በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ተጫዋቾች ምርጫ ታሪክ የመጀመርያውና ብቸኛው ግብ ጠባቂ ሆኖ ተሸለመው ጀማል ጣሰው የትውስታ አምዳችን የዛሬ እንግዳ ነው።
ኢትዮጵያ ከሦስት አስርት ዓመታት በኋላ ወደ ትልቁ አፍሪካ ዋንጫ መድረክ ስትመለስ የግብ ጠባቂነት ቦታውን በአግባቡ የተወጣው ጀማል ጣሰው ከ1997- 2000 በአሳዳጊ ክለቡ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከታችኛው እስከ ዋናው ቡድን መጫወት ችሏል። ሀዋሳ፣ ደደቢት፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ መከላከያ፣ ጅማ አባ ቡና፣ ድሬዳዋ ከተማ ተጫውቶም አሳልፏል። በግብ ጠባቂነት ህይወቱ በተለያዮ ጊዜያት ከበድ ያለ ጉዳት የማያጣው ይህ ምርጥ ግብ ጠባቂ በ2002 ለደደቢት እየተጫወተ ባለበት ወቅት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ተጫዋቾች ምርጫ ታሪክ የመጀመርያውና ብቸኛው ግብ ጠባቂ በመሆን ችሏል። ይህን ልዩ ክስተት ወደ ኋላ 10 ዓመት መልሶ እንዲያስታውሰን በትውስታ አምዳችን የዛሬ እንግዳች ጀማልጣሰው ይሄን ይናገራል።
“በጣም የሚገርም ጊዜ ነው። በግብ ጠባቂነት ህይወቴ መቼም የማረሳው ትልቅ ትውስታዬ ነው። በጊዜው ይህ ሽልማት አገኛለው ብዬ እስከ መጨረሻው ስም እስኪጠራ አልጠበኩም ነበር። እኔ ያሰብኩት አሁን እንደሚደረገው የግብጠባቂዎች ኮከብነት ሽልማት ነበር፤ በመጨረሻም እኔ በመሆኔ ደስ ብሎኛል። በወቅቱ እንደ ዛሬ የውጭ ግብጠባቂዎች ከሁለት የማይበልጡበት፣ ኢትዮጵያውያን ግብ ጠባቂዎች በከፍተኛ ብቃት እና በራስ መተማመን ምርጥ አቅማቸውን አውጥተው የሚጠቀሙበት ጊዜ ነበር። እኔ በወቅቱ ባልሸለም እንኳን ሌሎች ግብ ጠባቂዎች ይህን ክብር ያገኙ ነበር። ያን ጊዜ ወደ ኃላ ሳስታውሰው ራሴን ከስፖርት ቤተሰቡ ጋር ያስተዋወኩበት፣ ያለኝን አቅም ሁሉ አውጥቼ ጥሩ አቋሜን ያሳየሁበት አሪፍ ጊዜ ነበር። በወቅቱም ደደቢት የነበሩት የቡድኑ አባላት በሙሉ ምርጥ የነበሩበት ጊዜ ነው። ይህን ክብር ያገኘሁበትን ቀን መቼም አረሳውም በዛ ላይ እኔ ብቸኛው ግብጠባቂ ነኝ ይህ በጣም አስደሳች ነው። ከዛ በኃላ ባለው የግብ ጠባቂነት ህይወቴ ይህን ክብር ማስቀጠል ብችል በጣም ደስ ይለኝ ነበር። ግን በተለያዩ ሁኔታዎች አልተሳካም። አሁን ለምሳሌ በዚህ ዘመን ኢትዮጵያዊ ግብ ጠባቂ በየዓመቱ በወጥ የሆነ አቋም አትመለከትም፤ ወጣ ገባ ነው። አንድ ጨዋታ ላይ ጥሩ ይሆንና በቀጣይ በድጋሚ አትመለከተውም። ምክንያቱም የውጭ ሀገር ግብ ጠባቂ በዝቷል። እንዲሁም ኢትዮጵያዊ ግብ ጠባቂ ላይ ጫና በዝቷል። በሊጉ አንድ በረኛ ቋሚ ሆኖ ገብቶ ከሆነ የገባው ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ግብ ጠባቂ ነው። በረኛው አንድ ስህተት ከሰራ በሙሉ ኢትዮጵያዊ በረኛ ተሳሳተ ተብሎ በጅምላ ይወቀጣል። ይህ ደግሞ ግብ ጠባቂዎች ላይ በራስ መተማመን እንዳይኖር አድርጓል። በዛን ጊዜ ግን ብዙም ጫና ያልነበረ በመሆኑ ስህተትህን እያረምክ ትሄዳለህ በራስ መተማመንህም እየጨመረ ይሄዳል። ያው በዛን ጊዜ በዙርያዬ የነበሩት አሰልጣኞች ውበቱ አባተ የነበረ በመሆኑ በሚሰጡኝ ምክር በራስ መተማመኔ ጨምሮ ስለነበር ይመስለኛል እኔን እዚህ ጫፍ ላይ አድርሶኝ ይህን የመጀመርያ ግብ ጠባቂ ሆኜ ኮከብ ተጫዋች የሚለውን ክብር ያገኘሁት። አሁንም እንደ ከዚህ ቀደሙ አሁን ላሉ ግብጠባቂዎች ትኩረት ቢደረግ ደስ ይለኛል።”
ያለፉትን ሁለት ዓመታት ለፋሲል ከነማ እየተጫወተ የሚገኘው ጀማል ጣሰው የጉዳት ሁኔታ ካላስቸገረው በቀር እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም እያገለገለ ይገኛል።
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ