” ወደ ፊት ሀገሬ በመምጣት በስልጠናው ላይ የመስራት ዕቅድ አለኝ ” ስንታየሁ ጌታቸው (ቆጬ)

ከዘጠናዎቹ መጀመርያ አንስቶ በኢትዮጵያ እግርኳስ ስማቸው ቀድሞ ከሚነሱ ድንቅ አጥቂዎች መካከል አንዱ የሆነው ስንታየው (ቆጬ) ከሀገር ከወጣ ከረዥም ዓመታት በኃላ ሶከር ኢትዮጵያ አግኝታው አናግራዋለች።

የቀድሞ የአርባምንጭ ጨርቃጨርቅ ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በራሪው አጥቂ ስንታየሁ (ቆጬ) ከአስራ ስድስት ዓመት በኃላ ከሚኖርበት እንግሊዝ ሀገር አግኝተነዋል። በቀጣይ ጥቂት ቀናት ውስጥ ስለ እርሱ አጠቃላይ በእግር ኳስ ህይወቱ ዙርያ ዘገባዎችን ይዘን እንደምንቀርብ ከወዲሁ እየጠቆምን ለዛሬ ወደ ሀገሩ በኢትዮጵያ በመምጣት ለማሰልጠን እና ያለውን ልምድ ለማካፈል ሀሳብ ያለው መሆኑን አስመልክቶ የሰጠንን ሀሳብ ይዘን ቀርበናል።

” ከሀገሬ ከወጣው ረዥም ዓመት ሆኖኛል። እዚህ ሀገር ከመጣው ከእግር ኳሱ አልራቅኩም የተለያዩ ኮርሶችን ወስጃለው ፤ እየወሰድኩም እገኛለው። ወደ ሀገሬ ከአንድ ዓመት በኃላ የመመለስ ዕቅድም አለኝ። ከመጣው ደግሞ በእግር ኳሱ ብዙ ነገሮችን መስራት እፈልጋለው። መቼም በተዓምር ከእግር ኳሱ ልለይ አልችልም። እንደመጣው አንዳንድ ነገሮች ማድረግ እፈልጋለው። መጀመርያ ግን እዚህ ሀገር ጥናቶችን እያጠናው ኮርሶችን እየወሰድኩ ነው። የወሰድኩት የስልጠና ደረጃም ከፍ ያለ ነው። በአውሮፓ እና በአለሁበት እንግሊዝ ሀገር ማሰልጠን የምችልበት ኮርስ ነው። ዓላማዬ እኔ ያላገኘሁትን ዕድል የሀገሬ ተጫዋቾች እንዲያገኙ ማድረግ ነው። ምክንያቱም እኔ በአውሮፓ ደረጃ የመጫወት ህልምና ምኞቱ ነበረኝ ፤ ሆኖም አልተሳካልኝም። ነገር ግን ሀገሬ ያሉ ታዳጊዎች እንዲሁም ዋናው ፣ ወጣቱ እና ታዳጊ ብሔራዊ ቡድኑ ደረጃውን የጠበቀ ስልጠና እንዲያገኝ እና በዓለም አቀፍ መድረክ ተሳታፊ የሆነ ቡድን እንዲኖረን እፈልጋለው። የሀገራችን ህዝብ ለእግር ኳስ ያለው ፍቅር ከፍተኛ እንደሆነ ይታወቃል። የእኔም ከፍተኛ ምኞት ሀገሬን ለዓለም ዋንጫ ማብቃት ነው። ተስፋ አለኝ ከፈጣሪ ጋር እዚህ ደረጃ እንድንደርስ የምችለውን ነገር ሁሉ አደርጋለው። ሀገሬም ካሉ የቀድሞ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ጋር በመተባበር ይህን ማድረግ ነው ምኞቴ።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ