አስተያየት | የአንጋፋ አሰልጣኞቻችን የተሰነደ ኗሪ ታሪካቸው የት አለ?

በሀገራችን እግርኳስ የእኛው በሆኑት አንጋፋ አሰልጣኞቻችን የተደረሱ መጻህፍትን ማግኘት እጅጉን አስቸጋሪ ነው፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች  የበርካታ ዓመታት ልምድ ያካበቱ፣ ሰፊ ተመክሮ ያላቸውና አያሌ ውጣ-ውረዶችን ያሳለፉ ቢሆኑም  ይህን የህይወትና የሥራ ሒደታቸውን የሚዳስሱ መጻህፍት ሲጽፉ አይስተዋልም፡፡ አሰልጣኞቻችን- ሲተገብሩ የኖሩትን የአሰለጣጠን መንገዶች፣  ሲከተሏቸው የከረሟቸውን የልምምድ መመሪያዎች፣ የሚመርጧቸውን የተጫዋቾች አመላመል ሥርዓቶች፣ ከብዙኃን መገናኛዎች ጋር የነበሯቸውን ግንኙነቶች፣ በክለብ አመራሮችና ቴክኒክ ኮሚቴዎች የደረሱባቸውን ተግዳሮቶች፣  ከተጫዋቾች-ደጋፊዎችና ባላንጦቻቸው ጋር የገቡባቸዎን እሰጥ-አገባዎች እንዲሁም ሌሎች አሉታዊና አዎንታዊ ገጠመኞቻቸውን በዝርዝር ያሰፈሩባቸው መጻህፍት አልተዉልንም፡፡

በእግርኳሳችን ጥሩ ስራ ሰርተው ያለፉት እንደ ታላቁ ይድነቃቸው ተሰማ፣ መንግስቱ  ወርቁ፣ ሥዩም አባተ፣ ማስተር ቴክኒሻን ሐጎስ ደስታ፣ ረ/ፕሮፌሰር ሲሳይ ዘለቀ፣ ወንድማገኝ ከበደ፣ ገዛኸኝ ማንያዘዋል፣ መኩሪያ አሸብርና ሌሎችም አሰልጣኞች በሙያቸው አንቱታን ያተረፉ ቢሆኑም ሥለ አሰልጣኝነት ጥልቀትና ስፋት ያለው ጽሁፍ አላኖሩልንም፡፡ ኢንስትራክተር ካሳሁን ተካ፣ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው፣ አሥራት ኃይሌ፣ ከማል አህመድ፣ ወርቁ ደርገባና ንጉሴ ገብሬን የመሳሰሉ አሰልጣኞችም በዘመናቸው ለእግርኳሱ እድገት የሚችሉትን ያህል ቢጥሩም እነርሱም  እንዲሁ በፅሑፍ አልያም በተንቀሳቃሽ ምስሎች ለቀጣዩ የአሰልጣኞች ትውልድ ያስረከቡት መማሪያ ስለመኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡

በእርግጥ ስለ እነዚህ ታላላቅና ቀደምት አሰልጣኞች በተለያዩ መንገዶች (ጋዜጦች፣ መጽሄቶች፣ ድረ-ገጾች፣ አብረዋቸው ከሰሩ ሰዎች የቃል ምስክርነት፣…) ብንሰማም ዋነኛው ሙያቸውን በተመለከተ- ስለ ተጫዋቾች አያያዝና አስተዳደር፣ ራሳቸውን ለማሻሻል ስለወሰዷቸው እርምጃዎች፣ ስኬታማ ሆኖ ለመገኘት ስለ ተጋፈጧቸው ችግሮች፣ ስለ ውድቀቶታቸው መንስኤዎችና የእግርኳሱ አማተራዊ የአመራር አወቃቀር ስላደረሰባቸው በደሎችና እንጎልቶች የሚያስተምሩ መጽሃፍት አላሳተሙም፡፡ በእርግጥ እነዚህ አሰልጣኞች በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች፣ በሬዲዮና ቴሌቪዥን የስፖርት ፕሮግራሞች ላይ ረጃጅምና ሰፋፊ ቃለ መጠይቆችን ቢሰጡም እነዚህንም አንድ ላይ ሰንዶ መጽሃፍ የማድረግ ጥረት አልታየም፡፡

ብዙ ሰዎች አሁን ካለው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ደረጃ ይልቅ የቀድሞው እንደሚሻል ይናገራሉ፡፡እንደ’ኔ እምነት የቀድሞውን ማየት ያልቻልንና ያልታደልን በዚህ ዘመን በአሰልጣኝነት ሙያ ውስጥ የምንገኝ አካላት ግን ይህንን ለመቀበል የምንቸገር ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በዚያ ዘመን የነበሩ አሰልጣኞች በፅሁፍ ያስቀመጡልን ማመሳከሪያ የለም፤ የተቀረፁ የስልጠና እና የጨዋታ ቪዲዮዎችን ማግኘትም ያስቸግራል፡፡
ከላይ የጠቀስኳቸውና ሌሎችም አሰልጣኞች ስለ እግርኳሳዊ አስተሳሰባቸው፣ ስለአሰለጣጠን ዘይቤያቸው፣ ስለ ጨዋታ ፍልስፍናቸውና  አጠቃላይ ከባቢያዊ ግንዛቤያቸው በመጽሃፍ መልክ ምንም አላስቀመጡልንም፡፡ የህይወት ታሪካቸውን አልጻፉም፤ አላጻፉምም፡፡ በእነዚህ አሰልጣኞች ስር ከሰለጠኑ ተጫዋቾች ከምንሰማው ውጪ ምንም አይነት ሰነዶችን ማግኘት አልቻልንም ፡፡

ከአሰልጣኝ ሥዩም አባተ ይልቅ ስለ ጣልያናዊው አሪጎ ሳኪ ብዙ እውቀት እና መረጃ ማግኘት ይቀለናል፡፡ በሥዩም ስር ከነበረውና ስለአዝናኝነቱ በሰፊው ከተመሰከረለት ኢትዮጵያ ቡና ቡድን በላይ በአገራችን ስለ ሪኑስ ሚሸልሱ አጨዋወት በቪዲዮም ይሁን በጽሁፍ ብዙ ተብሏል፤ ተነግሯል፡፡

ብዙም የመጻፍ ልምድ በሌለበት የኢትዮጵያ እግርኳስ ከባቢ ውስጥ የጥንቱን ከአሁኑ ለማወዳደር በሁለቱም ዘመን ከነበሩና ካሉ ሰዎች ከመስማት ውጪ ሌላ የምናወዳድርበት ምንም ማንጸሪያ መንገድ የለንም፡፡እግርኳሳችን ከውጤት ባሻገር በጨዋታ ሥልት፣ በአሰለጣጠን ዝመናና በልምምድ መርኃግብርና አይነት አድጎም ይሁን ቁልቁል ወርዶ በድፍረት ለመናገር በጣም አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ አሰልጣኞች ቀድሞም ይሁን በዚህ ዘመን የስልጠናዎቻችንን አካሄድ የመጻፍ፣ የማሰልጠኛ መመሪያዎችን የማዘጋጀት፣ ተጫዋቾችን የማስተዳደርና የቡድን ግንባታ ሒደትን የመምራት እንዲሁም ግላዊ የህይወት ታሪክን በመፃፍ ረገድ በጣም ደካማ ናቸው፡፡ ይህም በቀጣይ ለሚመጡ አሰልጣኞች የሚያስተላልፉት እውቀት እምብዛም እንዲሆን አድርጓል፡፡

ካለፉት ሃያ ዓመታት ወዲህ እግርኳሳችን እንደ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራህቱ፣ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ እና አሰልጣኝ ገብረመድህን ሃይሌን የመሳሰሉ አሰልጣኞች አፍርቷል፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች በተለያየ ጊዜ በአንጻራዊነት ጥሩ ቡድን ሰርተው አሳይተዋል፡፡ ልምዳቸውን፣ ተመክሯቸውንና እውቀታቸውን ግን አብረዋቸው ከሰሩት እና እየሰሩ ካሉት ሰዎች ውጪ ሌሎቻችን በቀላሉ መጋራት አልቻልንም፡፡ ችግሩ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መማማሪያ መጻህፍት እና ዶክመንተሪዎች ካለመዘጋጀታቸው ጋር ይያያዛል፡፡

የዕለት በዕለት የስልጠና ፕሮግራሞችን ጨምሮ እቅዶችን፣ የማሰልጠኛ መመሪያዎች፣ የተጫዋቾች አያያዝና የቡድን አስተዳደር ዘዴዎችን የሚመለከቱ ጽሁፎችን የመፃፍ ልማድ ቢኖረን ምናልባት የአገራችንን እግር ኳስ የበለጠ ለመረዳት አማራጭ ይፈጥርልን ነበር ፡፡

ስለሆነም በዚህ ዘመን በትልቅ ደረጃ በማሰልጠን ላይ ያላችሁ አሰልጣኞች በተለይም እውቀታችሁን በትምህርት፣ በተለያዩ የሙያ ማሻሻያ ስልጠናዎችና ሴሚናሮች ያሳደጋችሁ፣  በርካታ አመታት የማሰልጠን ልምድ ያላችሁ  አሰልጣኞቻችን ተመክሮዎቻችሁንና ልምዶቻችሁን በማሰባሰብ በጥሩ ሁኔታ ጽፋችሁ አልያም አጽፋችሁ እንዲታተም ማድረግ ብትችሉ በብዙ እናተርፋለን፡፡  ከተጫዋቾች፣ ደጋፊዎችና የአስተዳደር ሰዎች ጋር የገጠሟችሁን ችግሮችና እነዚህን ተግዳሮቶች በምን መልኩ እንደፈታችሁ ልምዳችሁን በፅሁፍ ብታስቀምጡልን በደንብ እንማርበታለን፡፡ በተጨማሪም ልምምዶቻችሁን በማስቀረፅ በተለያዩ ማህበራዊ ገጾች ብትለጥፉልን ለቀጣይ ትውልድ እውቀትን በማሸጋገር ረገድ ገንቢ ውርስ ትታችሁ ማለፍ ያስችላችኋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የመፃፍ ልማድ በሌሎች አሰልጣኞችም ዘንድ እንዲሰርጽ በማድረግ አንዱ ከሌላው እንዲማር ሁኔታዎችን ያመቻቻል፡፡


ስለ ፀሐፊው


የአስተያየቱ ፀሐፊ አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ነው፡፡ አሰልጣኙ ባለፉት አስር ዓመታት በበጎ ፍቃድ  ታዳጊዎችን በማሰልጠንና ለበርካታ ክለቦች በማበርከት እውቅና ባተረፈው የአስኮ እግር ኳስ ፕሮጀክት ሲያሰለጥን ቆይቷል ፡፡ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአፍሮ-ፅዮን እግር ኳስ ክለብ ከ17 ዓመት በታች ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ