“የዘመናችን ከዋክብት ገፅ” ከአቡበከር ናስር ጋር…

የኢትዮጵያ ቡና የወቅቱ አጥቂ አቡበከር ናስር በዘመናችን ከዋክብት ገፃችን የዛሬ እንግዳ ነው። ወቅቱን በምን ሁኔታ እያሳለፈ እንደሚገኝ ከአዝናኝ ጥያቄዎች ጋር ያደረገው ቆይታን እነሆ።

በሁሉም የእድሜ እርከን ለብሔራዊ ቡድን መጫወቱ ልዩ ያደርገዋል። ከአሰልጣኝ ደግፌ ተስፋ ፍሬ የታዳጊ ቡድን የጀመረው የእግርኳስ ህይወቱ፣ በሐረር ሲቲ የአንድ ዓመት ቆይታ ካደረገ በኋላ ከ2009 ጀምሮ በኢትዮጵያ ቡና እየተጫወተ ይገኛል። ወደፊት ብዙ ስኬቶች ከሚጠብቃቸው ከዋክብቶች መካከል አንዱ እንደሚሆንም ይገመታል። በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ውድድሮች መሰረዛቸውን ተከትሎ የዘመናችንን ከዋክብት ወቅቱን በምን ሁኔታ እያሳለፉ እንደሚገኝ ከአዝናኝ ጥያቄዎችን ጋር በዚህ አምዳችን ከእኛ ጋር ቆይታ አድርጓል።

“እንኳን አደረሳችሁ”

ለመላው የእስልምና ተከታይ ኢትዮጵያውያን በሙሉ እና በኢትዮጵያ ቡና በሌሎች ክለቦችም ለሚገኙ ተጫዋቾች እንዲሁ እንኳን ለ1441ኛው የኢድ አል ፈጥር በዓል አደረሳቹ ማለት እፈልጋለሁ።

“ምሳሌ የማደርገው ተጫዋች…”

እንደምታቀው እኔ እና ሚኪያስ መኮንን ወደ ኢትዮጵያ ቡና እንደመጣን ያለውን ነገር እያስረዳን፣ ያለ ፍርሀት አቅማችንን አውጥነት እንድንጫወት፣ ወደፊት ትልቅ ተጫዋቾች እንደንሆን ይመክረን የነበረው፤ በግል ስብዕናውም ሆነ በችሎታው ሁሉም የሚያደንቀው መስዑድ መሐመድ ለእኔ ትልቅ ምሳሌ ነው። ለአንድ ቡድን የሚያስፈልጉ ነገሮች ሁሉ አሟልቶ የያዘ ተጫዋች ነው። ይህን አክብሮቴን ለመግለፅ በአንድ ወቅት ጎል አግብቼ ወደ እርሱ በመሮጥ ስሜቴን ገልጬ ነበር።

“ኳስ ተጫዋች ባልሆን…”

እውነት ለመናገር ከእግርኳስ ተጫዋች ባልሆን ይሄን እሆናለው ብዬ አስቤ አላውቅም። ምክንያቱም ቤተሰቦቼ እግርኳስን የሚጫወቱ መሆናቸው እና ከቤታችን አቅራቢያ ጉቶ ሜዳ በመኖሩ እግርኳስ ተጫዋች ከመሆን ውጭ ሌላ ነገር አስቤ አላውቅም።

ከወንድምህ እና ከአንተ ማን ይበልጣል?

ከሬድዋን ጋር በችሎታ ነው? እንዴ ያው እኔ እበልጠዋለው… (በጣም እየሳቀ)። አይ አይ እርሱ ይበልጣል። ትልቁ ወንድማችን ነው የሚበልጠው።

ፈርተህ ነው ?

ኧረ አይደለም። ያው አለ አይደል ሰለሚበልጠኝ ነው።

“የምወደው ምግብ..”

ሩዝ በስጋ በጣም የምወደው ምግብ ነው። እርሱን አዘውትሮ መብላት ደስ ይለኛል። ከዚህ ውጭ ሌሎች ምግቦችን መብላት ደሰ ቢለኝም እንደ ሩዝ በስጋ የምወደው ምግብ የለም።

“ከታደለ ጋር መጫወት…”
ታደለ መንገሻ አብሮኝ እንዲጫወት የምፈልገው ተጫዋች ነው። ካስታወስክ ኢትዮጵያ ከአልጄሪያ ጋር በአዲስ አበባ ስታዲየም ሲጫወቱ ቁጭ ብዬ ጨዋታውን የመከታተል እድሉ ነበረኝ። በዕለቱም ታደለ ያደረገውን ድንቅ እንቅስቃሴ ተመልክቻለው። ለጌታነህ ከበደ ያቀበለው ኳስ አስገራሚ ነበር። ዘንድሮ ኢትዮጵያ ቡና ይመጣል ተብሎ ሳይሳካ ቀርቷል። ከእርሱ ጋር አብሬ ብጫወት በጣም ደስ ይለኛል።

“ከእግርኳስ ውጭ…”

ብዙ ጊዜ የማሳልፈው ከሠፈር ልጆች ጋር አብሮ በመዋል ነው። ይህ እኔን በጣም ያዝናናኛል። ከዚህ ውጭ በቂ እረፍት ማድረግ ከወንድሞቼ እና ከቤተሰቦቼ ጋር አብሮ በማሰላፍ ነው ከእግርኳስ ውጭ ያለውን ጊዜ የማሳልፈው።

“በጣም የሚያስቸግረኝ ተከላካይ..”

ከተከላካይ ለእኔ አስቸጋሪው የቅዱስ ጊዮርጊሱ አስቻለው ታመነ ነው። ምክንያቱም ጥሩ ኳስ ይጫወታል፣ በጉልበቱም መጫወት የሚችል ጎበዝ ተከላካይ ነው።

“በዋናው ብሔራዊ ቡድን…”

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ17 ዓመት በታች ታዳጊ ቡድን እያለው በደርሶ መልስ ጨዋታ ግብፅ ላይ ሦስት ጎል ካስቆጠርኩ በኃላ በወጣት፣ በኦሊምፒክ እና በዋናው ብሔራዊ ቡድን እስካሁን ጎል አላስቆጠርኩም። ወደፊት አይቀርም ለሀገሬ በትልቅ መድረክ ጎል እንደማስቆጥር።

ከሀገር ውጭ መጫወት

የማንኛውም ተጫዋች ህልም ከኢትዮጵያ ውጭ መጫወትን ነው። አንዳንድ ነገሮች አሉ በሂደት ሁሉ ነገር ሲጠናቀቅ የማሳውቀው ይሆናል።

በመጨረሻም

የኢድ አል-ፈጥር በዓል ለሁሉም ሙስሊም ማኀበረሰብ የሠላም እንዲሆን እየተመኘው ይህ ወረርሽኝ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል ሁላችንም ራሳችንን እንጠብቅ የሚል መልዕክቴን አስተላልፋለው።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ