በሀገራችን ብሎም በተቀሩት ሀገራት ተለምዷዊ ዕይታ የመሐል ተከላካይ ሥፍራ ተጫዋች በተክለ ሰውነቱ ገዘፍ ያለ፣ በቁመቱ ረዝም ያለ እንዲሆን በሚታሰብበት ዘመን በቁመቱ አጭር በሰውነቱ ቀጠን ያለ ቢሆንም በአዕምሮው ፈጣን የነበረ አስደናቂ ተከላካይ ኢትዮጵያ ነበራት። የዘጠናዎቹ ኮከብ ሳሙኤል ደምሴ “ኩኩሻ”
በኢትዮጵያ ቡና ደምቆ የታየው ሳሙኤል ትውልድ እና ዕድገቱ አዲስ አበባ ጨርቆስ አካባቢ ሲሆን እንደማንኛውም ታዳጊ በሠፈር ውስጥ እግርኳስን በመጫወት ጀምሮ በኢትዮ ኤሌትሪክ የታዳጊዎች ቡድን (ሲ እና ቢ) መጫወት ችለሏል። በመቀጠል አየር ኃይል፣ ኒያላ፣ መድን ተጫውቷል። ትንሹ ልዑል ኩኩሻ በሁሉም ስፖርት አፍቃርያን ልብ ውስጥ የገባው ከ1989–96 ድረስ ኢትዮጵያ ቡና በቆየባቸው ሰባት ዓመታት ነበር። ከቡና ጋር የኢትዮጵያ ሻምፒዮና፣ የጥሎ ማለፍ እና የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ያነሳው ሳሙኤል በዘመኑ ምን ያህል ድንቅ ተጫዋች እንደነበረ በእርሱ ተቃራኒ ለቅዱስ ጊዮርጊስ የተጫወተው ሙሉዓለም ረጋሳ ይሄን ተናግሯል። “በሰውነቱ ደቃቃ ቢሆንም በአዕምሮው የሚጫወት ፈጣን እና ብልህ ተጫዋች ነው። ኳስን በሚገባ ተቆጣጥሮ በትክክል የሚያቀብል ታታሪ ተጫዋች ነው። ”
ዳዊት እና ጎልያድ በሚል ሥያሜ የተሰጠው የ1990ው የኢትዮጵያ ቡና እና አል አህሊ የካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ የመጀመርያ ዙር ጨዋታ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ 1-1 ተጠናቆ በመልሱ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ብዙ ጎል ተቆጥሮበት ከማጣርያው ውጪ ይሆናል ተብሎ ቢገመትም 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቆ ቡናማዎቹ ከሜማ ውጪ የተሻለ ባስቆጠረ ህግ ወደ ተከታዩ ማጣርያ ያለፉበት ታሪክ የሳሙኤል ኩኩሻ ጠንካራ የመከላከል አቅም የታየበት ነበር። አብሮት የተጫወተው ድንቁ አማካይ አሸናፊ ግርማ ለሶከር ኢትዮጵያ ሲናገር “ኩኩሻ በጣም ጎበዝ እና ብልጥ ከሚባሉት ሊቤሮዎች ግንባር ቀደም ነው። ፈጣን ነው፤ ከስቶፐሮች የሚያመልጡ ኳሶች በማቋረጥ በቀላሉ አጥቂዎችን ይነጥቃል። ኳስ ሲጫወት አቅልሎ ነው፤ ለአማካዮች ኳስ ሲያቀብል ይመቻል፤ ቀለል ያለ ነው።” ብሎለታል።
ብዙ እውቅና ካገኘበት ኢትዮጵያ ቡና ጋር በ1996 ከተለያየ በኋላ ለመከላከያ የተጫወተው አመለሸጋው ተከላካይ ሳሙኤል በቡና ካሳካቸው ድሎች በተጨማሪ ከመከላከያ እና መድን ጋር የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫን ማሳካት ችሏል። “ኩኩሻ” ከሀገሩ በመውጣት እግር ኳስን አስካቆመበት ጊዜ ድረስ በየመን ሊግ መጫወቱም ይታወሳል።
ሳሙኤል በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ታዳጊ፣ በኦሊምፒክ እና በዋናው ብሔራዊ ቡድን በመጫወት ሀገሩን አገልግሏል። በዚህም አዲስ አበባ በተዘጋጀው የሴካፋ የታዳጊዎች ውድድር ላይ ዋንጫ ማንሳት የቻለው እና በቦትስዋና መዲና ጋቦሮኒ በተዘጋጀው በታዳጊዎች የአፍሪካ ዋንጫ አራተኛ ደረጃ ይዞ በማጠናቀቅ በወቅቱ የአፍሪካ ብራዚል በተሰኘው ምርጡ ስብስብ ውስጥ አባልም ነበር። እነሆ ከሀገር ከወጣ 13 ዓመት የሆነው ኩኩሻ በእንግሊዝ ሀገር እየኖረ ይገኛል። ሶከር ኢትዮጵያ ይህን ድንቅ የዘጠናዎቹ ኮከብ ተከላካይ ከአለበት ሀገር አግኝታ አናግራዋለች።
” ከሁሉ አስቀድሜ አስታውሳቹ ርቀት ሳይገድባቹ ለቃለ መጠይቅ ስለጋበዛችሁኝ በጣም አመሰግናለሁ። እግር ኳስን በተጫወትኩባቸው ክለቦች ሁሉ በዋንጫ የታጀበ ስኬታማ ቆይታ አድርጌያለሁ። በተለይ በኢትዮጵያ ቡና የኢትዮጵያ ሻምፒዮና እና የጥሎ ማለፍ ዋንጫን አንስቻለው። መከላከያ እና መድንም እያለው የጥሎ ማለፍ ዋንጫን በማንሳት በእግርኳሱ ውስጥ የምችለውን ተሳትፎ አድርጌያለው። ኒያላም በነበርኩበት ጊዜም የክለቡ ኮከብ ተጫዋች በመባል የማስታወሻ ሽልማት ተበርክቶልኛል። በታዳጊ ቡድን ደረጃ የሴካፋ ዋንጫ እና በቦትስዋና በተካሄደው የአፍሪካ ታዳጊዎች ዋንጫ እስከ መጨረሻው ምዕራፍ በተጓዘው ቡድን ውስጥ ጥሩ ስኬት ቢኖረኝም በወጣት፣ በኦሊምፒክ ፣ በዋናው ብሔራዊ ቡድን ብዙም በስኬት የተሞላ ጊዜ አላሳለፍኩም።
” እኔ በምጫወትበት ዘመን የመሐል ተከላካይ አብዛኛውን ጊዜ በተክለ ሰውነቱ ገዘፍ ያለ በቁመቱ ረጅም መሆን አለበት የሚባል አስተሳሰብ የነበረ ቢሆንም አሰልጣኝ ሥዩም አባተ፣ አብረውኝ አጠገቤ በመሆን የተጫዋቱት እና የቡና አጨዋወት ዘይቤ ከእኔ አቅም ጋር ተደምሮ በጉልህ እንድታይ አድርጎኛል። ኳስ ጨዋታ ተክለ ሰውነት ብቻ ሳይሆን ብቃት እንዳለ ቢሆንም አዕምሮ እና የቡድንህ አጨዋወት ይወስነዋል፤ በዚህ ዘመን ሽመልስ በቀለን ምሳሌ ማድረግ ይቻላል። በዚህ ተክለ ሰውነቱ መሐል ላይ ኳስ በብልጠት ሲቀማ ፣ ኳስ ከመቀበሉ በፊት ለማን እንደሚያቀበል ፈጥኖ ሲያስብ ፣ ብቻውን በዚህ ሰውነቱ የቁጥር ብልጫ ሲወስድ ምንም ነገር ሳይገድበው ሲንቀሳቀስ ስንመለከት ተክለ ሰውነት መግዘፉ ትርጉም የለውም። ”
” ኩኩሻ የሚለውን ቅፅል ስም ያወጣልኝ አባቴ ነው። ኩኩ እያለ ይጠራኝ ነበር። በኃላ የሠፈር ልጆች እያቆላመጡ ኩኩሻ ብለው መጥራት ጀመሩ። ከዚህ ተነስቶ ነው ሳሙኤል ኩኩሻ እየተባልኩ መጠራት የቀጠልኩት። አሁን ሳሙኤል የሥራ መጠርያ ወይም የሆነ ቦታ የመመዝገቢያ ካልሆነ በቀር መጠርያ ስሜ ኩኩሻ ሆኗል፤ በዚህም ደስተኛ ነኝ።
” በእግርኳስ ተጫዋችነት ዘመኔ አላሳካሁትም የምለው ለኢትዮጵያ ቡና የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ አለማስገኘቴ ነው። በዘጠናዎቹ መጀመርያ እንደነበረን ጥንካሬ፣ ያን የመሰለ ወርቃማ ትውልድ ይዘን ይህን ልናሳካ ባለመቻላችን በጣም እቆጫለው። እንዲሁም በ1997 እና 98 የሴካፋ ዋንጫ ኢትዮጵያ ሻምፒዮን በሆነችበት ቡድን ውስጥ ለሀገሬ መጫወት አለመቻሌ በህይወት ዘመኔ የምቆጭበት ነው።
” የአሰልጣኝነት የመጀመርያ ኮርስ ወስጃለው ሆኖም የማሰልጠን ፍላጎት የለኝም። በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ ማሰልጠን በዚህ ዘመን ከባድ ነው። ሆኖም ለዕውቀት እንዲረዳኝ የአሰልጣኝነት ኮርስ ወስጃለው።
” አሁን የምኖረው በእንግሊዝ ሀገር ነው። ቤተሰብ መሥርቼ ከትዳር አጋሬ አንድ ሴት እና ወንድ ልጅ አሉኝ። ወንድ ልጄ እግር ኳስ ተጫዋች ቢሆን በጣም ደስ ይለኛል። ግን በዚህ ሰዓት የእርሱ ምርጫ እና ፍላጎት ይወስነዋል። እኔ አሳየዋለው እንጂ አላስገድደውም። ከሀገሬ ከወጣው አስራ ሦስት ዓመት ሆኖኛል። አክበራቹ ይህን ቃለ መጠይቅ ስላደረጋችሁልኝ በጣም አመሰግናለው። ፈጣሪ ኢትዮጵያና ህዝቦቿን አብዝቶ ይባርክ። ”
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ