ዳዊት ፍቃዱ የት ይገኛል?

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለበርካታ ዓመታት ለከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት በብርቱ ተፎካካሪነቱ የምናውቀው ዳዊት ፍቃዱ “አቡቲ” የት ይገኛል?

በ1999 ከአየር ኃይል ጋር የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ ቢያጠናቅቅም በክለቦች ህብረት እና በፌዴሬሽኑ መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ለሀዋሳ ከተማ ዋንጫው ቢሰጥም የኮከብ ተጫዋችነት እና ጎል አግቢነት ሽልማት ሳይሰጥ በመቅረቱ ይህን ክብር ሳያገኝ እንደቀረ ይገኛል። ከሁለት ዓመት የአየር ኃይል ቆይታ በኃላ ኢትዮጵያ ቡናን ተቀላቅሎ በ2002 የጥሎ ማለፍ እና የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር አንስቷል። ዳዊት ፍቃዱ ከ2003 ጀምሮ ለሰባት የውድድር ዘመናት በደደቢት በመቆየት ምርጥ አጥቂ መሆኑን በማሳየት የ2005 የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ከደደቢት ጋር አንስቷል። በተለይ ደደቢት በነበረበት ቆይታ ፍፁም ቅጣት ምት የመምታት እድል አልተሰጠውም እንጂ ይህን ዕድል ቢያገኝ ኖሮ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ የሚያጠናቅቅበት አጋጣሚዎች ነበሩ። በአንድ ጎል ተበልጦ በጌታነህ ከበደ እና በታፈሰ ተስፋዬ የተነጠቀው የኮከብ ጎል አግቢነት ክብር አንዱ ማሳያ ነው። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ቢሆን በተለያዩ ጊዜያት የተጫወተው ዳዊት ከ31 ዓመት በኃላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ በተካፈለበት ቡድን ውስጥ ባይኖርም በማጣርያው እና የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች ላይ ጥሩ አበርክቶ ነበረው።

ስኬታማ ከሆነበት ደደቢት ለቆ በ2010 ሀዋሳን እንደተቀላቀለ በሁለተኛ ሳምንት ወልዲያ ላይ ሐት-ትሪክ ሰርቶ አጀማመሩን ቢያሳምርም በቀሪው የውድድር ዓመት የታሰበውን ያህል ጎሎችን ማስቆጠር ሳይችል ቀርቷል። በተመሳሳይ በ2011 ወልዋሎ ቢያመራም በጉዳት የተፈለገውን አገልግሎት ሳይሰጥ በውድድሩ አጋማሽ ተለያይቷል። ስኬታማ ዓመታትን ካሳለፈበት ደደቢት በኃላ በሀዋሳ ከተማ እና ወልዋሎ በተለያዩ ምክንያቶች የእግርኳስ ህይወቱ ሳይረጋጋ ቆይቷል። ይልቁንም እጁ ላይ ያጋጠመው ጉዳት አቅሙን አውጥቶ እንዳይጠቀም ፈተና ሆኖበት ያለፉትን አንድ ዓመት ከሜዳ ርቋል። ይህን ተከትሎ ሶከር ኢትዮጵያ ዳዊት ፍቃዱ የት ይገኛል ስትል ፈልጋ አግኝታ አናግራዋለች።

” ሀዋሳ በነበርኩበት ወቅት በፍጥነት ስሮጥ ልወድቅ ስል የሜዳው ጠርዝ ፊቴን እንዳይመታኝ ብዬ በእጄ ወደቄ ከበድ ያለ የእጅ ውልቃት ጉዳት አስተናግጄ ነበር። በጊዜው በቂ እረፍት ማድረግ ሲገባኝ ሀዋሳ ከተማ ወሳኝ ጨዋታዎች ስለነበሩት ወደ ሜዳ ስመለስ እጄ ዝም ብሎ እየወለቀ አስቸግሮኝ ነበር። ወልዋሎም እያለውም በተመሳሳይ ይህ ጉዳት ያስቸግረኝ ነበር። በቂ ህክምና ማድረግ አለብኝ ብዬ በራሴ ወጪ ቀዶ ጥገና አድርጌ ከህመሜም በሚገባ አገግሜ በተለይ ይህን ስድስት ወር በቂ የሆነ ዝግጅት ሳደርግ ቆይቻለው። ሆኖም ዘንድሮ የውድድሩ አጋማሽ ላይ በአንዱ ክለብ ወደ ሊጉ እመለሳለው ስል በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ውድድሮች ተቋርጠዋል። ያው ፈጣሪ ይህን በሽታ ያርቅልን እንጂ በቀጣይ ዓመት ልምምዴን በጥሩ ሁኔታ ሰርቼ ወደ ቀድሞ አቋሜ እመለሳለው።” ብሏል።

ዳዊት ፍቃዱ በ2005 ከጌታነህ ከበደ በአንድ ጎል አንሶ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሳይሆን መቅረቱ የሚታወስ ሲሆን ወቅቱን በማስታወስ በ21 ጎሎች በጋራ ሽልማት መውሰድ ይገባቸው እንደነበር ገልጿል። “በአንድ ወቅት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ደደቢት ከአዳማ ከተማ ጋር ሲጫወቱ 7-1 ስናሸንፍ ጌታነሀ ከበደ ጎል አላገባም ነበር። የዛን ጊዜ በኃይሉ ቱሳ ይመስለኛል ያሻማውን ኳስ የአዳማው ዳንኤል የሻው እና ጌታነህ እኩል እየሮጡ ዳንኤል ራሱ ላይ ያገባል። ቪዲዮ ሁሉ ልታገኙ ትችላላቹ የበለጠ ለማረጋገጥ። ሆኖም ጌታነህ ከበደ እንዳገባ ሆኖ ተመዝግቦ በዛች ጎል እርሱ 22 ሆኖ ከእኔ በአንድ ጎል በልጦኝ የጨረሰበት መንገድ ቢታወቅልኝ ደስ ይለኛል።” ብሏል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ