ግንባታው ከተጀመረ ዘጠኝ ዓመታትን ያስቆጠረው የሀዋሳ ዓለም አቀፍ ስታዲየም በተለያዩ ምክንያቶች እየተጓተተ ለምን እስካሁን መጠናቀቅ አልቻለም?
በ2004 ግንባታው የተጀመረውና ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ ከ45-50 ሺህ ተመልካቾችን በወንበር እንደሚያስተናግድ የተነገረለት ስታዲየሙ በአራት ዓመታት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ቢጠበቅም በተለያዩ ምክንያቶች እየተጓተተ ዓመታት ተቆጥረው እስካሁን መጠናቀቅ አልቻለም፡፡ በ2008 ለመላው ኢትዮጵያ ውድድሮች ሲባል አፋጣኝ ሥራዎችን ሲከወን የነበረው የዚህ ስታዲየም ፕሮጀክት ከውድድሩ በኋላ ግን ያዘገመ ሥራዎች እየተሰሩበት አሁን ላይ “ቆሟል” የሚባልበት ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
ሳትኮም በተባለ የኮንስትራክሽን ተቋራጭ ሲሰራ የቆየው ስታዲየሙ ባልተጠናቀቀበት ሁኔታ ከሀገር አቀፍ ስፖርታዊ ጨዋታዎች አንስቶ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወላይታ ድቻ ክለቦች አህጉራዊ ውድድሮች ግልጋሎት ሰጥቷል። ስታዲየሙ በውድድር ወቅት በተለይ እንደ ችግር የሚነሳበት የመጫወቻ ሳሩን የመቀየር ሥራ በስድስት ወራት ውስጥ ተፈፃሚ ይሆናል ተብሎ ቢጠበቅም ወቅቱን መጠበቅ ሳይችል ይኸው ድፍን ሁለት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የመብራት (ፓውዛ)፣ ስክሪን ገጠማ፣ የሚዲያ ክፍል፣ የመልበሻ፣ የውስጥ ማማሟቂያ እና መፀዳጃ ቤቶች የተሰሩለት ቢሆንም የወንበር፣ የተጠባባቂ ተጫዋቾች መቀመጫ፣ ጥላ፣ መጠነኛ ማሻሻያን የሚሹ የዲዛይን ሥራዎች እንዲሁም የፊኒሺንግ ሥራዎች ይጠብቁታል። ከዚህም በተጨማሪ ከሜዳው ውጪ የሚገኙ ሁለት የእግር ኳስ መለማመጃ ሜዳዎች እና በዲዛይኑ ላይ የተካተቱ የሌሎች ስፖርቶች ማከናወኛ ግንባታዎች ከዚህ ቀደም በጥንድፊያ የተሰሩ በመሆናቸው በዲዛይኑ መሠረት መጠናቀቅ ይጠበቅባቸዋል።
የደቡብ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ የሺዋስ ዓለሙ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ስታዲየሙ አሁን ያለበት ሁኔታ እና እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችን በዚህ መልኩ አስረድተዋል።
“በመጀመሪያው ዙር ግንባታ በአመዛኙ ትልቁ ስታዲየም መሠረታዊ ሥራዎች እያለቁ ነው። ችግር የነበረበት የሳር ንጣፉ አሁን እየተስተካከለ ነው። ከዛ ውጪ ያለው የቴክኖሎጂ ገጠማው ነው፤ እሱ የኮንስትራክሽን ድርጅቱ ሳትኮም ያመጣው የውጪ ድርጅት ጋር በመሆን አብዛኛዎቹን የቴክኖሎጂ ሥራዎችን ጨርሷቸዋል፡፡ ባለፈው ህዳር እና ታኅሣሥ ላይ የቴክኖሎጂ ገጠማ ሥራው ተሰርቷል፡፡ በሁለተኛ ምዕራፍ የተያዘው የጣራ እና የወንበር ሥራ ነው የሚቀረው። እሱ በኮንትራክተሩ እና በክልላችን ኮንስትራክሽን ቢሮ አማካኝነት አዲስ የተሰራ ዲዛይን ስላለ ዲዛይኑ ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ተብሎ የማሻሻያ ሥራው እየተሰራ ነው። ይህ የዋናውን የስታዲየም ገፅታ የተመለከተ ጉዳይ ነው።
“ከዚህ ጋር ተያይዞ ካፍ በተደጋጋሚ የሰጣቸው ኮመንቶች አሉ። በተሰጡን ኮመንቶች መሠረት ከማስተካከል አኳያ አንዳንዶቹ ከመጡት ገምጋሚ ቡድን ጋር ካለ የመረጃ ልውውጥ ችግር ጋር የተያያዘ ነው። ያ ደግሞ ሰነዶች ከታዩ በኃላ ለማስተካከል ተሞክሯል፡፡ የሚቀሩ ክፍሎችን የማደስ መሠረታዊ የሆኑ ሀሳቦች ቀርበዋል። የመጫወቻ ሜዳ፣ የመልበሻ ክፍል፣ የውስጥ ማማሟቂያን በተመለከተ በአመዛኙ በተሰጡት አስተያየቶች መሠረት ለማስተካከል ተችሏል፡፡ ከዋናው ስታዲየም ጋር በተጓዳኝ የማስፋፊያ ሥራዎች ደግሞ አሉ። የመለማመጃ ሜዳ፣ ትንንሽ ሜዳዎች (እንደ ቅርጫት ኳስ ሜዳ እና መሰሎች)፣ ውሀ መዋኛ እና ሌሎች ቀሪ ሥራዎች አሉ። ”
ኮሚሽነሩ ሥለ ግንባታው በጊዜው አለመጓዝ ላነሳንላቸው ጥያቄ ማብራሪያቸውን በመቀጠል የበጀት፣ የኮሚቴ መቀያየር፣ ከተቋራጮች ጋር አለመግባባት፣ የፀጥታ ሁኔታ እና ኮሮና ወረርሺኝ ለፕሮጀክቱ መጓተት ምክንያት መሆናቸውን ገልፀዋል።
“ሥራውን ከያዘው የኮንስትራክሽን ድርጅት ጋር አለመግባባት እየተፈጠረ በመሆኑ በአማካሪው እና በአሰሪ ቢሮው በኩልም ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት ነበር፤ ነገር ግን ውጤታማ ባለመሆኑ እያነሳ ያለውም ጥያቄ በአሰራር ደረጃ የማይመለስ በመሆኑ ውሉን ለማቋረጥ እንቅስቃሴ ላይ ነን። የማስፋፊያ ሥራውን የሚሰራው ‘በረከት እንደሻው’ የሚባል ድርጅት ጋር ከ2008 ጀምሮ (የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ጀምሮ) ሲሰራ የነበረ ድርጅት ነው። የሚጠይቃቸው ጥያቄዎችን ከተገባው ውል አንፃር ሊመለሱ የማይችሉ ከመሆኑ ባለፈ ያለፉትን 18 ወራት ሥራ ላይም ስላልነበረ ተገምግሞ የመጨረሻ ውሳኔ ላይ እየተደረሰ ነው ያለው፡፡
” ከተቋራጩ በተጨማሪ ፕሮጀክቱን የሚከታተለው ኮሚቴ በየጊዜው መለዋወጥ ሥራውን አስቸጋሪ አድርጎታል። ‘የሀዋሳ ስታዲየም የህዝብ ተሳትፎ እና አስተዳደር’ የሚባል ኮሚቴ አለ። እዚህ ክልል በነበረው የአመራር መለዋወጥ እና ሽግሽግ በአብዛኛውም ሥራ አስፈፃሚ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩም በአጠቃላይ አሁን ስለሌሉ ያን የመተካት ጉዳይ ከክልሉ ባህልና ቱሪዝም እና ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጋር ተነጋግሮ የፈረሰውን ቦርድ መልሶ ለመሰየም እና ለማቋቋም እንቅስቃሴ ላይ ነው ያለነው።
” ከዚህ ጎን ለጎን በሁለተኛው ምዕራፍ የሚካተቱ የፊኒሽንግ እና ብዙ ወጪ የሚያስወጣው የጣሪያ፣ የወንበር እንዲሁም ዙሪያ አጥር ግንባታ ለመስራት ባለፈው ክረምት ጨረታ ወጥቶ ነበር። ሆኖም የወጣውን የሚያሟላ አካል ስላልነበር፣ ለዛ የሚረዳ በቂ በጀትም ስላልነበረ በቴክኒክ ውድቅ ተደርጎ ተጨማሪ በጀት ወጥቶ በድጋሚ ጨረታ ለማውጣት ከ200 እስከ 250 ሚሊዮን ያስፈልጋል የሚል መመሪያ ስላለ ያን ለማድረግ በሒደት ላይ ነው ያለነው። ትልቅ ሀገር አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ውድድሮች ሲያስተናግድ የነበረ ሜዳ ቢሆንም በተጠበቀው ልክ ባለፉት ሁለት ዓመታት ሥራ አልተሰራም። ለሥራው የክልሉ መንግሥት በጀት በአግባቡ ሲበጅት ቢቆይም በነበረው የፀጥታ ችግር ጥቅም ላይ ማዋል አልተቻለም። በዚህ ዓመት ለመከናወን ሲታሰብ ደግሞ ለግንባታው የተያዙ አብዛኛው ወጪዎች ወደ ኮሮና ስለዞሩ የበጀት እጥረት አጋጥሟል።
“የሳር መቀየር ሥራው እንደተባለው መከናወን ከነበረበት ጊዜ አንፃር በጣም ቆይቷል። ወደ መቀየሩ ሒደት ዘንድሮ ነው የተገባው። ግን ችግሩን በጥልቀት ገምግሞ ከማቅረብ አንፃር መዘግየቶች ነበሩ፡፡ አብዛኛው የሜዳውን ስራ የሚይዘው ይሄን ሳር የመቀየር ነው፡፡ ሳሩን ለመቀየርም በዝርዝር ነው እየተገመገመ የሄደው ለዚህ የሚመች ደረጃው የጠበቀ ኮረት የማስተካከል አፈሩን የማጠብ የፍሳሽ ሥርዓቱን የማስተካከል ጉዳይ አሁን በሚገባ እየሄደ ነው ያለው። ከኮንትራክተሩ ጋር የነበረን ውል በዚህ ሚያዚያ ወር ላይ የሚያልቅ የነበረ በመሆኑ በፍጥነት ነው ሲሰራ የነበረው። አሁን ላይ ያለበት ሁኔታ ጥሩ ነው። ያው የዘገየበት ሁኔታ የአስፈፃሚ አካላት መጓተት አመራሩ በፍጥነት መመሪያ ያለመስጠት ያመጣው ችግር ቢሆንም ዘንድሮ ያን ለማስተካከል ተሞክሯል፡፡ የሳር ንጣፉ በአምስት ወር ለመጨረስ ነው ስምምነት ላይ የተደረሰው። ጥሩ እየሄደ ከኮሮና መምጣት ጋር በተያያዘ ግን ዘግይቷል፡፡ አሁን ግን በፍጥነት ተመልሶ ወደ ስራ እንዲገባ መግባባት ላይ ስለተደረሰ በሁለት ወር የመጨረስ ስራ ላይ እንገኛለን። ችግሩ ተከስቷል፤ ለማስተካከልም ተዘግይቷል። ያም ቢሆን በአጭር ጊዜ ይጠናቀቃል፡፡ ”
ስታዲየሙ መቼ እንደሚናቀቅ እና ቀጣይ ሥራዎች በምን መልኩ እንደሚካሄዱ ግልፅ መረጃ ማግኘት አዳጋች ሲሆን ካለው የሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር በቂ የማጠናቀቂያ በጀት የማግኘቱ ጉዳይ አጠያያቂ ሆኖበታል። በጉዳዩ ላይም ለስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነሩ ጥያቄውን አንስተን ስታዲየሙን ለማጠናቀቅ እየሄዱ ስላሉበት መንገድ እና እቅድ የሚከተለውን ብለውናል።
” ከዋናው ስታዲየም ጋር በምዕራፍ ሁለት መካተት ያለበት የጣሪያ እና የወንበር ሥራ የራሱ የሆነ በጀት ስለሚፈልግ ከመስተዳድር ምክር ቤት እና ከክልሉ ምክር ቤት ጋር ተነጋግሮ ማስመደብ፤ በመቀጠል ባለፉት ሁለት ዓመታት የዘገየውን ስታዲየም በምን አይነት መልኩ እናፋጥነው የሚለው ጉዳይ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተነጋግረን አዲስ ቦርድም ተቋቁሞ ይሄን በበላይነት የሚመራውን ዳግም ለመመለስ በሒደት ላይ ነን።
“እንደ ኮሚሽን የመጀመሪያው ምዕራፍ ዘንድሮ መጠናቀቅ አለበት የሚል አቋም ነው የያዝነው። በመጀመሪያው ዙር ቅድም ያልኩት የመጫወቻ ሳሩ ያልቃል፣ የቴክኖሎጂ ገጠማው ያልቃል፣ በዚህ ዙር ተጨማሪ ኮንትራት የተሰጡ የውጪ የማስፋፊያ በአመዛኙ ብዙዎቹ አልቀው የተወሰኑት በኮንትራክተሩ በተፈጠረው ችግሮች የተቋረጡ ቢኖሩም የተሰሩ ሥራዎች ግን አሉ፡፡ ከማስፋፊያ ስራዎች አንፃር 86% ተሰርቷል፡፡ በትልቁ ስታዲየምም ላይ መሰራት ካለበት መሀከል 96% ተሰርቷል፡፡ የማስተካከል እና የለቀማ ስራዎች ሲቀሩ ይሄን ዘንድሮ ለመጨረስም ነው ያሰብነው። የአጥር ግንባታ እና የላንድ ስኬፒንግ ስራ በሚቀጥለው በጀት ዓመት አጋማሽ ላይ እንጨርሳለን የሚል ነው የኮሚሽኑ እቅድ። ”
እስከ አሁን 750 ሚሊዮን ብር ፈሰስ እንደተደረገበት የተነገረለት ስታዲየሙን ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ ለአዲስ የኮንስትራክሽን ተቋራጭ ጨረታ አውጥቶ በቀጣይ ሥራ የሚጠብቀው ሲሆን ዘንድሮ ወደ ሥራ ለመመለስ 20 ሚሊዮን ብር በጀት ቢመደብለትም በተለያዩ ምክንያቶች መንግስት ከዚህ በጀት ላይ 16 ሚሊዮን ብሩን ለሌላ ስራ አውሎታል ተብሏል፡፡ በቀጣይ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅም ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብን እንደሚጠይቅ ታውቋል።
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ