“የዘመኑ ኮከቦች ገፅ” ከአዲስ ግደይ ጋር…

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በመሰረዙ ምክንያት ተጫዋቾች በምን ሁኔታ ወቅቱን እያሳለፉ ነው በሚል በጀመርነው አምድ ከአዲስ ግደይ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በከፍተኛ የግብ አስቆጣሪነት ዝርዝር ውስጥ ባለፉት ዓመታት ስሙ የሚጠራው አዲስ ግደይ በ2005 ለስልጤ ወራቤ በክለብ ደረጃ በመጫወት የእግር ኳስ ህይወቱን ጀምሮ ለሦስት ዓመታት ቆይታውን በዚያ አድርጓል፡፡ የወራቤ ቆይታውን ካጠናቀቀ በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ሲዳማ ቡና 2008 ላይ ከመጣ ጊዜ አንስቶ በወጥነት አስደናቂ ብቃቱን እያሳየ የሚገኘው አዲስ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በተደጋጋሚ ጥሪ ደርሶታል። አጥቂው የኮሮና ቫይረስ ወደ ሀገራችን መግባቱን ተከትሎ ፕሪምየር ሊጉ በመሰረዙ ይህን ጊዜ እንዴት እያሳለፈ እንደሆነ እና ተያያዥ አዝናኝ ጥያቄዎችን አክለን በዘመኑ ኮከቦች ገፅ ይዘነው ቀርበናል፡፡

“ጊዜዬን የማሳልፈው …”

“ኮሮና ከገባ ጊዜ አንስቶ የግል እንቅስቃሴዎችን እያደረግኩ እንዲሁም ፊልሞችን እያየሁ ነው ጊዜዬን የማሳልፈው፡፡ ከዚህ በፊት ያልተለመደ በሽታ ስለሆነ በባለሙያ በሚሰጡ ምክሮች በሚዲያዎች መረጃዎች በማግኘት በዛ መልኩ ጥንቃቄዎችን እያደረግኩ ነው፡፡ እኔም አብረውኝ የሚኖሩትም ሁሉም ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ጥንቃቄዎችን እያደረግን ነው የምንገኘው።”

“ተጫዋች ባልሆን ኖሮ…”

“በተደጋጋሚ ይሄን ነገር መልሼዋለሁ፤ ኳስ ተጫዋች ባልሆን ኖሮ ነጋዴ እሆን ነበር። (ሳቅ) እርግጠኛ ሆኜ ነጋዴ ያልኩት ልጅ እያለሁኝ ያው የደሀ ቤተሰብ ልጅ ስለሆንኩ በበቂ ሁኔታ ወደዛ ለመግባት ማንኛውንም ሥራ እሰራ ነበር፡፡ በተለይ መንገድ ላይ ፍራፍሬዎች እና የተለያዩ ነገሮችን በመነገድ ውስጥ ስላደኩኝ ነጋዴ መሆኑ ይቀለኝ ነበር።”

“አብሮኝ ቢጫወት…”

“በብሔራዊ ቡድን ደረጃ የተወሰነ ጨዋታዎችን አብሬው ብጫወትም በክለብ ደረጃ ግን አብሮኝ ቢጫወት ደስ የሚለኝ ሳላሀዲን ሰዒድ ነው። በጣም ጎበዝ አጥቂ ነው፡፡”


“የመጀመርያ ጎሌ…”

“በሚገባ አስታውሰዋለሁ፤ የመጀመሪያ የፕሪምየር ሊግ ጎል ያስቆጠርኩት ወላይታ ድቻ ላይ ነው፡፡ ይርጋለም ስታዲየም ላይ ነበር ጨዋታው። የማልረሳባቸው ብዙ አጋጣሚዎች ነበሩ። ከተቀያሪ ወንበር ተነስቼ በሁለተኛው አጋማሽ በመጀመሪያ የኳስ ንክኪ ነበር ጎል ያስቆጠርኩት። ጎሉን ባላገባ እንኳን የተፈጠሩት ምክንያቶች ጨዋታውን እንዳልረሳው የሚያደርገኝ ነበር፡፡ በብሔራዊ ቡድን አንድ ጎል አለኝ። ከጅቡቲ ስንጫወት ድሬዳዋ ላይ በነበረን ጨዋታ ጎል አስቆጥሬያለሁ፡፡

“ራስን ዝግጁ ማድረግ…”

“በሽታው በጣም ጥንቃቄ ስለሚፈልግ ከባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክሮች ህብረተሰቡ ተግባራዊ ማድረግ እና ታዛዥ መሆን ይጠበቅበታል። የሚሰጡትን የግንዛቤ ማስጨበጫዎች ሳይዘናጋ መፈፀም አለበት። በዚህ አጋጣሚ ተጫዋቾችም ካቆምን ወደ ሁለት ወር ገደማ ሆኖናል። ከዚህ በኃላ ረዘም ላለ ጊዜ ላንገናኝ ስለምንችል አካል ብቃታቸውን እየሰሩ ሳይዘናጉ መጠበቅ አለባቸው። በቤት ውስጥ እንቅስቃሴ በማድረግ ለቀጣዩ ውድድር ራሳቸውን በሚገባ አዘጋጅተው እንዲቀርቡ ማለት እወዳለሁ።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ