ከጃን ሜዳ እስከ ዓለም መድረክ – የበዓምላክ ተሰማ የዓለም ዋንጫ ትውስታ

በዓለም አቀፍ መድረክ ሀገሩን ከፍ አድርጎ ያስጠራው በዓምላክ ተሰማ በዓለም ዋንጫ ኮስታሪካ ከ ሰርቢያ በነበረው የምድብ ጨዋታ ስለተፈጠረው ክስተት በትውስታ አምዳችን ይናገራል።

በሀገራችን ዳኝነት ፈታኝ በሆነበት በዚህ ዘመን ሙያውን አክብሮ ከመጀመርያ መምርያ ዳኝነት እስከ ኢንተርናሽናል ዳኝነት ድረስ በቁርጠኝነት እና በትጋት አሁን ላለበት ደረጃ ደርሷል። በዓምላክ ትውልድ እና እድገቱ አዲስ አበባ ነው። የዳኝነት ህይወቱ አስቀድሞ ረዳት ዳኛ የነበረ ቢሆንም ኃላ በመቀየር ዋና ዳኛ በመሆን በጃን ሜዳ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ መከላከያ ከ17 ዓመት በታች የታዳጊ (የC ጨዋታ) በማጫወት ጅማሮውን አድርጎ ሀገር ውስጥ በትልቅ የውድድር መድረኮች አንስቶ በአህጉራችን የክለቦች፣ የቻን እና የአፍሪካ ዋንጫን በብቃት ዳኝቷል። በዚህ ያልተገደበው ትሁቱ የመልካም ስብዕና ባለቤት በዓምላክ ተሰማ በዓለም አቀፍ መድረኮች ሀገሩን በመወከል እየሰራ ይገኛል። ያገኘውን ልምድ ለሙያ አጋሮቹ ያለ ስስት በማካፈል የሚታወቀው በዓምላክ በዚህ ዘመን የኢትዮጵያ ዳኝነትን ነፍስ እንዲዘራ አድርጎታል ማለት ይቻላል።

በሀገር ውስጥ ውድድር በራሳቸው ዳኛ ገለልተኝነት የተጠራጠረው የቱኒዚያ ፌዴሬሽን በኤስፔራንስ እና ኤቶል ዱ ሳህል መካከል የተደረገውን ጨዋታ ተጋብዞ ማጫወቱ ይታወቃል። ለብዙዎች ወደፊት ዳኛ ለመሆን ለሚያስቡ ወጣቶች ተምሳሌት መሆንም የቻለው በዓምላክ የካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ፣ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ፍፃሜ ፣ የካፍ ሱፐር ካፕ፣ የአፍሪካ ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች ከመራቸው ትልልቅ ውድድሮች መካከል ይጠቀሳል። ከሥዩም ታረቀኝ (1970) እና ተስፋዬ ገ/ኢየሱስ (1978) ቀጥሎ በ2018 በሩሲያ በተዘጋጀው የዓለም ዋንጫ ከኢትዮጵያ የተመረጠ ዳኛ በመሆን ከፍተኛ ልምድ አግኝቶ ተመልሷል። በዓለም ዋንጫ ሀገሩን በመወከሉ የተሰማውን ስሜት እና ስለነበረው ቆይታ፣ እንዲሁም በአራተኛ ዳኝነት ስለተሳተፈበት የኮስታሪካ እና ሰርቢያ ጨዋታ በትውስታ አምዳችን እንዲህ አጫውቶናል።

“አስታውሳለው በዓለም ዋንጫ እንደተመረጥኩ መረጃውን ከሚዲያ ሰምቶ አንድ ወዳጄ ነው የነገረኝ። ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታን ልዳኝ ጅማ ነበርኩ። ጨዋታው አልቆ ከሙያ ባልደረቦቼ ጋር ሆኜ ነው የሰማሁት። ስሜቱ በጣም ከባድ ነው። ጅማ እና እኔ ሁልጊዜ ትልቅ የማይረሳ ትውስታ አለን። በህይወቴ ውስጥ ትልቁ ነገር ከሰማሁባቸው ነገሮች አንደኛው ነው ማለት እችላለው። ወደ ሩሲያ ሄጄ የተሰጠኝ ሚና የተጠባባቂ ዳኝነት ነበር። ተጠባባቂ ዳኛ መሆን በዚህ ሰዓት ከፍተኛ ኃላፊነት ያለበት ነው። የኮስታሪካ እና የሰርቢያ ጨዋታ አስገራሚ ክሰተት ነው የተፈጠረው። የተሰጠኝን ኃላፊነት እየተወጣው ባለሁበት ሰዓት አንድ የሰርቢያ ተጫዋች (ኔማንያ ማቲች) እና የኮስታሪካ ም/አሰልጣኝ (ሊዊስ ማሪን) ጥሩ ያልሆነ ስሜት ውስጥ እንደሆኑ ተረድቼ፤ ጨዋታው ደግሞ ከፍተኛ ፉክክር የነበረበት ስለሆነ በመሐል ላይ በመግባት የማግባባት ሥራ ሠርቼ ከፍተኛ ጠብ እንዳይፈጠር ያቅሜን አድርጌያለሁ። ይህን በማድረጌ የባሰ ነገር እንዳይከሰት አስቀድሜ መቆጣጠር ችያለው። ያንን የመከላከል ስራ ባንሰራ ኖሮ ቀይ ካርድ የሚያዩ ተጫዋቾች እና የአሰልጣኞች ቡድን አባላት ይኖሩ ነበር። በዚህ አጋጣሚ የፊፋው ፕሬዝደንት ይሄን ጨዋታ ይመለከቱ ነበር። መልበሻ ክፍል ድረስ በመምጣት የማስታወሻ ፎቶ ተነስተናል። የሰራነው ስራ መልካም እንደነበረ፤ በፍጥነት ነገሩን ባንቆጣጠረው ከዚህ በላይ በመጥፎ ሁኔታ ይጠናቀቅ እንደነበረ ደስታቸውን ገልፀውልናል። እኔም የዚህ ታሪክ አባል በመሆኔ ሁሌም ሳስበው ደሰተኛ ነኝ። ”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ