“ተስፋዬ ኡርጌቾ አባቴ እንደሆነ ይታወቅልኝ” – ሜላት ተስፋዬ (ልጅ)

የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና ቅዱስ ጊዮርጊስ አማካይ ተስፋዬ ኡርጌቾ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ ከተሰማ ሰባተኛ ቀን ሆኖታል። ተስፋዬ ኡርጌቾ ከእግርኳስ ህይወቱ ውጭ ባለው የግል ህይወቱ ዙርያ በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን ልጅ አለው የለውም በማለት የሚሰጡት መረጃዎች ያሳሰበት የመጀመርያ ሴት ልጁ ሜላት ተስፋዬ “እኔ ልጁ ነኝ” ስትል ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገችው አጭር ቆይታ ተናግራለች።

” በመጀመርያ አመሰግናለው። አባቴ በጣም መልካም እና ቅን ሰው ነበር። በእርሱ ህልፈት የተሰማኝ ሀዘን ከፍተኛ ነው። ነፍሱን ፈጣሪ በገነት ያኑርልኝ። አባቴ በእግርኳስ ተጫዋችነቱ ለሀገሩ ሰርቶት ባለፈው ነገር ሁሉ ኩራት ይሰማኛል። በመቀጠል ወደ ሚዲያ የወጣሁት ብዙም ፈልጌ አልነበረም። ነገር ግን በአንዳንድ ሚዲያ ላይ ልጅ እንደሌለው ተደርጎ ሲነገር ስሰማ ‘ለምን?’ ብዬ ነው። ልጁ መሆኔ እንዲታወቅ እፈልጋለው። ከአባቴ ጋር እስከ ህልፈተ ህይወቱ ድረስ እንገናኝ ነበር። አሁን 23 ዓመቴ ነው። በትምህርቴም ዘንድሮ በሆቴል ማኔጅመንት ተመራቂ ነኝ። ትምህርቴንም እንድማር ይረዳኝ የነበረው አባቴ ነበር። እኔ ዋናው የምፈልገው የተስፋዬ ልጁ መሆኔ እንዲታወቅ ነው።” ብላለች።

በተያያዘ ዜና ዛሬ ማታ በሚቀርበው የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር የሬድዮ ፕሮግራም ላይ እንግዳ ሆና እንደምትቀርብ እና ምን አልባትም የክለቡ የበላይ አመራሮች አንድ ነገር ሊያደርጉላት እንደሚችሉ ሰምተናል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ