ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ​ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 5ኛ ሳምንት በመጨረሻ ቀን ውሎው ከሚያስተናግዳቸው ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ የሚያገናኘው ጨዋታ ተጠቃሽ ነው። ሁለቱ ቡድኖች በሚገናኙባቸው ወቅቶች ከሚኖረው ጠንካራ ፉክክር ተነስተን ይህን ጨዋታ ትኩረት ሰጥተነዋል።


ቦታ – አዲስ አበባ ስታድየም

ቀን – ሰኞ ህዳር 25 2010

ሰዐት- 09፡00

ዳኞች- ዋና ዳኛ ፡ እያሱ ፈንቴ (ፌደራል)

ረዳት ዳኞች- ሙስጠፋ መኩ (ፌደራል) እና ሲራጅ ኑርበርጋ (ፌደራል)


የቅርብ ጊዜ ውጤቶች (ከቅርብ ወደ ሩቅ)

ቅዱስ ጊዮርጊስ | አሸአቻ

ኢትዮ ኤሌክትሪክ | ተሸ  አሸ  አቻ


የኢትዮ ኤሌክትሪክ ተከታታይ አመታት ደካማ ውጤት እና በጊዜ ሂደት ከትልቅ ክለብነት ደረጃ መውረድ ሰዎች ለዚህ ጨዋታ ያላቸውን ግምት ዝቅ እንዲል የሚያደርግ ቢሆንም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በሚደረጉ ጨዋታዎች በሜዳ ላይ የሚታየው ፉክክር በሁለቱ ቡድኖች መሀከል የሚደረገውን ጨዋታ እንዲጠበቅ የሚያደርገው ነው። የተሻለ አጀማመርን በማሳየት ከሁለቱ የመጀመሪያ ጨዋታዎች አራት ነጥቦችን ሰብስቦ የነበረው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በወልዋሎ ዓ.ዩ የደረሰበት ሽንፈት ሊጉን ከመምራት አግዶት ወደ 11ኛ ደረጃ ወርዷል። ሻምፒዮኖቹ ከመቐለ ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋሩ በኃላ ይርጋለም ላይ በሲዳማ ቡና የጨዋታ ብልጫ ቢወሰድባቸውም ሶስት ነጥብ ይዘው ከመመለስ ግን አልተቆጠቡም። ነገ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ የሚያደርገው ጨዋታም ቡድኑን ወደ ሰንጠረዡ አናት የመጠጋት ዕድልን ይፈጥርለታል።


በጨዋታው ምን ይጠበቃል ?

የዘንድሮው አመት የኢትዮ ኤሌክትሪክ የማጥቃት ዕቅድ በአዲስ ፈራሚዎቹ አልሀሰን ካሉሻ እና ዲዲዬ ለብሪ ዙሪያ የሚያጠነጥን ይመስላል። እስካሁን ቡድኑ ያስቆጠራቸው ሁሉም ጎሎች ከሁለቱ ተጨዋቾች የተገኙ ነበሩ። እንደ ቡድን በሶስት ጨዋታዎች አራት ግቦችን ማስቆጠር ከሊጉ ደረጃ አንፃር መልካም የሚባል ቢሆንም። በቡድኑ በሁለቱ ተጨዋቾች ጥምረት ላይ ጥገኛ መሆኑ አሉታዊ ጎን ይኖረዋል። በወልዋሎው ሽንፈት ላይ የታየው የቡድኑ የአማካይ ክፍል መበታተን ደግሞ በቀጣይ ጉዞው ላይ ጥያቄን የሚያጭር ሆኗል። ቡድኑ ግቦችን ለማግኘት በሚመፈልግበት ወቅት በሜዳው ስፋት የሚያጣምራቸው ሶስት አጥቂዎች በተለይም ከመስመር የሚነሱት ተጨዋቾች ከጨዋታ ባህሪያቸው አንፃር በቡድኑ የአማካይ ክፍል እንቅስቃሴ ላይ የሚኖራቸው ደካማ ተሳትፎ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በአዲስ አበባ ዋንጫ ላይ የነበረውን የአማካይ ክፍል ጥልቀት ሲያሳጣው ታይቷል። 

አዲስ አይነት መልክ እየተላበሰ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሙሉ ለሙሉ ተሰርቶ ያለቀ አይመስልም። የአሰልጣኝ ቫስ ፒኒቶ ኳስን ከኋላ መስርቶ የመጫወት አካሄድ የሚፈልገውን መናበብ ለማምጣት ጊዜ የሚወስድ ይመስላል። ቢሆንም በቡድኑ ለአመታት የዘለቀው የማሸነፍ ስነልቦና ይህን ክፍተቱን ለመሙላት እያገዘው ይገኛል። በመቐለው ጨዋታ በመጨረሻ ሰዐት ጎል ማስቆጠሩ እና በሲዳማው ጨዋታ የጨዋታ ብልጫ ተወስዶበትም ሶስት ነጥብ ማሳካት መቻሉ ይህንን በደንብ ያሳያሉ። ይህ የቡድኑ ጠንካራ ጎን ቡድኑ በአጨዋወት ለውጥ ውስጥ ቢሆንም እንኳን ከውጤት እንዳይርቅ ትልቅ እገዛ ይኖረዋል። ሆኖም እስካሁን ባለው ሁኔታ የቡድኑ አስፈሪነት በደንብ የሚታየው ቀጥተኛ ኳሶች በሚጣሉበት ወቅት እና ቡድኑ የቀደመ አጨዋወቱን በሚተገብርባቸው የጨዋታ ወቅቶች ላይ ነው።

ከሁለቱ ቡድኖች ወቅታዊ የቡድን ቅርፅ መስረት ካሉሻ አልሀሰን እና ዲዲዬ ለብሪ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮች ጋር እንዲሁም የሻምፒዮኖቹ አማካይ አብዱልከሪሚ ኒኪማ ከሄኖክ ካሳሁን ጋር የሚገናኙባቸው የጨዋታ እንቅስቃሴዎች በጨዋታው ወሳኝ እንደሚሆኑ ይገመታል። ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮ ኤሌክትሪክ ይዞት እንደሚገባው የጨዋታ ስትራቴጂ ቢወሰንም የጊዮርጊስ የአማካይ ክፍል በኳስ ቁጥጥር ላይ ተመስርቶ ክፍተቶችን ለማግኘት የሚያደርገው ጥረት ውጤታማነትም በጨዋታው ተጠባቂ ይሄናል።


የቡድን ዜና

ቅዱስ ጊዮርጊስ አበባው ቡጣቆን እና አቡበከር ሳኒን ብሔራዊ ቡድን ምርጫ እንዲሁም ባሳለፍነው ሳምንት ለህክምና ወደ ህንድ ያቀናውን ናትናኤል ዘለቀን ጨምሮ  ሳላዲን ሰይድ እና ታደለ መንገሻን በጉዳት ምክንያት የማይጠቀም ይሆናል። በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩልም ግርማ በቀለ ለብሔራዊ ቡድን የተጠራ ሲሆን አዲስ ነጋሽ በቅጣት እንዲሁም ግብ ጠባቂው ሱሊማን አቡ በጉዳት ጨዋታው ያመልጣቸዋል። 


ምን ተባለ ?

ም/አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

” በሊጉ በየሳምንቱ ከሚጠብቁን ጨዋታዎች መሀከል አንዱ ነው። እኛ ለሻምፒዮንነት ነው የምንጫወተው። ለዚህም እያንዳንዱን ጨዋታ ማሸነፍ እንፈልጋለን። ሦስት ነጥብን ነው የምንፈልገው እና ሁሉም ጨዋታዎች ለኛ እኩል ዋጋ አላቸው። አብዛኞቹ ቡድኖች ጊዮርጊስን ተከላክለው እኩል ለመውጣት ነው ሜዳ የሚገቡት። የጥንቃቄ ጨዋታን ይዘው ነው የሚቀርቡት። ቢሆንም ይህ ለኛም ሆነ ለተጨዋቾቻችን አዲስ አይደለም። በርግጥ ጨዋታውን የሚወስነው በሜዳ ላይ የሚኖረው እንቅስቃሴ ነው። ነገር ግን እንዲህ አይነት ነገር እንደሚገጥመን ቀድመን ነው የምናስበው። 

” ሁሌም አዲስ አሰልጣኝ ሲመጣ ከስልጠና ጋር የተያያዘ ብዙ አዲስ ነገር ይኖራል። ተጨዋቾችም ነገሮችን እንደ አዲስ ነው የሚማሩት። ይህ ደሞ ጊዜ ይፈልጋል። አሰልጣኙም በአንድ እና ሁለት ወር ውስጥ ሚፈልገውን ነገር ይሰራል ማለት አይቻልም። ከሱፐር ካፑ በኃላ በብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች እና በጉዳት ምክንያት ሙሉ ቡድናችንን ማግኘት አልቻልንም። በዚህ አንድ ወር ውስጥ እንኳን ያደረግነው ሁለት ጨዋታ ብቻ ነው። ይህ ደግሞ ተጨዋቾቻችንን ከጨዋታ ቅኝት አስወጥቷቸዋል። የቡድን ግንባታው ሂደት ላይም ተፅዕኖ አሳድሯል። ከነዚህ ነገሮች ጋር እየታገልን ቡድኑን ለመስራት እየሞከርን ነው። ”


አሰልጣኝ ብርሀኑ ባዩ – ኢትዮ ኤሌክትሪክ

“በዘንድሮው ውድድር አራተኛ ጨዋታችን ነው። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እያለን ማለት ነው። በየጨዋታው ውጤት ይዘን ለመውጣት ወደ ሜዳ  እየገባን ነው። ለነገውም ጨዋታ በዚሁ መልኩ ተዘጋጅተናል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በጣም ጠንካራ ቡድን እንደሆነ እናውቃለን። ዞሮ ዞሮ እኛም ጠንክረን ተጫውተን ውጤት ይዘን ለመውጣት አስበናል። ”

” ቡድኖች ከሜዳቸው ውጪ ውጤት ይዘው ሲመጡ በራሳቸው ላይ የሚጨምሩት ነገር ይኖራል። እና የሳምንቱ ሽንፈት ስነልቦና ጋር የተያያዘ ይመስለኛል። እግር ኳስ እንደዚህ ነው። አንዳንዴ ቡድኖች ከተጠበቀው ውጪ ሆነው ይገኛሉ። ያ ነገር አሁን አልፏል። ነገም በሲቲ ካፑ ላይ የነበረንን አይነት ጥንካሬ ይዘን ወደ ሜዳ እንገባለን።”


ግምታዊ አሰላለፍ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-3-3)

ሮበርት ኦዶንካራ

አብዱልከሪም መሀመድ – ሳላዲን ባርጌቾ – ምንተስኖት አዳነ – መሀሪ መና

ጋዲሳ መብራቴ – ሙሉአለም መስፍን – አብዱልከሪም ኒኪማ

በሀይሉ አሰፋ – አሜ መሀመድ – ኢብራሂማ ፎፋና


ኢትዮ ኤሌክትሪክ (4-3-3)

ዮሀንስ በዛብህ

አወት ገ/ሚካኤል  – ሲሴይ ሀሰን – ተስፋዬ መላኩ – ዘካርያስ ቱጂ

ጥላሁን ወልዴ – ኄኖክ ካሳሁን – በኃይሉ ተሻገር

ካሉሻ አልሀሰን – ዲዲዬ ለብሪ – ኃይሌ እሸቱ                

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *