቱ ይታወሳል።

በዚህ ቅሬታ ዙርያ አስተያየት እንዲሰጡን የጠየቅናቸው ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው በበኩላቸው ለቀረበባቸው ቅሬታ ተከታዩን ምላሽ ሠጥተዋል። 

” በመጀመርያ እንዲህ ያለ ነገር ከማውራታቸው አስቀድሞ እኔ የተናገርኩትን ሙሉ ለሙሉ አዳምጦ መሆን ይገባል። እንዲሁ በግርድፉ መንገር ተገቢ አይደለም። እኔ ለመገናኛ ብዙሀን ያልኩት ክለቦች ገንዘብ ካላቸው ይክፈሉ። ገንዘብ ከሌላቸው ገንዘብ ከየት ይመጣል ነው ያልኩት። ሁላችንም ደሞዝ ባይኖር ገቢ የምናጣ ከሆነ መንግስት የሚሰጠን ባቄላ ተሰልፈን ከመቀበል እና ያነን ቆርጥመን ከመብላት ውጭ ምንም አማራጭ የለንም። ገንዘብ ከሌለ ምድነው የሚሆነው አልኩ እንጂ አይከፈል አላልኩኝም። ተጫዋቹ ከክለቦች ገንዘብ ካለው ዛሬም ሆነ የዛሬ ዓመት መክፈሉ አይቀርም፤ በተዋዋለው ውል መሠረት ማግኘት ይችላል። ስለዚህ በእኔ ላይ ያቀረቡት አስተያየት በፍፁም ያላልኩት ከእውነት የራቀ ነው። ይህን ማስተካከል አለባቸው። እኔ ሰው አይብላ የምል ሰው አይደለሁም።”

በሁለቱ ወገኖች በኩል የተፈጠረውን አለመግባባት አስመልክቶ የቀረበው የቅሬታ ደብዳቤ ለፌዴሬሽኑ የደረሰው እንደሆነና ጉዳዩን በሂደት ተከታትሎ እንደሚያሳውቅ ሰምተናል።

የማኅበሩ የቅሬታ ደብዳቤ 

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ