“የዘመናችን ከዋክብት ገፅ” ከሱራፌል ዳኛቸው ጋር…

በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ውድድሮች መሰረዛቸውን ተከትሎ የዘመኑ የእግርኳሳችን ኮከቦች ጋር ወቅቱን በምን ሁኔታ እያሳለፉ እንደሆነ ከአዝናኝ ጨዋታዎች ጋር በዚህ አምዳችን ይዘን ቀርበናል።

በዚህ አራት ዓመት ውስጥ በእግርኳሱ ጎልተው ከወጡ ስኬታማ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው። በአዳማ ከተማ ከታዳጊ እስከ ዋናው ቡድን መጫወት የቻለው አማካይ ሱራፌል ያለፉትን ሁለት ዓመታት በፋሲል ከነማ ቆይታ እያደረገ ይገኛል። በ2011 የኢትዮጵያ ጥሎ ዋንጫን ከፋሲል ከነማ ጋር ከማንሳቱ ባሻገር በግሉ የውድድር ዓመቱ ኮለብ ተጫዋች በመሆን ተመርጧል። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በወጣት በኦሊምፒክ እና ከቅርብ ወራት በፊት ደግሞ በቦታው የመጀመርያ ተመራጭ በመሆን ዋሊያዎቹን እያገለገለ ይገኛል። ሊጉ በኮሮና ምክንያት በመቋረጡ ጊዜውን በምንሁኔታ እያሳለፈ እንደሚገኝ እና ሌሎች ጥያቄዎችን ዛሬ የዘመኑ ኮከቦች ገፅ በጀመርነው አምዳችን ሱራፌል ዳኛቸውን እንግዳ አድርገናል።

“ልጄ አብራኝ ባትሆን ኖሮ…”

“ውድድሩ በመቋረጡ ያለውን አብዛኛውን ጊዜ ቤት በመሆን አሳልፋለው። ከሴት ልጄ ጋር ነው ብዙውን ጊዜ የማሳልፈው። በዚህ ሰዓት እርሷ አብራኝ ባትሆን ኖሮ ጊዜው ለእኔ ከባድ ይሆን ነበር። ለልጄ ጥሩ ፍቅር እየሰጠሁ እኔም ደስታ እያገኘሁ ነው። ”

“አንድ ጠርሙስ ሳኒታይዘር ሳልጨርስ አልቀርም…”

“ሁሌም በማለዳ ብቻዬን በመሆን ልምምዴን እየሰራሁ ነው። ለራሴም ለቤተሰቤም ለሴት ልጄም ስል በጣም ነው የምጠነቀቀው። ራሴን ከበሽታው ለመጠበቅ በቂ ጥንቃቄ አደርጋለው። እስካሁን ከውሃ መታጠብ ውጭ ለጥንቃቄ ስል አንድ ጠርሙስ ሳኒታይዘር ሳልጨርስ አልቀርም (እየሳቀ)። ”

 

“ኳስ ተጫዋች ባልሆን … “

” የባጃጅ ሹፌር እሆን ነበር። ምክንያቱም ቤተሰቦቼ እግርኳስ ተጫዋች እንድሆን አይፈልጉም ነበር። ሆኖም በነበረኝ ከፍተኛ የመጫወት ፍላጎት ዛሬ እዚህ ደርሻለሁ።”

“ከዳዊት ጋር…”

“ዳዊት እስጢፋኖስ እግርኳስን አቅልሎ እየተዝናና ስለሚጫወት ከእርሱ አጠገብ ሆኜ ብጫወት ደስ ይለኛል።”

“የሚያዝናኑኝ ተጫዋቾች…”

” ሽመክት ጉግሳ እና ጀማል ጣሰው አጠገብህ ከሆኑ አፍህ አይከደንም፤ በጣም የሚያዝናኑኝ ተጫዋቾች ናቸው። ከእግርኳስ ተጫዋቾች ውጭ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ የሆነ ያሬድ የሚባል የሚገርም ቀልደኛ ልጅ አለ። ”

” በህልሜ ቀድሜ ተጫወትኩ…”

” በ2008 ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ውስጥ እያለሁ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከሶማሊያ ጋር በነበረው ግጥሚያ ለመጫወት ከነበረኝ ፍላጎት የተነሳ ከጨዋታው አስቀድሞ በህልሜ ጨዋታውን ተጫውቼ አድሬ ሜዳ ገብቼ እንዴት ልጫወት፤ በጣም ነው የተቸገርኩት። ከዚያን ቀን ወዲህ እንዲህ ያለ ነገር አጋጥሞኝ አያውቅም። ”

” የመጀመርያ ጎሌ…”

” የፕሪምየር ሊግ የመጀመርያ ጎሌ አዳማ ከተማ እያለሁ በ2009 ወላይታ ድቻ ላይ ያስቆጠርኩት ነው። በብሔራዊ ቡድን ደግሞ በቅርቡ ኮትዲቫር ላይ ያስቆጠርኩት ጎል የመጀመርያዬ ነው። ይህች ጎል ለእኔ ታሪካዊ ጎል ናት። ምክንያቱም የአፍሪካ ትልቅ ቡድን ላይ ጎል በማስቆጠሬ፣ የልጄ ማስታወሻ በመሆኗ እና የመጀመርያ ጎሌ በመሆኗ ነው። ”

“ወደ ውጪ…”

“ከኢትዮጵያ ውጭ ለመጫወት የምችልበት ዕድሎች ይኖራሉ እስቲ ወደ ፊት የምናየው ይሆናል። ”

“በመጨረሻም…”

ማስተላለፍ የምፈልገው ነገር ይህ አስከፊ ወረርሺኝ አልፎ ነገ የተሻለ ነገር ይመጣል። ወደ እግርኳሱም እንመለሳለን። ሆኖም እስከዛ ራሳችን እና ቤተሰባችንን ለመጠበቅ ሲባል ጥንቃቄ እናድርግ፤ ከህክምና ማለሙያዎች የሚተላለፉ መልክትን እናክብር፤ መዘናጋቶች አሉና ብዙ ዋጋ እንዳያስከፍለን ጥንቃቄ እናድርግ እላለሁ።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ