የመንግስቱ ወርቁ ‘የኖራ ማህተም’

ታሪካዊው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ሰው መንግስቱ ወርቁ በተጫዋችነት ዘመኑ በአንድ ወቅት በሜዳ ላይ የፈጠረውን ትዕይንት ከገነነ መኩሪያ ጋር ካደረገው ቃለ መጠይቅ እና ኃላ ላይ በመፅሐፍ መልክ ከወጣው ታሪክ በመነሳት እንዲህ አቅርበንላችኋል።

በሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ቻምፒዮን የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በጋሽ ይድነቃቸው ተሰማ ጥረት እስከ አውሮፓ ድረስ እየሄደ የወዳጅነት ጨዋታዎችን በማድረግ ራሱን ይበልጥ ያጠናክር ነበር። በመሆኑም በምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ ሀገራት አንፃር ሲታይ በእጅጉ የተሻለ አቋም ላይ ይገኝ ነበር። ከሜዳው ውጪ አራት እና አምስት ጎል እያስቆጠረ የጎረቤት ሀገራትን ማሸነፍ የለመደው የዚህ ታሪካዊ ስብስብ ተጫዋቾች ከሜዳ ላይ ብቃታቸው በተጨማሪ እርስ በእርስ በነበራቸው ልዩ ቅርርብ እና መተሳሰብም ጭምር ይታወቃሉ። በጨዋታ መሀል አንዳቸው ከተነኩ ቀሪዎቹ እንደንብ ተነስተው እስከ ጨዋታ መቋረጥ ድረስ የሚያደርስ ፀብ ውስጥ የገቡባቸው አጋጣሚዎችም በርካታ ነበሩ።

ዛሬ የምናስነብባችሁ ታሪክ መነሻም ተመሳሳይ ይዘት ነበረው። ብሔራዊ ቡድኑ ለቀጣዩ የአራተኛው አህጉሪቱ ዋንጫ ወደ ጋና ከማምራቱ አስቀድሞ ከኬኒያ ጋር የደርሶ መልስ ጨዋታ አድርጎ ነበር። ኬኒያ ላይ በተደረገው የመጀመሪያ ጨዋታም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እየመራ በነበረበት ወቅት የኬኒያው ግብ ጠባቂ ኢታሎ ባሳሎ ላይ በሰራው ጥፋት ኢታሎ ከጋናው የአፍሪካ ዋንጫ ውጪ ያደረገውን የስብራት ጉዳት አስተናገደ። በዚህም የተነሳ ሜዳ ውስጥ ድብድብ ተጀምሮ ህዝቡ ወደ ሜዳ እስከመግባት ፖሊስም አስለቃሽ ጭስ እስከመተኮስ ደረሰ። ኢታሎ ላይ በሆነው ነገር ልባቸው የተነካው የይድነቃቸው ልጆችም 4-3 ለመሸነፍ ተገደዱ።

ፈገግ የሚያሰኘው ጉዳይ የተከሰተው በመልሱ የአዲስ አበባ ጨዋታ ነበር። የቡድን አጋራቸው እና ቁልፍ ተጫዋቻቸው ኢያሎ ጉዳት እልህ ውስጥ የከተታቸው ኢትዮጵያዊያኑ ሰባት ግቦችን ተጋጣሚያቸው ላይ አዝንበው ጨዋታውን በ7-1 አሸናፊነት አጠናቀቁ። በወቅቱ የቡድኑ ኮከብ የነበረው መንግስቱ ወርቁ ግን ይህ ብቻ አልበቃውም። እልኸኛው አጥቂ በስሙ አራት ግቦችን አስቆጥሮ ጎል ቢጠግብም ልቡ አልረካም ነበር። ስምንተኛ ግብ የሚያስቆጥርበትን ዕድልም አገኘ ሊያውም የኬኒያን ተከላካዮች ከኋላው አስቀርቶ ግብ ጠባቂውን ለብቻው የሚያገኝበት አጋጣሚ። መንግስቱ ግን ግብ ለማስቆጠር አላሰበም። ታላቁ 8 ቁጥር ከጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ /ሊብሮ/ ጋር ካደረገው እና ኋላ ላይም በመፅሀፍ መልክ በታተመው ቃለ ምልልስ ላይ በዛች ቅፅበት ያደረገውን ነገር እንዲህ ሲል ተናግሯል።

… ” ተከላካዮቹን ሁሉ አምልጬ ሄጄ ከርቀት ከበረኛው ጋር ተገናኘን። ተከላካዮቹ ወደ ኋላ ቀርተዋል። ያልተከተሉኝ በረኛውን አልፌ እንደማገባ ስላወቁ ነው። እኔ ግን ኳሷን ፔናሊቲ መስመሩ ኖራ ላይ በእግሬ ረግጬ በደንብ ኖራው ላይ አሸኋትና ወደ ፊት ትንሽ ነካ አደረኳትና አስቀመጥኳት። ይሄ ሁሉ የሚሆነው በአጭር ሰኮንድ ውስጥ ነው። በረኛው በጣም ጥቁር ነው። እጁና ፊቱ ሁሉ ሰፊ ነው። ልክ ኖራው ላይ አሻሽቼ ሮጦ ሲመጣ ጎን እና ጎን ይመታል ብሎ እጁን ዘርግቶ ስለነበር አነጣጠርኩ እና በኃይል ፊቱን ስመታው በቂጡ ቁጭ አለ። በረኛው ሲነሳ ኳሱ ላይ ያለው ኖራ እንደ ማህተም ፊቱ ላይ ስለቀረ ሕዝቡ ፊቱን እያየ ይስቅ ጀመር። እኔም እልህ የያዘኝ ቢሆንም ፊቱን ሳየው በዚያ ጥቁረቱ ላይ የኖራው ንጣት የኳሱን ቅርፅ አይቼ ሳልወድ አሳቀኝ።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ