የሴት ተጫዋቾች የደሞዝ ክፍያ በወቅቱ አለመከፈል እየተቸገሩ ነው

ክለቦች ለሴት ተጫዋቾች መክፈል የነበረባቸውን የወር ደመወዝ በአግባቡ እየፈፀሙ ባለመሆኑ በተጫዋቾቹ ዘንድ ቅሬታን አስነስቷል፡፡

በ2012 በኢትዮጵያ በሁለቱም ፆታ ሲደረጉ የነበሩ የእግር ኳስ የሊግ ውድድሮች ከወራት በፊት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የተነሳ ከቆሙ በኃላ በቅርቡ ደግሞ በይፋ ሙሉ ለሙሉ መሰረዛቸው ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ውድድሮቹ ቢሰረዙም ክለቦች ከተጫዋቾች ጋር በገቡት ውል መሠረት ወርሀዊ ክፍያቸውን እንዲከፍሉ ማሰሰቡ የሚታወቅ ቢሆንም ክለቦች ተግባራዊ ከማድረግ ይልቅ እጃቸውን ሰብስበው ቁጭ ብለዋል፡፡ አንዳንድ ክለቦች ይህን ጉዳይ ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በአግባቡ ቢከፍሉም አመዛኞቹ ክለቦች ግን ከማስፈፀም ይልቅ በራቸውን መዝጋትን አማራጭ አድርገዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ እና በሁለተኛ ዲቪዚዮን ላይ ያሉ ክለቦች በወቅቱ ለተጫዋቾቻቸው ክፍያን ሳይፈፅሙ ረጅም ወራትን እያስቆጠሩ በመምጣታቸው በርካታ ሴት ተጫዋቾች ቅሬታን ለፌዴሬሽኑ ማሰማት ጀምረዋል፡፡ ተጫዋቾቹ እንዳሉት ከሆነ “ደመወዝ ሳይከፈለን ረጅም ጊዜን አስቆጥረናል፡፡ በእጃችን ገንዘብ የለም፡፡ ክለቦቻችንን በተደጋጋሚ ክፈሉን ብንልም ለኛ ትኩረት ከመስጠት ይልቅ ለወንድ ቡድኖቻቸው ብቻ ትኩረትን ይሰጣሉ፡፡ እኛም ተጫዋች ነን፤ ይህን ችግራችንን ፌድሬሽኑ ተገንዝቦ ደመወዛችንን ሊያሰጠን ይገባል፡፡” ሲሉ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ አንድ አንድ ተጫዋቾች እንዳሉት ከሆነ የኮሮና ቫይረስ ከመከሰቱ ቀደም ብሎም ደመወዝ አልተከፈለንም ያሉ ሲሆን “ከሁለት ወር እስከ ሰባት ወር ድረስ ክለቦች ደመወዛችንን በአግባቡ አልከፈለንም፡፡” ብለዋል፡፡ ከአምስት የፕሪምየር ሊግ እና የሁለተኛ ዲቪዚዮን ክለቦች ውጪ ሌሎቹ ክለቦች በአግባቡ ለተጫዋቾቻቸው ክፍያን እየፈፀሙ እንዳልሆነም ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡

ፌዴሬሽኑ በቀጣይ የሴት ተጫዋቾችን ጉዳይ በተጨማሪም ከወንድ ተጫዋቾች ጋር በተገናኘ የሚነሳው ቅሬታን በምን መልኩ ለመፍታት አስቧል በሚሉት ዙሪያ ከፌዴሬሽኑ ተወካይ በቀጣይ ምላሽ ይዘን እንመለሳለን፡፡


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ