“የግብፅ በደል እና የዳኛው ቡጢ” ትውስታ በስንታየሁ ጌታቸው (ቆጬ)

ግብፅ በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ከፍተኛ በደል ፈፅማለች የሚለው ስንታየሁ (ቆጬ) በ1990 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ግብፅ አሌክሳንድሪያ ላይ ስለተፈፀመው ደባ እና የዳኛውን ቡጢ አስመልክቶ በትውስታ አምዳችን ይሄን ነግሮናል።

ወቅቱ 1989 ነበር፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ አስከፊ የውጤት ጉዞ ላይ ትገኛለች። ወደ ሞሮኮ ለጨዋታ በተደረገው ጉዞ በጠፉ በርካታ ተጫዋቾች ምክንያትም ብሔራዊ ቡድኑ ሳስቷል። ዋልያዎቹ በቡርኪና ፋሶ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የ1998 የአፍሪካ ዋንጫ አስቀድመው መውደቃቸውን ያረጋገጡ በመሆኑ የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈፃሚ አንድ ውሳኔ ይወስናል። ከወራት ቀደም ብሎ ቦትስዋና ላይ በተካሄደው የአፍሪካ ታዳጊዎች ዋንጫ አመርቂ ውጤት ይዞ የተመለሰው ቡድን ተስፋ ሰጪ ነገር ያሳየ በመሆኑ ተጫዋቾቹን ወደ ዋናው ቡድን በመጥራት የተወሰኑ ልምድ ያላቸውና በማጣርያውም ግቦች ማስቆጠር በቻሉት እንደነ አሰግድ ተስፋዬ እና ኤልያስ ጁሀር የመሳሰሉትን ቡድኑ ውስጥ በማካተት ለምድብ ማጣርያው የመጨረሻ ጨዋታ ግብፅን እንዲገጥሙ ወደ ካይሮ ለመላክ ከውሳኔ ላይ ደረሰ።

ሐምሌ 20 ቀን 1989 አሌክሳንድሪያ ላይ የተከናወነው ጨዋታ ለኢትዮጵያ ከመርሐ ግብር ማሟያነት ያለፈ ባይሆንም ግብፅ በወቅቱ 5 ነጥብ እና 1 ጎል ይዛ ከምድቧ 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣ የነበረ በመሆኑ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ይህን ጨዋታ የግድ አሸንፋ በ8 ነጥብ እና ሁለት ንፁህ ግብ ሁለተኛ ላይ የተቀመጠችው ሴኔጋል ደግሞ በሞሮኮ መሸነፍ ይኖርባታል። በዚህ ስሌት መሰረት አጣብቂኝ ውስጥ ገብታ ጨዋታውን ያደረገችው ግብፅ ኢትዮጵያን 8-1 በመርታት (ሞሮኮ ሴኔጋልን አሸንፋ) በሁለተኝነት ወደ አፍሪካ ዋንጫ ማምራት ችላለች። ድል እና ጎል አስፈላጊዋ የነበረው ግብፅ ካስመዘገበችው ድል ባሻገር አስገራሚው ክስተት የነበረው የዕለቱ ዳኛ በሚፈፅሙት በደል የተማረረው ስንታየሁ (ቆጬ) ዳኛውን አባሮ የደበደበበት እና ለወራት የተቀጣበት ክስተት ነው። የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ብሔራዊ ቡድን ድንቅ አጥቂ በዚህ ጉዳይ እንዲሁም ግብፅ ለዓመታት በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ስላደረሰችው ትልቅ በደል በዛሬው የትውስታ አምዳችን ያለፈውን ጊዜ መለስ ብሎ እንዲህ ያስታውሰናል።

” በጣም መናገር የምፈልገው ነገር ነው። በዐባይ ጉዳይ በተመለከተ ኢትዮጵያ ከግብፅ ጋር በእግርኳሱ ስትጫወት የምታሰልፈው ተጫዋቾቿን ሳይሆን የመከላከያ ሠራዊቷን ነው የሚል ፁሑፍ አንብቤ በጣም ደስ ብሎኝ ነበር። የዐባይ ግድብ መገደቡ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በጣም ደስተኛ ነኝ። ግብፅ ሁልጊዜ በእግርኳሱ ስታደርግብን የነበረውን በደል ስታስበው የፖለቲካ አመራሮቻችን ይህን የዐባይ ግድብ እዚህ ደረጃ ማድረሳቸው በጣም ደስተኛ ነኝ፣ አመሰግናቸዋለውም። ምክንያቱም ግብፅ እኛ ላይ በእግርኳሱ ያደረሰችው ግፍ ከፍተኛ ነው። የካፍ ፅህፈት ቤት ካይሮ መሆኑ፣ በየትኛውም የእድሜ እርከን በብሔራዊ ቡድን እንዲሁም በክለብ ደረጃ የምንመደበው ከግብፅ ነው። በዚህ ምክንያት በሜዳቸው የሚጫወቱትን ጨዋታ እንደሚያሸንፉ እርግጠኛ ናቸው። ይህ የሚሆነው ለምድነው አንደኛ የሚመደበውን ዳኛ ይገዙታል በሻንጣ ነው ብር የሚሰጡት። በጣም የሚገርምህ ግብፆች በ20 ደቂቃ ውስጥ ጎል ሳያገቡ ከቀሩ ይህን ወደ ኃላ መመልከት ይቻላል። በእርግጠኝነት ፍፁም ቅጣት ምት ያገኛሉ። ይህን የምናገረው ጋቦሮኒ ላይ ጥሩ ውጤት ስላመጣን ምክንያት ለማቅረብ አይደለም።

“ወደ ጨዋታው ልመልስህና ከጋቦሮኒ የመጣውን ቡድን እንዳለ ማለት ይቻላል። ሳንዘጋጅ ወደ ግብፅ እንድንሄድ ይነገረናል። እኛም ጨዋታውን ለማሸነፍ ከነበረን ከፍተኛ ፍላጎት አኳያ ስድስት አጥቂዎች ነበር ይዘን ወደ ሜዳ የገባነው። አሰግድ፣ ኤልያስ ጁሀር እኔ ሌሎችም አጥቂዎች ነበሩ። ሆኖም በዛን ወቅት ስምንት ጎል ሲገባብን ይገርምሀል ዳኛው ፍፁም ቅጣት ምት ዝም ብሎ ይሰጣል፣ ብድግ ብሎ እንደፈለገ ተጫዋች በቀይ ካርድ ያስወጣል፣ ግብፆች ጎል እያገቡ እንኳን ዳኛው የሚያደርገው ነገር በጣም የሚያናድድ ነው። ሄጄ የሚያደርገው ነገር ተገቢ አይደለም ብዬ ላናግረው ስል በቪዲዮ ማየት ይቻላል። ዳኛው ቀድሞ እኔን በቦክስ መታኝ፤ በቃ ከአቅሜ በላይ ሲሆን በጣም ተናድጄ ዳኛውን አባርሬ መታሁት። በዚህም ተቀጣሁ። በኃላ ላይ የጨዋታውን ቪዲዮውን አይተው ውሳኔያቸው ተገቢ ባለመሆኑ ቅጣቱን አንስተውልኛል። በአጠቃላይ ግብፅ በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ የፈፀመችው በደል ከፍተኛ ነው። ትልቅ በደል አድርሰውብናል። እንዴት አንድ ሀገር ሁልግዜ ከግብፅ ጋር ሊመደብ ይችላል። ሁልጊዜ ነበር ከግብፅ ጋር የምንመደበው! አንድ ጊዜ ከእርሷ ጋር ሳንመደብ ስንቀር ቡድናችን ለአፍሪካ ዋንጫ አለፈ። እና ለማለት የምፈልገው የዐባይ ግድብ እየተገደበ በመሆኑ በጣም ነው ደስ ያለኝ።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ