ስለ ደብሮም ሐጎስ ሊያውቋቸው የሚገቡ እውነታዎች

ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ማቀበል የእርሱ መለያዎች የሆኑት የዘጠናዎቹ ኮከብ ደብሮም ኃጎስ ማን ነው?

የአንጋፋው የኢትዮጵያ እግርኳስ ባለውለታ የማስተር ቴክኒሻን አሰልጣኝ ሐጎስ ደስታ ልጅ ነው። ትውልድ እና እድገቱ አዲስ አበባ ልዩ ስሙ ቀበና “ቤሌር ሜዳ” ነው። አመለሸጋው የመስመር ተጫዋች ተወልዶ ባደገበት አካባቢ በሚገኘው ሜዳ እግርኳስን ሲጫወት አድጓል። ደብሮም የመጀመርያው ክለቡ በአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ሥር ይሳተፍ የነበረው ቀበና ናታ የተሰኘ ቡድን ነበር። የግንባር ኳስ አጠቃቀሙ ጥሩ እንደሆነ የሚታወቀው ደብሮም በመቀጠል ከኦሜድላ በኃላም በአሰልጣኝ ሥዩም አባተ በሚሰለጥነው አየር መንገድ በማምራት ከተጫወተ በኃላ ለጉና ንግድ የተጫወተ ሲሆን በመቀጠል ከፍተኛ ስም እና ዝና ወዳገኘባቸው የሀገሪቱ ታላላቅ ክለቦች ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በማምራት መጫወት ችሏል።

ጎል የማግባት አቅም ቢኖረውም በወቅቱ ለነበሩ አጥቂዎች ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ የማቀበል ችሎታው ከፍተኛ እንደሆነ አብረውት የተጫወቱት ሁሉ ይመሰክሩለታል። በድጋሚ 1998 እና 99 ተመልሶ እግርኳስ እስካቆመበት ጊዜ ድረስ ለኢትዮጵያ ቡና መጫወት የቻለው ደብሮም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ፣ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ደግሞ የጥሎ ማለፍ ዋንጫን ማንሳት ችሏል። ይህ ፈጣን የመስመር ተጫዋች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሁሉም እድሜ እርከን በመጫወትም ይታወቃል። በኦሊምፒክ ማጣርያ ወደ አቴንስ ሊያመራ ከጫፍ በደረሰው ብሔራዊ ቡድን ውስጥ አንበል በመሆን ከማገልገሉ ባሻገር ለተከታታይ ዓመታት በ1997 እና 98 በሀገር ውስጥ እና በውጭ ኢትዮጵያ የሴካፋ ዋንጫን ስታነሳ የነበረው ሚና ከፍተኛ ነበር። ጉና ንግድ በ1991 በታሪክ የመጀመርያው የአፍሪካ የክለቦች ተሳትፎ እንዲያሳካ ወሳኝ ሚና መጫወት ችሏል። ያመነበትን ነገር ለመወሰን ወደ ኃላ የማይለው ደብሮም ብዙ መጫወት የሚችልበት ወቅት በ1999 ኳስ ማቆሙ ለብዙዎች ያልተጠበቀ ነበር።

” እግርኳስ ትጫወታለህ በሆነ ወቅት ታቆመዋለህ። ካለፈ በኃላ ይሄን ነገር ባደርግ ባላደርግ ብለህ ትቆጫለህ። በእኔ በኩል በእግርኳስ ተጫዋችነት ዘመኔ ያመንኩበትን ሁሉ በማድረጌ ይህን አላደረኩም ብዬ የምፀፀትበት ምንም ነገር የለም። በጣም ደስተኛ ሆኜ ነው የእግርኳስ ተጫዋችነት ዘመኔን ያጠናቀኩት። በተቻለኝ አቅም ያለኝን በራስ መተማመን ተጠቅሜ የምችለውን አድርጌ አልፌያለው። አሁን ያለውም ትውልድ በኃላ የማይፀፅተውን ነገር አድርጎ ማለፍ እንዳለበት መልዕክት አስተላልፋለው። በጣም የሚቆጨኝ ወደ አቴንስ ኦሊምፒክ የማለፍ ከፍተኛ እድል ኖሮን በራሳችን፣ የፌዴሬሽን ሰዎች የአመራር ክፍተት እና አለመግባባት ይህን ትልቅ ታሪክ አለማሳካቴ በጣም የምቆጭበት ነው። በአሰልጣኝነት ህይወት የመቀጠል ከፍተኛ ፍላጎት አለኝ፤ ወደ ፊት በአዕምሮም በአካልም በደንብ ተዘጋጅቼ እመለሳለው።

” አባቴ ሠርቶ ባለፈው ነገር እጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ። ስለ እርሱ ከእኔ ይልቅ ከእርሱ ጋር ሠርተው ያለፉ ቢመሰክሩለት ደሰተኛ ነኝ። አሰልጣኝ በነበረበት ዘመን የሚገባውን ሁሉ ሠርቶ አልፏል። ለእግርኳስ የነበረው ስሜት እጅግ ከፍተኛ ነው። ለሰዎች የነበረው ፍቅር በጣም ከፍተኛ የነበረ ዘመኑን ሙሉ ለኢትዮጵያ እግርኳስ የሰጠ፣ የለፋ ሰው ነው። የሰራውን መልካም ስራ በማሰብ ዛሬ ስሙን በበጎ ሲያነሱ ማየት ለእኔ ትልቅ እርካታ ይሰጣል። አባቴ ሠርቶ ባለፈው ነገር በጣም ደስተኛ ነኝ። እኔንም ወደ እዚህ ሙያ እንድገባ ያደረገኝ እርሱ ነው። የእርሱንም ሙያ ማስቀጠል እፈልጋለው። ወደ ፊትም እርሱ የሚወሳበት ብዙ ነገር ማዘጋጀት እፈልጋለው። አሰልጣኞችን በተመለከተ መናገር የምፈልገው፤ ሐጎስ ብቻ ሳይሆን ከእርሱ ጋር የነበሩ ቀደምት ታላላቅ አሰልጣኞች የልፋታቸውን ያህል እውቅና ሳያገኙ ሲቀር ትንሽ ቅር ይለኛል። እና መንግስቱ ወርቁ፣ ካሳሁን ተካ፣ ወርቁ ደርገባ፣ አስራት ኃይሌ፣ ሥዩም አባተ፣ ገዛኸኝ ማንያዘዋል ሌሎችም ስማቸውን ያልጠራኃቸው አሰልጣኞች እነዚህ ሰዎች ምንም አይነት ጥቅም ሳያገኙ እድሜ ዘመናቸውን ለኢትዮጵያ እግርኳስ የለፉ ሰዎች ናቸው። ወንግስቱ ወርቁ ለልጁ ‘እኔ የማወርስህ ገንዘብ ወይም ወረረቅ የለም፤ በእርግጠኝነት የምነግርህ ግን የሌባ ልጅ አትባልም’ ብሎት ነበር። ይሄን ያህል ነበር በቅንነት ለሙያቸው ያላቸው ታማኝነት ነው። ዛሬ ማነው ይህንን አባባል በሙሉ ልብ የሚናገር አሰልጣኝ? እንዲህ ያሉ ሰዎች የሚገባውን ክብር ባለማግኘታቸው የሚሰማኝ ስሜት አለ።

” የእግርኳስ ተጫዋችነት ዘመኔ 10 ዓመት ብቻ ነው። ከዚህ በላይ መጫወት እችል ነበር። ሆኖም ወደ አሰልጣኝነቱ ለመግባት ከነበረኝ ፍላጎት የተነሳ እግርኳስን አቁሜያለው። ወደ ውጭ ሀገር በመሄድ የመሰልጠን ፍላጎት ነበረኝ ። ያው ወደ ፊት ወደ ዚህ ሙያ መመለሴ አይቀርም።

” ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ዋና ቡድን ለመጀመርያ ጊዜ ተመርጬ ከጊኒ ጋር ያደረኩትን ጨዋታ እና በሴካፋ ዋንጫ ሩዋንዳ ሄደን በ50 ሺህ ደጋፊዎች መሐል ያንን ዋንጫ ይዘን የመጣንበት ጨዋታ በእግርኳስ ህይወቴ መቼም የማልረሳው ትውስታዬ ነው።

” ወንድ ልጄ አዶንያስ አዲስ አበባ ነው ያለው። እግርኳስ የመጫወቱ ፍላጎት ከፍተኛ በመሆኑ ወደፊት ጥሩ ተጫዋች ይሆናል ብዬ አስባለሁ።”

ደብሮም በደደቢት የታዳጊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ አና የዋናው ቡድን በም/አሰልጣኝነት ማገልገሉ የሚታወቅ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በሲውዲን ሀገር እየኖረ ይገኛል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ