የጆናታን ዊልሰን Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics የአማርኛ ትርጉም ምዕራፍ ዘጠኝ ሦስተኛ ክፍል ይህን ይመስላል።
ከ1958ቱ የሲውዲኑ የዓለም ዋንጫ በኋላ የሶቭየት እግርኳስ ወዳድ በብራዚላዊው ዲዲ ቴክኒካዊ ብቃት እጅጉን ተማርኮ ከርሟል፡፡ ሩሲያውያኑ በእነርሱ የጨዋታ አቀራረብ እንደ እርሱ ያሉ የአጥቂ አማካዮች አለመያዛቸውም ይከነክናቸው ገብቷል፡፡ በእርግጥ በ1960ዎቹ ሁለት የጨዋታ አቀጣጣዮች አግኝተዋል፡፡ የዳይናሞ ሞስኮዎቹ ቢባ እና ጊናዲ ጉሳሮቭ፡፡
በመሰረቱ ማስሎቭ ቀደም ብሎ ለቡድኑ (ዳይናሞ ሞስኮ) አባላት የአጥቂ አማካዮችን በላቀ መንገድ ለመጠቀም የሚያስችል ጥሩ ግንዛቤ ፈጥሮላቸው ነበር፡፡ በወቅቱ እነዚህን ተጫዋቾች በአግባቡ የመጠቀም ልማድና የእነርሱን አጨዋወት በሚመለከት ወጥ የሆነ አሰላለፍ አልነበረም፡፡ ለምሳሌ፦ በ1968 ቦስኮቭ የጉሳሮቭን ከኳስ መገለል የተቀበለው የክለቡን አጥቂ ዩሪ አቭሩትስኪን በድጋሚ የሥልጠና ሒደት የአጥቂ አማካይ ለማድረግ በመጣር እንደነበር ጋሊንስኪ ያስታውሳል፡፡ ” አቭሩትስኪ ለጨዋታ አቀጣጣይነት ሚና የተለየ ትኩረት ሰጥቶ ሰርቷል፡፡ ክፍት ቦታዎችን ማሰስ የዘወትር ተግባሩ አድርጓል፤ የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች እርሱ ላይ ጥብቅ ክትትል ሲያደርጉ የቡድን አጋሮቹ ነጻ ይሆናሉ፡፡ እርሱ ሁሌም በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፥ ኳሶች ሲደርሱትም የተሳኩ ቅብብሎች ይከውናል፡፡ ጥቂት ክፍተት ሲያገኝ ደግሞ በፍጹም ኳሱን ወደኋላ አይመልስም፡፡ ተጫዋቾች የቦስኮቭን ትዕዛዝ ይከተሉ-አይከተሉ አልያም የአሰልጣኛቸውን ሐሳብ ይረዱ-አይረዱ እርግጠኛ አይደለሁም፥ ነገርግን አቭሩትስኪ በቅርብ ርቀት ከሚቆጣጠረው ባላጋራ (Marker) ነጻ ሲሆን ሌሎች የቡድን አጋሮቹ ራሳቸው ኳሷን ወደፊት ማቀበል አልያም <ድሪብል> ማድረግ ቅድሚያ ይሰጣሉ፡፡ በእንዲህ አይነቱ ሁኔታ የጨዋታ አቀጣጣዩ መኖር የሚፈይደው ነገር አይኖርም፡፡ እንዲያውም ተቃራኒ ቡድን ሲያጠቃ በአግባቡ ስለማይከላከል እና አንድን ተጫዋችን በተናጠል ስለማይቆጣጠር (Marking) ለቡድኑ እንቅፋት ወይም ሸክም ይሆናል፡፡” ብሎ ጋሊንስኪ ጽፏል፡፡
ይህ ጉዳይ ሁሉም ቅሬታ የሚያነሳበት ችግር ሆኖ ዘልቋል፡፡ በተለይም በሰሜን አውሮፓ የቅንጦት ተጫዋቾች (Lexury Players) ላይ የሚጣለው እምነት በጣሙን አነስተኛ እየሆነ መሄዱ በሰፊው እየተለመደ መጣ፡፡
ጋሊንስኪ ለእነዚህ ተጫዋቾች ስለሚቸረው የተለየ እንክብካቤ የምሬት አስተያየቱን ይሰጣል፡፡ በዚህ ጉዳይ በስላቅ መልክም ቢሆን የሰላ ሒስ አቅርቧል፡፡ ” በእግርኳስ የተወሰኑ አሰልጣኞች የጨዋታ አቀጣጣዮችን የሚገልጿቸው በህክምና ማዕከል እንደሚገኙ ታማሚዎች ነው፡፡ አንድ ወይም ሁለት የፊት መስመር ተሰላፊዎች የመከላከል ግዴታዎቻቸውን እንዲተዉ ቢደረግ ምንም አይደል፡፡ ነገርግን ይህን በመሃል አማካዮች ማድረግ ይቻላልን? እርሱ (የጨዋታ አቀጣጣዩ) ዲዲ ነው? ወይስ ቻርልተን ነው?” ሲልም በጻፈው ጽሁፍ አፊዟል፡፡ የአጥቂ አማካዮች (Playmakers) የልዩ ክህሎት ባለቤት ካልሆኑ በቀር የመከላከል ግዴታ እንዳለባቸውም ጠቁሟል፡፡
ለዚህ ችግር ማስሎቭ እንደ መፍትሄ አድርጎ የወሰደው ብራዚላዊው ዲዲ በሜዳ ላይ ያገኘውን ነጻነት እርሱም ለፈጣሪ ተጫዋቹ ይህንኑ ነጻ ሚና መስጠት ነበር፡፡ ነገሩ የተዘነጋ ግኝት ሆኖ ቢቆይም በዜዜ ሞሬይራ የተፈጠረና ብራዚል በ1954ቱ የዓለም ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመችው በቀጠና የመከላከል ዘዴ (Zonal Marking) ነበር፡፡ በ1958 እና 1962ቱ የዓለም ዋንጫዎች ለብራዚል ብሄራዊ ቡድን መፍካት መሰረት የሆነው ኅልዮት በሶቭየት ህብረት ሃገራት ግን በፍጥነት ተቀባይነት ማግኘት አልቻለም፡፡ በቀጠና የመከላከል ዘዴን በቀላሉ መተግበር አስቸጋሪ የሚያደርገው ጥብቅ አደረጃጀት እና በተጫዋቾች መካከል ሊኖር የሚገባ ፍጹም መግባባትን መሻቱ ነው፡፡ ይህኛው የመከላከል አጨዋወት አንድ ተከላካይ በአቅራቢያው ያለ የተቃራኒ ቡድን ተጫዋችን በተናጠል እንደሚቆጣጠርበት ሥልት ቀለል ያለ ኃላፊነት አይደለም፡፡ ተከላካዩ በሚንቀሳቀስበት ዞን ሁለት የተጋጣሚ ቡድን የፊት መስመር ተሰላፊዎች ሊመጡ ይችላሉ፤ ምናልባት በሌላ የመከላከል ወረዳ ላይ የማጥቃት ሒደቱን የሚመሩ በርካታ ተጫዋቾች (Over-manning) ከተገኙም ተከላካዩ እዚህኛው ቦታ በመምጣት አንድ የተጋጣሚ አጥቂን መቆጣጠር ይጠበቅበት ይሆናል፤ በዚህ ጊዜ በመከላከል ሒደት ውስጥ ከሚገኘው ቡድን ሌላኛው ተከላካይ መጥቶ በቀድሞው ተከላካይ የተለቀቀውን ዞን መሸፈን ይኖርበታል። ይህ ሁሉ ታዲያ ያለ በቂ ዝግጅት እንዲሁ በቀላሉ ሊተገበር የሚችል አይደለም፡፡
ከ1966ቱ የዓለም ዋንጫ ቀደም ብሎ ኒኮላይ ሞሮዞቭ በሶቭየት ብሄራዊ ቡድን በቀጠና የመከላከል ዘዴን ለመተግበር ሞክሮ አልተሳካለትም፡፡ ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት ሃገሪቱ ከፈረንሳይና ሲ.ኤስ.ኬ.ኤ. ጋር ባካሄደቻቸው የወዳጅነት ግጥሚያዎች ስድስት ግቦች ከተቆጠረባት በኋላ አሰልጣኙ በመከላከል ሥልቱ ላይ እምነት አጣ፡፡ ስለዚህም አምስት ተከላካዮችን የማሰለፍ አማራጭ ወሰደ፡፡ አንድ ጠራጊ ተከላካይ (Sweeper) ከአራቱ ተከላካዮች ጀርባ ሆኖ የማጽዳት ሥራውን እንዲያካሂድ ታዘዘ፤ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት በተጋጣሚ ቡድን ሥር ሲሆንም የመሃል አማካዮች ወደኋላ እየተመለሱ እንዲከላከሉ ተደረጉ፤ የማጥቃት ሒደቱም በፈጣን የመልሶ-ማጥቃት እንቅስቃሴ እንዲከወን ተወሰነ፡፡ ከዚያ ሶቭየቶች በውድድሩ ግማሽ ፍጻሜ ደርሰው በዓለም ዋንጫ የተሳትፎ ታሪካቸው ምርጡ ደረጃቸውን ያዙ፡፡ ከሄሌኒዮ ሄሬራው ኢንተርሚላን ጋር የሚመሳሰለው እጅግ ጠንካራው የመከላከል አደረጃጀታቸው (Ultra-Defensive System) ለአንድ ችግር ብቻ የሚያገለግል አይደገሜ መፍትሔ (One-off Solution) ከመሆን አልዘለለም፡፡
ማስሎቭ በአሰልጣኝነት ሥራው በቀጠና የመከላከል ዘዴን (Zonal Marking) የሙጥኝ ብሎ ዘለቀበት፡፡ እርሱ ይህን የመከላከል አጨዋወት ሥርዓት የሥነ ምግባር መርህ ያህል ሊከተለው የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ ወስኗል፡፡ እንዲያውም አንዴ “ተጫዋችን-በ-ተጫዋች የመያዝ (Man-Marking) የመከላከል ሥርዓት ኃላፊነቱ ለሚሰጠው ተጫዋች የመዝለፍ፣ የማዋረድና ሞራላዊ ጭቆና የማሳደር ያህል ነው፡፡” እስከ ማለት ደርሷል፡፡
ያኔ ቢባ የትኛውንም የተጋጣሚ ተጫዋች በቅርብ ርቀት ሆኖ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲያደርግ አይታዘዝም ነበር፡፡ ለነገሩ በወቅቱ ሌሎቹም የዳይናሞ አማካዮች ይህ አይነቱ ግዴታ አልተጫነባቸውም፡፡ ” ሙሉ ዴሞክራሲያዊ መብቱን እንዳስጠበቀ የቆየው አንድሪይ ቢባ ብቻ ነው፡፡ እርሱ እጅግ ጎበዝና ታማኝ ተጫዋች ነበር፡፡ በተፈጥሮ የተቸረው ክህሎቱን የሚያመክኑ ተጨማሪ ሚናዎች መቀበል ፈጽሞ አይፈቅድም፤ ማድረግ የሚጠበቅበትን ብቻ ይከውናል፡፡ ቢባ ለጨዋታው መልክ የመስጠት ሙሉ መብት ነበረው፡፡ አጠቃላይ የጨዋታ ቅርጽ የሚያስጠብቁ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ረገድ ሜዳ ላይ እንደ አሰልጣኝ ሆኖ ቡድኑን ይመራል፡፡ ሌሎቹም ከእርሱ የተለያዩ ሐሳቦችን በመቃረም የሚቻላቸውን ያህል ራሳቸውን ለማብቃት ጥረዋል፡፡” ይላል ማስሎቭ፡፡
ማስሎቭ በጥሩ ሁኔታ የተደራጀ ቡድን በእያንዳንዱ የሜዳ ክፍል ላይ ከተጋጣሚ አንጻር የተጫዋች ቁጥር ብልጫ ሊያገኝ እንደሚችል ያምናል፡፡ ይህን እሳቤ ጂኦርጂይ ኩዝሚን የተባለው ጋዜጠኛ በቅርጫት ኳስ የጨዋታ ሒደት ውስጥ አስተውሎት <ኪዬቭስኪዬ ቬዶሜስቲ> የተሰኘ ጋዜጣ ላይ እንዳሰፈረው ይናገራል፡፡ ቢባ ነጻ ሚና ተሰጥቶት ሲጫወት በመሃለኛው የሜዳ ክፍል የመከላከሉን ሥራ በመደበኛነት የሚወጣ ተጫዋች (Fixed Defensive Unit) ያስፈልገዋል፡፡ ይህም ከአራቱ የኋላ መስመር ተሰላፊዎች መካከል አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የመስመር ተከላካዮቹ (Full Backs) ወደፊት እንዲሄዱ ያግዛቸዋል፡፡ በአራት ተከላካዮች (Back Four) ከተዋቀረው የተከላካይ ክፍል ፊት ሆኖ አንጋፋው ተከላካይ ቫሲል ቱርያንቺክ ይህን ኃላፊነት በአግባቡ ይወጣል፡፡ በዚህም ሳቢያ ተጫዋቹ በሶቭየት እግርኳስ የመጀመሪያው የተከላካይ አማካይ (Holding Midfielder) ለመሆን ችሏል፡፡ ማስሎቭ እንደሚናገረው የእርሱ ዋነኛ ሥራ ቀዳሚ የመከላከያ መስመርን በመዘርጋት (First Line of Resistance) የተጋጣሚ ቡድን አጥቂዎችን እንቅስቃሴ መመከት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የዳይናሞ ኪዬቮችን የማጥቃት ሒደት ማስጀመር የእርሱ ቀጣይ ተልዕኮ ይሆናል፡፡ በሌላ ቋንቋ ቱርያንቺክ ልክ ጆዜፍ ዘካሪያስ ለሃንጋሪዎቹ ሲያደርግ የነበረውን ለዳይናሞዎች ያደርግ ጀመር፡፡ በዚያ ዓውድ ሲታይ ተጫዋቹ የእግርኳስ ህይወቱን ሲጀምር በመሃል አጥቂነት መሆኑ ለአዲሱ ሚናው እገዛ እንዳደረገለት ይገመታል፡፡ የሃንጋሪያውያኑ ተጽዕኖ በሰፊው ካረፈበት ቦታ እንደተገኙት ዛቦ እና ሜድቪድ ሁሉ ምናልባት እርሱም ከዛካርፓትያ መምጣቱ የራሱ የሆነ ድርሻ ሳይኖረው እንዳልቀረ ይታሰባል፡፡
ከሁሉም በላይ ግን ቱርያንቺክ ባላጋራን ተጭኖ የመጫወት ዘይቤን (Pressing Game) ለመተግበር ጉልህ ድርሻ የነበረው መሆኑ ነው፡፡ እንዲህ አይነቱን ተጽዕኖ ፈጣሪና የጨዋታን ውስብስብ ታክቲክ (Geometry of the Game) በቀላሉ የሚረዳ ተጫዋች ባይኖረው ኖሮ ማስሎቭ ይህን የአጨዋወት ሥልት ይሞክረው ነበርን? ጭራስ ያስበውስ ይሆን? የየዕለት ውሎውን የሚያሰፍርበት ማስታወሻዎች አልያም መጽሄቶች ስለሌሉ ምላሹን መስጠት ይከብዳል፡፡ ማስሎቭ ቀደም ሲል ቢባን በተጠቀመበት መንገድ ቱርያንቺክንም ለመጠቀም መወሰኑ የበዛ ብልሃተኝነቱን አመላክቷል፡፡ አማካዩ ከኋላ እየተነሳ ጨዋታ የመምራት ብቃቱ በርካታ አማራጮችን ለማሰብ የሚያስችል ከመሆኑም በላይ ተጫዋቹ ክህሎቱን የሚጠቀምበት ሒደት ለሌሎቹ የቡድኑ አባላት ትምህርት እንዲሆናቸው ያግዛል፡፡ በ1966 በቪክቶር ማስሎቭ ሥር ዳይናሞዎች የመጀመሪያ ዋንጫቸውን ሲያሸንፉ የቡድኑ አማካይ ክፍል እጅጉን የተጠቀጠቀ፣ ተጋጣሚን መፈናፈኛ አሳጥቶ በሜዳው ላይ የሚፈጠሩ ያልተጠበቁ ክፍተቶችን ለመቆጣጠር የሚጥር ነበር፡፡ ያኔ የሞስኮ ህትመት ውጤቶች ስጋት ባረበበባቸው አርዕስቶች ተጥለቅልቀዋል። አንድ ጋዜጣ እንዲያውም አራት የዳይናሞ ተጫዋቾች ኳሱን ወደያዙት የተቃራኒ ቡድን ተጫዋቾችን ቀረብ ብለው በሚያሳይ ምስል ሥር ” ይህ አይነቱን የእግርኳስ አጨዋወት አንፈልግም፡፡” የሚል ጽሁፍ ይዞ ወጥቷል፡፡
የተጋጣሚ ቡድንን ተጭኖ የመጫወት ዘይቤ (Pressing) ከመሃል አማካዮች የማያቋርጥ እንቅስቃሴን እንደሚሻ ሁሉ ከፍተኛ የአካል ብቃትም ይጠይቃል፡፡ በእግርኳስ ጅምር ዓመታት በቀላሉ ተተግባሪ ያልነበረውም በዚህ ምክንያት እንደሆነ መገመት አያዳግትም፡፡ በዳይናሞ ኪዬቭ ዘመናዊውን የሥነ-ምግብ እና የአካል ብቃት አጠባበቅ ለመረዳት መጠነኛ ግራ መጋባት እንደተፈጠረ ሁሉ እግርኳስን የሙሉ ጊዜ ሥራ ማድረግም ቀድሞ የሚጠየቅ ጉዳይ እየሆነ ሄደ፡፡ ክለቡ በ1961 በያቼስላቭ ሶሎቪዮቭ መሪነት የመጀመሪያውን ድል ሲቀዳጅ በአካል ብቃቱ ረገድ እጅግ ጠንካራ ቡድን የነበረ መሆኑ ተጠቃሽ ነው፡፡ ቪክቶር ማስሎቭ ደግሞ አጠቃላይ ነገሮችን ከፍ ወዳለ ደረጃ አሻግሯል፡፡ የቡድኑ አማካይ ቮሎድሚር ሙንቲያን ” ለተጫዋቾች የአካል ብቃት ዝግጅት ከፍተኛ ትኩረት በመቸር ማስሎቭ የመጀመሪያው የዳይናሞ አሰልጣኝ ነው፡፡ ሁሌ የሚታወሰው የሌቫኖቭስኪ ገድል ቢሆንም በዚህ ረገድ የሚልቀው ድርሻ የማስሎቭ ነው፡፡ ሌቫኖቭስኪ ሳይንሳዊ የአካል ብቃት መሰረታውያን ላይ ነበር የሚያተኩረው፡፡” ሲል ይመሰክራል፡፡
ምስል፦ ዳይናሞ ኪዬቭ 1-1 ሴልቲክ፣ በአውሮፓ ክለቦች ዋንጫ- የመጀመሪያው ዙር ሁለተኛው ጨዋታ፣ ኪዬቭ፣ 1967
ይቀጥላል...
ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡ ባለፉት አስራ ሦስት ዓመታትም አስር መፅሐፍትን ለህትመት አብቅቷል፡፡