Soccer Ethiopia

በደቡብ ኢትዮጵያ ተጀምሮ በአሜሪካ ካንሳስ የቀጠለው የታዳጊው የእግር ኳስ ጅማሮ

Share

በስፖርቲንግ ካንሳስ ሲቲ አካዳሚ ውስጥ የሚገኘው ናቲ ክላርክ ወደ ትውልድ ሀገሩ ኢትዮጵያ ለጉብኝት የመጣበትን አጋጣሚ በመንተራስ ስለታዳጊው ጥቂት ልንላችሁ ወደናል።                                             

ከአስር ዓመት በፊት የተከሰተውን የሀይቲ መሬት መንቀጥቀጥ ተከትሎ በማደጎ ልጅ ለማሳደግ የወሰኑ ጓደኞቻቸውን ተሞክሮ በመውሰድ ነበር ቤኪ እና ጂፍ ክላርክ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት። በሃምሳዎቹ አጋማሽ ይገኙ የነበሩት እና የሦስት ልጆች ባለቤት የሆኑት ጥንዶች መዳረሻም በደቡብ ኢትዮጵያ ሲዳማ ዞኝ የምትገኘው በንሳ ነበረች። ይህ አጋጣሚም የአንድ የአምስት ዓመት ልጅን የህይወት አቅጣጫ ቀይራለች። ከአያቱ ጋር ይኖር በነበረባት በንሳ በቅጠል በተሞሉ የካልሲ ኳሶች እግር ኳስን እየተጫወተ ያደገው ህፃን ከጥንዶቹ ጋር እስከወዲያኛው የመኖር ዕድልን አገኘ ፤ የዛሬው ናቲ ክላርክ።

የያኔው የበንሳ ብላቴና የክላርክ ቤተሰብ አባል ሆኖ ወደ አሜሪካ ቶፔካ ካቀና በኋላም አዲሱን ህይወቱን መላመድ ብዙ እንዳልከበደው አሳዳጊዎቹ ይናገራሉ። ለመጀመሪያ ጊዜ ባዩት ወቅት እየተጫወተ ያገኙት እግር ኳስን በቀጣይነት እንዲጫወት ዕድል ሲሰጡትም ተሰጥኦው በግልፅ እየታየ መጣ። አስረኛ ዓመቱ ላይ ሲደርስም የስፖርቲንግ ካንሳስ ሲቲን አካዳሚ የ12 ዓመት በታች ቡድን መቀላቀል ቻለ። በቆይታውም ከችሎታው መሻሻል በተጨማሪ በቶሎ በስሎ መታየቱ እና የመሪነት ባህሪው ‘አጎት ክላርክ’ የሚል ቅፅል ስም አስገኝቶለታል። በመሀል ተከላካይ ቦታ ላይ እየትጫወተ የሚገኘው ይህ በትውልድ ኢትዮጵያዊ የሆነ ታዳጊ ከአንድ ዓመት በፊት ለአሜሪካ የ15 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የመጠራት ዕድልም ገጥሞታል። ፖካንድ ላይ በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር በተዘጋጀው ምጥን ውድድር ላይም በሦስት ጨዋታዎች ላይ መሰለፍ ችሏል።

ኮቪድ 19 በዓለም አቀፍ ደረጃ ከመዛመቱ ወራት በፊት የ15 ዓመቱ ተከላካይ በትውልድ ሀገሩ ኢትዮጵያ ለሚገኙ ታዳጊዎችን የሚያነሳሳ ደግነቱን አሳይቶ ነበር። ባሳለፍነው ጥር ላይ ተጫዋቹ ወደ ኢትዮጵያ በንሳ ወረዳ በመምጣት በካንሳስ ሲቲ የተዘጋጁ ስጦታዎችን አበርክቷል። ከአያቱ ጋር የመጀመሪያዎቹን አምስት የልጅነት ዓመታት ባሳለፈበት በዚህ አካባቢ ኳሶች ፣ መለያዎች እና ቁምጣዎችን ለአካባቢው የታዳጊዎች ቡድን አበርክቷል። ክላርክ ስለሁኔታው ሲናገር “ቤተሰቦቼ ኢትዮጵያዊያን ለእግር ኳስ ያላቸውን ፍቅር ያውቃሉ። በመሆኑም የእግር ኳስ መገልገያ ቁሳቁሶችን ማከፋፈል ጥሩ ሀሳብ እንደሆነ አምነውበት ነበር። እናም አካዳሚው ኳሶች ፣ ቁምጣዎች እና መለያዎችን ሲሰጥ እኛም ተጨማሪ አልባሳት እና ጫማዎችን ሰጥተናል። ” ብሏል። ክላርክ ከቡድን አጋሮቹ ጃክ ዲን እና ቤተሰቦቹም ተጨማሪ ስጦታዎችን ለልጆቹ አስረክቧል። ከዛም አልፎ ስምንት ሻንጣ የሚሆኑ ቁሳቁሶችን ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች ፣ ቡድኖች እንዲሁም ከጓደኞቹ እና ከቤተሰቦቹ አሰባስቧል።

መስጠትን በአምስት ዓመቱ በማደጎ ከወሰዱት ከአሳዳጊ ቤተሰቦቹ እንደተማረ የሚናገረው ታዳጊው ተግባሩ የፈጠረበትን ስሜት እንዲህ ሲል ተናግሯል። ” ባደግኩበት አካባቢ ብዙ ነገሮች ሳይሟሉልኝ እንዳድኩ አስታውሳለው። አሁን ደግሞ ብዙ የማልጠቀምባቸው ነገሮች አሉኝ። እናም እነዚህን ቁሳቁሶች በጣም ለሚያስፈልጓቸው ሰዎች ማድረስ ትልቅ ዕድለኝነት ነው። እኔ ተርፎኝ እንደዘበት የተውኳቸውን ነገሮች እነሱ ዕለት በዕለት ሊጠቀሙባቸውም ይችላሉ። ”

በጎ አድራጊው የመሀል ተከላካይ ታዳጊ የእግር ኳስ ህይወቱ ቀጥሎ በሙሉ ጊዜ እግርኳስ ተጫዋችነት እናየው ይሆን ?

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ

ሶከር ኢትዮጵያ

ሶከር ኢትዮጵያ በ ‘አብርሀም ገ/ማርያም የማስታወቂያ ድርጅት’ ስር የሚሰራ ድረገፅ ሲሆን በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ በሚያተኩሩ ዜናዎች፣ ቁጥራዊ መረጃዎች፣ ታሪኮች፣ ጥልቅ ዘገባዎች፣ አስተያየቶች እና ትንታኔዎች ላይ ትኩረቱን ያደርጋል።

ዘርፍ

ማኅደር

top