1977 እና እግርኳሳችን – በኤርሚያስ ብርሀነ

ዛሬም ትዝታዬን ይዤ መጥቻለሁ። ከዚህ ቀደም እንዳልኳችሁ “ጉምቱ” ፀሃፊ አይደለሁም፡፡ ከሥነ-ጽሁፍ ዘርፍ ስጦታውንም፣ ችሎታውንም የታደልኩኝ እንዳልሆንኩ አስባለሁ። በቃ-እኔ የምፅፈው የራሴን ትውስታ ብቻ ነው። ማንንም መጥቀም አልያም መጉዳት፥ አንዱን ማግዘፍ ወይም ሌላውን ማሳነስ አላማዬ አይደለም። ወደኋላ የመመለስ፣ የማሰላሰልና የመጻፍ ጊዜ አግኝቻለሁ፡፡ ስለዚህም ደስ እያለኝ ያሳለፍኩትን ያን ዘመን አስባለሁ፤ ከልጅነቴና ወጣትነቴ ጋር የተቆራኘውን የሃገሬን እግርኳስ አወሳለሁ- ይኸው ነው፡፡

ለማስታወስ የምጥረው ከሰላሣ ዓመታት በፊት የተከሰቱ እግርኳሳዊ ኹነቶችን ስለሆነ አንዳንዴ የተፈጠሩ ክስተቶችን ልደባልቅ እችላለሁ፤ በትረካዬ ውስጥ የጊዜ፣ የባለድርሻዎች ሥም፣ የሁኔታዎች ቅደም ተከተልና ሌሎችም ሥህተቶች ይኖሩ ይሆናል- ለመታረም ዝግጁ ነኝ፡፡ የዘነጋኋቸው ነገሮች ካሉም አስታዋሽ አካል ይሞላልኛል የሚል ዕምነት አለኝ። ለምሳሌ፦ ባለፈው ፅሁፌ ላይ ብሄራዊ ቡድናችን ለ13ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት ሶቪየት ህብረት እንደሄደ  ገልጬ ነበር። ይሁን እንጂ በወቅቱ የቡድኑ አባል የነበረው ተፈራ ገብረክርስቶስ ወዲያው አርሞኛል። ያኔ ብሔራዊ ቡድናችን ዝግጅቱን ያደረገው በምስራቅ ጀርመን ነበር፡፡ ሌሎቻችሁም እንዲሁ ገንቢ አስተያየታችሁን ለግሳችሁኛል፤ በጎደለውም ሞልታችኋል – እጅግ በጣም አመሰግናለሁ፡፡

ቀጥዬ የዛሬው ትዝታዬን እነሆ እላለሁ፦

1977 ዓ.ምን በበርካታ ጉዳዮች አስታውሰዋለሁ፡፡  በዚህ ዓመት የኢሠፓ (የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ) ተመሥርቷል፤ አስረኛው የአብዮት በዓል ደምቆ ተከብሯል፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ደግሞ “ድርቅ ተከሰተ፤ ረሃብ ገባ፤ አገራችን ችግር ላይ ነች፡፡” የሚሉ አስደንጋጭ ዜናዎች ተሰምተዋል። ጤፍ ጠፍቶና ተወዶም ስንኞች ተቋጥረዋል፡፡
”          ልመደው ሆዴ፣
           ሩዙን ብላው በዘዴ፣
           ተወዷል ጤፍና ስንዴ።
የተወዳጁ ንዋይ ደበበ “የጥቅምት አበባ” እና ሌሎች ዘፈኖቹ በከተማው ውስጥ በሁሉም ቦታዎች እንደጉድ ተሰምተዋል፡፡ በራሴ በኩልም የማልዘነጋቸው የህይወት አጋጣሚዎች ተከስተዋል፡፡ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና (ማትሪክ) ተፈታኝ የነበርኩት በ1977 ነው፡፡ ይህ ዓመት ከጉርምስና ጋር በተያያዘ ችግር ውስጥ የገባሁበት ወቅትም ነበር፡፡

ወደ ኳሳችን ስንመጣ ደግሞ፦

ብሔራዊ ቡድናችን ዓመቱን የጀመረው በአሳዛኝ ሽንፈት ነበር። ከሃገር ውጪ ከኬንያ በጥሩ ውጤት ተመልሶ አዲሰ አበባ ላይ 2-0 እየመራ ደጋፊዎች  “ማን ይሆን የሚቀጥለው ተጋጣሚያችን?” እያልን ስናስብ ነገሮች በቅጽበት የተገላቢጦሽ ሆኑ፡፡ ኬንያዎች ሦስት አግብተውብን በገዛ ሜዳችን ላይ 3-2 ተሸነፍን፤ በዚህም እጅግ በሚያስከፋ ሁኔታ  ከውድድሩ ተሰናበትን።

ለቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድንና ደጋፊዎቹ ደግሞ 1977 መልካም ዓመት ነበር፡፡ ከዚያ ቀደም ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ሁለተኛ ዲቪዥን ወርዶ ለአንድ አመት ያህል በቫርኔሮ እና ሌሎች ሜዳዎች ሲጫወት ከርሞ ወደ አንደኛ ዲቪዥን ተመለሰ፡፡ ስለዚህም ደጋፊዎቹ የሚወዱት ቡድናቸው በአዲስ አበባ ስታዲየም ሲጫወት የሚያዩበት ጊዜ ሆነ፡፡ በዚህም ሳቢያ የዓመቱን ውድድር መጀመር በናፍቆት ጠበቁት።

(በዚህ አጋጣሚ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ1971 ዓ.ም ፈርሶ በ1975 ዓ.ም እንደገና ሲቋቋም ከባዱንና ዋናውን መስዋዕትነት የከፈለውን እሸቱ ቀጭኑ ነው፡፡ እሸቱ የሰራውን ያህል ባይነገርለትም ለቅዱስ ጊዮርጊስ የወቅቱ የዲቪዚዮን እድገት ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል። እኔም ይህን ባለውለታ በትንሹ ለማንሳት እወዳለሁ፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ አንደኛ ዲቪዥን መመለስ ለእሸቱ ቀጭኑ ትልቅ ድል ነበር። እሸቱ የአንጋፋው ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ብቻ ሳይሆን የሃገራችን እግርኳስም ታላቅ ባለውለታ ነው። ታሪካዊ ስራውን ሁሌም እናስታውሰዋለን፡፡ እግዚአብሄር ነፍሱን በገነት ያሳርፍ፡፡)

የ1977 ዓ.ም የውድድር ዓመት ሲጀመር ቅዱስ ጊዮርጊስ የመጀመሪያ ግጥሚያውን ከብዙ ዓመት ተፎካካሪው ምድር ጦር ጋር ሊያደርግ ወደ ሜዳ ሲገባ የህዝቡ አቀባበል ልዩ ነበር። የምድር ጦር ደጋፊዎች
        የመቻል አበባ-አበባ፣
                    ኧኸ!
        እልል ብዬ ልግባ፡፡
        የጦሩ አበባ-አበባ፣
                    ኧኸ!
        እልል ብዬ ልግባ፡፡
እያሉ ጠንካራ ቡድናቸውን ሲቀበሉ ፥ በክለባቸው ወደ አንደኛ ዲቪዥን መመለስ ብቻ ሳይሆን በቡድናቸው ውስጥ ዳኛቸው ደምሴን፣ ሙሉጌታ ከበደን እና ገብረመድህን ኃይሌን የመሳሰሰሉ ክዋክብትን የያዙት የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ደግሞ በጭብጨባና በዘፈን ቡድናቸውን ሲያጅቡ ስታዲየሙ በአንድ እግሩ ቆመ። ጨዋታው እንደተጀመረ በአዲስ መልክ የተደራጁት ጊዮርጊሶች በፍፁም የሚቻሉ አልሆኑም። ዳኛቸው የኋላውን መስመር በብቃት ሲመራው ከፊት ደግሞ የገብረመድህን፣ የሉቾ እና የሙሉጌታ ጥምረት አስገራሚ ነበር። ቅብብላቸው ብዙ ዓመት አብረው የተጫወቱ እንጂ በጥቂት ወራት የተሰባሰቡም አላስመሰላቸውም። በግሩም አጨዋወታቸው ሦስት ጎል አግብተውና ታሪካዊ ተቀናቃኛቸው ምድር ጦር ደግሞ አንድ ጎል አግብቶ የመጀመሪያው ግማሽ በቅዱስ ጊዮርጊስ 3-1 መሪነት ተጠናቀቀ። የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የመክፈቻ ጨዋታ ነበርና ፌዴሬሽኑ ልዩ ዝግጅት አድርጎ ነበር፡፡ በእረፍት ሰዓት ተወዳጁ ታማኝ በየነ ህዝቡን ሊያዝናና ወደ ሜዳ ገባ። በቀልዱ አብዛኛውን የስታዲየም ተመልካች እጅጉን እየሳቀና እያዝናና ቢቀጥልም በስታዲየሙ አንደኛው ክፍል ግን የሚታየው የመዝናናትና የመሳቅ ሁኔታ እምብዛም ነበር። እንዲያውም ፀጥ-ረጭ ያለ ድባብ ተላብሷል። ይህም ቦታ በተለምዶ የሚስማር ተራ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ ነው። እንደሚታወቀው ሚስማር ተራ የምድር ጦር ደጋፊዎች የሚቀመጡበት ስፍራ ነበር። የዝምታቸውም ምክንያት የቡድናቸው በቅዱስ ጊዮርጊስ በሰፊ ጎል መመራት እንደነበረ ግልጽ ነው። ይሄ ጉዳይ የገባው ፈጣኑና ብልሁ ታማኝም ፊቱን ወደ እነርሱ በማዞር “የኳስና የፍቅር ውጤቱ ቀድሞ አይታወቅም።” በማለት የሚከተለውን ስንኝ አስከተለላቸው፡፡
“የኳስ ውጤቱ ቀድሞ የሚታወቅ ቢሆን ኖሮ፣
      ኢትዮጵያ ኬንያን ባሸነፈች ሁለት-ለ-ዜሮ፡፡”

በማለት ቡድናችን ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሀለት ጎሎች ልዩነት እየመራ በመጨረሻም በኬንያ የተሸነፈበትን አጋጣሚ ሊያስታውሳቸው ሞከረ፡፡ ይህን ጊዜ ዝም ብለው የነበሩት አንበሶቹ የምድር ጦር ደጋፊዎች ድምቅ ባለ ሁኔታ ለታማኝ በየነ  አድናቆታቸውን ከገለፁ በኋላ “አማሬሳ!” በሚለው ዘፈን ቡድናቸው ከመልበሻ ቤት ሲወጣ ሞቅ አድርገው ተቀበሉት።
              አማሬሳ ኦኦአ፣
              አማሬሳ ኦኦኦ፣
              ሳንጃ ምድር ጦር ነመኛታ፣
               ኦፋን ነመኛታ፡፡
እያሉ ስታዲዮሙ የሚፈርስ እስኪመስል ድረስ ጨፈሩ። በመሃልም
           “ጦሩ ከነ አርማው፣
            በጨዋታ ድል አለው።”
የሚለውንም እያከሉ
           “እልል በይ ወፌ፤ እልል በይ አሞራ” የምትለውን ዘፈናቸውን እየዘፈኑ ለቡድናቸው ብርታት ሆኑ። ፍልሚያው በአስገራሚ ሁኔታ 4-4 ተጠናቀቀ። “ብዙ ይገባበታል፡፡” የተባለው ምድር ጦር ከኋላ ተነስቶ ጨዋታውን በአቻ ውጤት መጨረሱ እንደ ተዓምር ታየ።

የዚያን ቀን የሚከተሉትን ነገሮች ታዘብን። የቅዱስ ጊዮርጊሰ ደጋፊዎች ቡድናቸው በሰፊ ጎል መርቶ የማታ-ማታ ጨዋታውን አቻ ቢጨርስም በቡድናቸው አቋም ተደስተው ወደ ቤታቸው ሄዱ። ያ የጥንቱ ኃያል ቡድን ቅዱስ ጊዮርጊስ እየተመለሰ እንደሆነም ምልክት ታየ፡፡ የሆነውም ይኸው ነበር። ቅዱስ ጊዮርጊሰ በውድድር ዓመቱ የተዘጋጁትን ዋንጫዎች በሙሉ ጠራርጎ ወሰደ፡፡

በምድር ጦር ቡድን በኩል ደግሞ ምንም እንኳ በከፍተኛ የጎል ልዩነት ተመርቶና የጨዋታ የበላይነት ቢወሰድበትም የመጨረሻ ፊሽካ እስኪነፋ ድረስ ተጫውቶ ውጤት ይዞ ከሜዳ የመውጣት ብቃት እንዳለው ተመለከትን። የምድር ጦር ደጋፊዎች ደግሞ የቡድናቸው አንቀሳቃሽ ሞተር መሆናቸውንም አሳዩ፡፡ ቡድናቸውን ለማነሳሳት በምን ሰዓት-የቱን ዘፈን ዘፍነው የቡድናቸውን ጥንካሬ ማውጣት እንደሚችሉና ቡድናቸውንም ባለውጤት ማድረግ እንደሚችሉ አመላከቱ።

አርቲስት ታማኝ በየነ ደግሞ ማንን፣ መቼ፣ በምን እንደሚያዝናና የማወቅ ብቃቱ፣ ማንንም ሳያሰከፋ፣ ሁሉን አስደስቶ፣ ሁለን አስቆ፣ በሁሉ ተመስግኖ፣ በሁሉ ተወዶ የመሄድ ስጦታውን እና ችሎታውን በአይናችን አይተን-መሰከርን። እኔ በዚያን ቀን የሁለቱም ቡድን ደጋፊ ባልሆንም በማየው ድባብ በጣም እየተደሰትኩ አመሸሁ፤ በአንድ ሁኔታ ደግሞ የበለጠ እርካታ አገኘሁ። በቅዱስ ጊዮርጊስ ጠንክሮ ወደ አንደኛ ዲቪዚዮን መመለስ ደስ ብሎኝ ነበር፡፡ የተደሰትኩትም ለአንድ ሰው ነበር፡፡ እርሱም ምርጡ የሰፈራችን የለገሃር ልጅ ሰሎሞን መኮንን (ሉቾ) ነው፡፡ ሉቾ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ1975 ዓ.ም ወደ ሁለተኛ ዲቪዥን ሲወርድ ሌሎች ክለቦች በከፍተኛ ገንዘብ ወደእነርሱ ሊያዛውሩት ቢሞክሩም “ያደኩበት ክለቤን አለቅም፡፡” ብሎ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አብሮ ወርዶ፣ በሁለተኛ ዲቪዥን ውድድር በየቦታው ዞሮ ተጫውቶ፣ ከቡድን ጓደኞቹ ጋር ቅዱስ ጊዮርጊስን ወደ አንደኛ ዲቪዥን አሳደገ፡፡  በተጨማሪ ደግሞ በመክፈቻው ፍልሚያ ከጦሩ ጋር ሲጫወቱ አዲስ ከመጡት ክዋክብቶች ጋር ወዲያው ተግባብቶ፣ ምርጥ ብቃት አሳይቶና ጎልም አግብቶ ሲደሰት ስላየሁት እጅጉን ደስ አለኝ፡፡ ሉቾን ሁሉም ይወደዋል፤ የለገሃር ልጅ ደግሞ አብልጦ ይወደዋል፡፡ ችሎታ ኖሮን ማሊያ መምረጥ እንኳን ሲፈቀድልን የሉቾ 14-ቁጥር  የብዙዎቻችን ምርጫ ነበር፡፡ ሉቾ የለገሃር ኩራት! ሰሎሞን መኮንን (ሉቾ) ሁሌም እንወድሃለን! ሁሌም እንኮራብሃልን!

በአንድ ቀን፣ በአንድ ጨዋታ፣ አንድ ስታዲዮም ውስጥ ይሄንን ሁሉ ክስተት ማየት የሚታሰብ አልነበረም። እኛ ግን የዚያን ቀን ይሄን ሁሉ ነገር ተመለከትን። ተደስተንም ቤታችን ገባን። ለዚያም ነው ይኸው ከሰላሣ አምስት ዓመታት በኋላም እንደዚህ ደስ ብሎኝ የማወራው!

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ