የጆናታን ዊልሰን Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics የአማርኛ ትርጉም ምዕራፍ ዘጠኝ አራተኛ ክፍል ይህን ይመስላል።
የ1961ዱ የዳይናሞ አጨዋወት ላይ የተመረኮዙ ቁጥራዊ መረጃዎች አስገራሚ መልዕክት ነበራቸው፡፡ ክለቡ በዚሁ ዓመት የሊግ ዋንጫ ሲያነሳ በሰላሳ ጨዋታዎች የተቆጠሩባቸው ጎሎች ሃያ ስምንት ብቻ ነበሩ፡፡ በመከላከሉ ረገድ የተዋጣለት አደረጃጀት እንደነበራቸው ይህ ማሳያ ነው፡፡ በቀጣዩ ዓመት አምስተኛ ደረጃ ይዘው ሲያጠናቅቁ በአርባ ሁለት ጨዋታዎች አርባ ስምንት ግቦች አስተናገዱ፡፡ በ1963 ደግሞ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ቁልቁል ዘጠነኛ ሲወርዱ በሰላሳ ስምንት ጨዋታዎች አርባ ስምንት ጎሎች ገባባቸው፡፡ በ1964 ቪክቶር ማስሎቭ ቡድኑን ከተረከበ በኋላ በሊጉ የደረጃ መሻሻል አሳይተው ስድስተኛ ሆነው የውድድር ዓመቱን ሲያገባድዱ በሰላሳ ሁለት ጨዋታዎች የተቆጠሩባቸው ግቦች ወደ ሃያ ስምንት ቀነሱ፡፡ በ1965 ቡድኑ በማስሎቭ ሥር ከፍተኛ እመርታ ማሳየቱ ታየ፤ በዚህኛው የውድድር ዘመን ዓመቱን ሙሉ ለዋንጫ ሲፋለሙ ከርመው መጨረሻ ላይ ሁለተኛ ሆነው አጠናቀቁ፡፡ የሚቆጠርባቸውን የጎሎች መጠን በመቀነስ ሒደት ቀጥለው ተጋጣሚዎቻቸው በሰላሳ ሁለት ጨዋታዎች ከሃያ ሁለት ግቦች በላይ ሊያስመዘግቡባቸው አልቻሉም፡፡ በቀጣዮቹ ሶስት ተከታታይ የውድድር ዘመኖች የመከላከል አደረጃጀታቸውን የበለጠ በማሻሻል ተጉ፤ ተሳካላቸውም፡፡ በ1966 በሰላሳ አራት ጨዋታዎች አስራ ሰባት ግብ፣ በ1967 በአስገራሚ ሁኔታ በሰላሳ ስድስት ጨዋታዎች አስራ አንድ ግብ፣ በ1968 በሰላሳ ስምንት ጨዋታዎች ሃያ አምስት ግብ ተቆጠረባቸው፡፡
ከእነዚህ አስደናቂ ቁጥራዊ መረጃዎች በኋላ ማስሎቭ በሚከተለው የመከላከል አጨዋወት ታክቲክ ላይ የሚነሱ የተቃውሞ ክርክሮች መርገብ ጀመሩ፤ ይህ የሚጠበቅ ስለነበር ብዙዎችን አላስገረመም፡፡ በሶቭየት በስፖርት ጋዜጠኝነት ለረዥም ዓመታት የሰራው እና የ<ፉትቦል ማጋዚን> መስራቹ አንጋፋው ማርቲን ሜርዛኖቭ የ1967 የውድድር ዘመንን በዳሰሰበት ዘገባው ” ተጫዋቾች በጋራ መግባባትና መናበብ ሲከላከሉ፣ አንዳቸው ከሌላኛቸው ጋር እየተደጋገፉ ክፍተቶችን ሲሸፍኑ እና ትኩረታቸውን በአንድ የተጋጣሚ ተጫዋች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ከማድረግ ይልቅ በመከላከል ወረዳቸው ላይ በሚገቡ ሁሉም የባላጋራ ቡድን ተጫዋቾች ላይ ክትትል ሲጀምሩ የበለጠ ስኬታማ እንደሚሆኑ እየታየ ነው፡፡ ይህም በዞን የመከላከል አጨዋወት (Zonal Marking) ተጫዋችን-በ-ተጫዋች በመከታተል ከሚከወነው የመከላከል (Man Marking) ዘዴ የበለጠ ፍሬያማ እንደሆነ ማመሳከሪያ ሆኗል፡፡” ሲል ጽፏል፡፡
በእርግጥ በወቅቱ ይህን የሜርዛኖቭ ሐሳብ መረዳት እምብዛም አስቸጋሪ አልነበረም፡፡ በ1967 የዳይናሞዎች በሻክታር ዶኔስክ 2-1 መረታት መጪዎቹን ሁኔታዎች ጠቋሚ ፍንጭ ሆኖ አልፏል፡፡ ሌባኖቭስኪ ዳይናሞን ከለቀቀ በኋላ ወደ ምስራቁ የሃገሪቱ ክፍል ተጉዞ ሻክታሮችን ከመቀላቀሉ በፊት <ቼርኖሞሬትስ ኦዲሳ> በተባለ ክለብ ሁለት የውድድር ዘመናት አሳልፏል፡፡ በዚህ ክለብ ቆይታው ታክቲካዊ አስተሳሰቡን ቀርጿል፤ ግንዛቤውንም አዳብሯል፡፡ ከአሰልጣኝ ኦሌግ ኦሼንኮቭ ጋር በመሆን የቀድሞ ክለቡን የዳይናሞ የአጨዋወት ሥልትን ለማክሸፍ ውጥን ያዘ፡፡ ሌሎች ቡድኖች የሻምፒዮኖቹን ዳይናሞዎች አጨዋወት ተጽዕኖ ለመቋቋም ከመጣር ያለፈ ምንም በማያደርጉበት ወቅት ሌባኖቭስኪ ግን ሻክታሮች እንዲያጠቁ ይወተውት ያዘ፡፡ ለዚህ ሲባል ቡድኑ 4-2-4 ፎርሜሽንን መረጠ፡፡ ሁለቱ የሻክታር አማካዮች የዳይናሞዎቹ ሙንቲያን እና ዛቦ ላይ ጥብቅ የቅርብ ርቀት ቁጥጥር (Man Marking) እንዲያደርጉባቸው ታዘዙ፡፡ ይህ መላ የዳይናሞውን ሜድቬድ ብቸኛ የፈጠራ ምንጭ እንዲሆን አስገደደው፤ ተጫዋቹ ደግሞ የመፍጠር ብቃቱ ከእነ ሙንቲያንና ዛቦ አንጻር ለውድድር የሚቀርብ አልነበረም፡፡ ስለዚህም ሜዳ ላይ እርሱ በነጻነት ቢጫወት ለሌባኖቭስኪ ሥጋት ሊሆን አይችልም ነበር፡፡ ምንም እንኳ ሌባኖቭስኪ የሚቻለውን ያህል የዳይናሞዎችን ጠንካራ የማጥቃት ክፍል ለመፈተን ቢፈልግም ዋነኛ እቅዱ የተጋጣሚው የተከላካይ ክፍል ላይ የቁጥር ብልጫ በመውሰድ
ዳይናሞዎች እንዲዳከሙ ማድረግ ነበር፡፡ በ1969 በተካሄደ የአውሮፓ ክለቦች ዋንጫ ጨዋታ ዳይናሞ ከአንድ ዓመት በፊት የውድድሩ አሸናፊ የነበረውን ሴልቲክ በአንደኛው ዙር ቢያሸንፍም በወቅቱ የፖላንድ ሊግ ዋንጫ ባለቤት <ጎርኒክ ዛብርዜ> በደርሶ መልስ ድምር ውጤት 3-2 ተሸንፎ በሁለተኛው ዙር ተሰናበተ፡፡ በዚህ ፍልሚያ ዳይናሞዎች የፖላንዱ ክለብ ተጫዋቾች የነበሩት ዎድዝሚርዝ ሉባንስኪና ዚክፍሪድ ዞልቲዚክን እንቅስቃሴና ፍጥነት መቋቋም ተስኗቸው ተስተዋሉ፡፡
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ጥቂት ጨዋታዎች ለአብነት ያህል የቀረቡ ይሁኑ እንጂ ዳይናሞዎች የተጋጣሚዎቻቸውን አቀራረብ እያጤኑ የአጨዋወት ሥልታቸውን በመደበኛነት ሲቀያይሩ ታይተዋል፡፡ ይህ በወቅቱ በሌሎች ክለቦች የተለመደ አልነበረም፡፡ ተቀያያሪው የዳይናሞዎች አጨዋወታት በሶቭየት ሊግ የሚታዩ በርካታ የእግርኳስ ስልት ቄንጠኛ ለውጦችን ለመላመድ አስችሏቸዋል፡፡ ” የዳይናሞ ስብስብ ሁለት የተለያዩ ቡድኖች የሚመስል መልክ አለው፡፡ አንደኛው ተጋፋጭና በተጋጣሚ ላይ የበላይነት ለመውሰድ የሚታትር ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በደቡባውያኑ (የደቡብ አውሮፓ ሃገራት) እግርኳስ ሥልት የተቃኘ፣ ዝግ ባለ ፍጥነት የሚካሄድ፣ ቴክኒካዊና የቡድን ሥራ ላይ የሚያተኩር አጨዋወት የሚተገብር ነው፡፡ ይሁን እንጂ በዳይናሞ ከአንደኛው ቡድን ወደ ሌላኛው ቡድን እጅግ በቀላሉ ሽግግር ማድረግ ይቻል ነበር፡፡ ጨዋታ ከመጀመሩ ቀደም ብሎ በሚከወኑ አንድ ወይም ሁለት ለውጦች አልያም አልፎአልፎ በጨዋታ ወቅት በሚካሄድ የአንድ ተጫዋች ቅያሪ ይህን ሽግግር ማምጣትና ማሳካት አስቸጋሪ አልነበረም፡፡ ዳይናሞዎች ከደቡብ አውሮፓ የአጨዋወት ዘይቤ በመስመሮች ላይ በሚደረግ ፈጣን ሩጫ በመታገዝ ተሻጋሪ ቅብብሎች፣ ጠንካራ ምቶች እና ረዣዥም የአየር ላይ ኳሶች ወደሚዘወተርበት የጨዋታ አይትት በቀጥታ ለመዘዋወር ጊዜ አይፈጅባቸውም፡፡” ሲል ጋሊንስኪ ጽፏል፡፡
ማስሎቭ በእግርኳሳዊ እሳቤው ከጊዜው ቀድሞ ሄዷል፡፡ በሁለት የመሃል አጥቂዎች ለመጠቀም ከወሰነም በኋላ ለወደፊቱ ቡድኖች በጨዋታ አንድ አጥቂ ብቻ ማሰለፍ እንደሚጀምሩ ተንብዯል፡፡ ” እግርኳስን ልክ እንደሚበር አውሮፕላን ውሰዱት፡፡ ፍጥነት ሲጨምር የአየር ግፊቱም አብሮ ይጨምራል፡፡ ስለዚህ አውሮፕላኑ ከፍ ባለ የአየር ግፊት የመቋቋም ኃይል ዲዛይን ሊደረግ ይገባዋል፡፡” ሲል ያብራራል፡፡ ተቀባይነት ከማግኘት፣አዲስ ነገር ከመፍጠርና ውጤታማ ከመሆን አንጻር ማስሎቭ ልዩነት ፈጥሯል፤ አስገራሚ ሥራም ሰርቷል፡፡ ይሁን እንጂ ማስሎቭ ከዚያም በላይ አንድ እርምጃ ወደፊት የመቅደም እቅድ ነበረው፡፡ እግርኳሳዊ አስተምህሮዎቹ ዳይናሞ እና አያክስን በመሳሰሉ ክለቦች ፈጣን ተቀባይነት ቢያገኙለትም በአሰልጣኝነት ዘመኑ መሰረት የጣለላቸው በቀጠና የመከላከል ዘዴ (Zonal Marking) እና ተጋጣሚን ተጭኖ የመጫወት ዘይቤ (Pressing) በእርሱ የአሰልጣኝነት ዘመን ፍሬ አፍርቶ ለማየት አልታደለም፡፡
በጥር 1981 የሌባኖቭስኪ ዳይናሞ ዜኒት ሌኒንግራድን 3-0 በማሸነፍ የሶቭየት ሊግን ለአስረኛ ጊዜ አሸነፈ፡፡ <ስፖርቲቭና ሃዜታ> የተሰኘ ጋዜጣ ላይ የወጣ አንድ ጽሁፍ ቡድኑ በዋንጫው ጨዋታ የተገበረውን ፍሰት ያለው እንቅስቃሴ በማስመልከት ውዳሴውን አዥጎደጎደ፡፡ ይህም በዚያ ዓመት በክለቡ የታየው አጨዋወት ቀስ በቀስ እመርታ የሚያሳይ መሆኑን አመላክቷል፡፡ ” ቪክቶር ማስሎቭ የማጥቃት ሒደቱ በተለያዩ ተጫዋቾች የሚመራ ቡድን የመፍጠር ህልም ነበረው፡፡ ለምሳሌ፦ አናቶሊ ባይሾቬት እና ቪታሊ ኽሜልኒስኪ የተጋጣሚ ተከላካዮች ላይ የማጥቃት ጫና በመፍጠር ጨዋታ ሊጀምሩ ይችላሉ፤ ትንሽ ቆይተው ደግሞ ወደ አማካይ ክፍል አፈግፍገው ይጫወታሉ፡፡ ይህ ሲሆን ታዲያ በቀዳሚ የመጫወቻ ቦታቸው ሌሎች የቡድን አጋሮቻቸው ይተካሉ፤ ምናልባትም ሙንቲያን እና ሴሬብሪያንኮቭ ይህንን ኃላፊነት ይወስዱ ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ በጊዜው እንዲህ አይነቱ አጨዋወት እምብዛም ተቀባይነት አላገኘም፤ ይልቁንም የዚህኛው ዘመን ግኝት እንደሆነ ይታሰባል፡፡” ይላል የጋዜጣው መልዕክት፡፡
የማስሎቭ ተጫዋቾች በደመነፍስም ሆነ እንዳጋጣሚ አሁንም-አሁንም በሜዳ ላይ የመጫወቻ ቦታቸውን ይቀያይሩ ነበር፡፡ ” በማስሎቭ አማካኝነት የተገኘውን 4-4-2 ፎርሜሽን በመደበኛነት እንድንተገብር ብንታዘዝም በጨዋታ ሒደት ውስጥ ቦታ የመቀያየር፣ እርስበርስ የመተካካትና ክፍተቶችን የመድፈን እንቅስቃሴዎች የግድ ነበሩ፡፡ በቡድናችን ማንኛውም ተከላካይ ወደፊት እየሄደ ያለ ሥጋት ማጥቃት ይችላል፤ ምክንያቱም ተከላካዩ በተገቢው ሰዓት ወደ መደበኛ ቦታው ካልተመለሰ የቡድን አጋሩ ጥሎት የመጣውን ክፍተት እንደሚሸፍንለት ያውቃል፡፡ አማካዮችና የፊት መስመር ተሰላፊዎች ከቀድሞው ጊዜ በላቀ ራሳቸውን በተለያዩ የሜዳ ላይ ሚናዎች ለማሳተፍ ዝግጁ ሆነዋል፡፡ ይህ ቡድን (ዳይናሞ ኪዬቭ) ከ<ቶታል ፉትቦል> ጋር የተመሳሰለ እግርኳስ ይጫወታል፡፡ ሰዎች የቶታል ፉትቦል አጨዋወት ሥልት በሆላንድ የጀመረ ይመስላቸዋል፤ ይህ የሆነው ግን ምዕራብ አውሮፓውያኑ የማስሎቭን ዳይናሞ ስላላዩት ነው፡፡” ይላል ዛቦ፡፡
በ1970 በሶቭየት ሊግ ዳይናሞ በደረጃ ሰንጠረዡ ወደ ሰባተኛ ሲንሸራተት ዳይናሞ ማስሎቭን ከአሰልጣኝነት መንበሩ አነሳው፡፡ በ1966 በርካታ የክለቡ ተጫዋቾች ለአለም ዋንጫው ወደ እንግሊዝ ሲጓዙ ማስሎቭ ዳይናሞ በሊጉ የነበረውን ደረጃ እንዳያጣ ከወጣት ቡድኑ ወደ ዋናው ቡድን ብዙ ወጣቶችን በማሳደግ የክለቡን ሕልውና ለመጠበቅ በእጅጉ ጥሯል፡፡ በ1970 ግን ይህን ለማድረግ የሚያስችል እድል አልገጠመውም፤ ዳይናሞም የክለቡን ዘላቂ ሕልውና ለማስቀጠል ብቁ ተተኪዎች አልነበሩትም፡፡ ” የማንኛውም አሰልጣኝ ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው በሚያስመዘግበው ውጤት መሰረት ነው፡፡ የጸደይ ወቅት አልቆ የውድድር ዘመኑ እንደተጋመሰ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ሁለተኛ ነበርን፡፡ እስከ መጨረሻው ያንን አቋም ይዘን ብንዘልቅና ደረጃችንን ባንለቅ ኖሮ እርግጠኛ ነኝ <አያታችን> ሥራውን አይለቅም ነበር፡፡ ማስሎቭ በ1966 ከክለቡ ተመርጠው ወደ አለም ዋንጫ የተጓዙትን ተጫዋቾች የአስገራሚ ክህሎት ባለቤት በሆኑ ሌሎች ወጣቶች ተክቶ ድንቅ ቡድን አዘጋጀ፡፡ ያኔ የሰራውን ገድል በ1970ም እንዲደግም ተጠበቀበት፡፡ በጊዜው የተፈጠረው ተመሳሳይ ሁኔታ ነበር፡፡ ለሜክሲኮው የዓለም ዋንጫ ከዳይናሞ የተመረጡት ተጫዋቾች ለአንድ ወር ከአስራ አምስት ቀናት ያህል ከክለቡ ጋር ባልነበሩ ጊዜ ቡድኑ ሁለት ጨዋታዎች ብቻ ለማድረግ ተገደደ፡፡ በዚህ ጊዜ ከተጠባባቂው ቡድን ተወስደው በዋናው ቡድን እንዲሰለፉ የተመለመሉት ወጣቶች የበርካታ ጨዋታዎች ተመክሮ ስላልነበራቸው ለክለቡ ካስገኙት ጥቅም ይልቅ ጉዳቱ አመዘነ፡፡ ማስሎቭ ይህን ልምድ አልባነት ከግምት ሳያስገባ ቀርቶ ወደ ብቃታቸው ያልተመለሱትን አንጋፋ ተጫዋቾች ማሰለፍ ጀመረ፤ ያኔ የውድቀታችንን ቁልቁለት ተያያዝነው፡፡” በማለት የክለቡ ተከላካይ ቪክቶር ማትቪዬንኮ የዳይናሞና ማስሎቭን የመለያየት ምክንያት ይዘረዝራል፡፡
ምናልባት በአሰልጣኙና በዳይናሞ መካከል የተፈጠረውን ቅራኔ በቀላሉ ሊረዱት የሚገባ ጉዳይ ሊሆን ይችላል፡፡ ማስሎቭ ከክለቡ ጋር ለሰባት ዓመታት ቆይቷል፤ ውስጡ የመሰላቸት ስሜት አድሮም ይሆናል፡፡ የስንብቱ ሒደትና መልክ ግን በእርሱ ላይ ጥቁር ጠባሳ ትቶ አልፏል፡፡ ኮማን እንዲያውም ” በዳይናሞ ታሪክ እጅግ አሳፋሪው ምዕራፍ” ሲል ድርጊቱን ኮንኖታል፡፡ ማስሎቭ ከኪዬቭ እንዲለቅ የተደረገበት ምክንያት ፖለቲካዊ ግፊቱ ያይላል፡፡ የ1970ው የውድድር ዘመን መገባደጃ ሲደርስ ዳይናሞ ወደ ሞስኮው ተጉዞ CSKSን መግጠም ነበረበት፡፡ ጨዋታው ከመደረጉ ቀደም ብሎ ክለቡ ባረፈበት “ሆቴል ሩሲያ” በወቅቱ የዩክሬይን ብሄራዊ የስፖርት ኮሚቴ ምክትል ሊቀ መንበር የነበረው ሚዝያክ ተገኝቶ ማስሎቭ ከአሰልጣኝነት መንበሩ ስለመነሳቱ በይፋ አወጀ፡፡ ማስሎቭ በተመልካቾች ቦታ ተቀምጦና በእርሱ ምትክ አሰልጣኝ ሳይሾም ዳይናሞ ጨዋታውን 1-0 ተረታ፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የቡድኑን ተጫዋቾች አሳፍሮ ወደ አውሮፕላን ማረፍያ ሲጓዝ የነበረው አውቶቡስ በዩጎ ዛፓድናያ የምድር ውስጥ ባቡር ጣቢያ ቆመና ወደ ኪዬቭ በረራ ለማድረግ ከተዘጋጁት የቡድኑ አጠቃላይ አባላት መካከል ቪክቶር ማስሎቭን አወረደው፡፡ ባቡሩ እርሱን ጥሎ መንጎድ ሲጀምር ከወደ ትከሻው ወደኋላ ዘወር ብሎ በዝግታ እጁን ወደላይ ከፍ አድርጎ የስንብት የሚመስል ሰላምታ ሰጣቸው፡፡ ” እኔው ራሴ ይህን ኹነት በአይኔ ባልመለከት ኖሮ እንደ ማስሎቭ ያለ የገዘፈ ስብዕና ያለው ሰው ያልቅሳል ብዬ ለማመን እቸገር ነበር፡፡” ሲል ኮማን የማስሎቭን አሳዛኝ ስንብት ያስታውሳል፡፡
ማስሎቭ ወደ ቶርፒዶ ተመልሶ ማሰልጠን ጀመረና ከክለቡ ጋር የጥሎ ማለፉን ዋንጫ አሸነፈ፡፡ ቀጠለና የአርሜኒያውን አራራት ዬሬቫን ይዞ እዚህም የጥሎ ማለፍ ዋንጫ ባለድል ሆነ፡፡ ይሁን እንጂ የዳይናሞ ስኬቱን የመድገም ተነሳሽነቱና ወኔው አብሮት አልነበረም፡፡ በ1977 በስድሳ ሰባት ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡ ከዓመታት በፊት ከዳይናሞ አባሮት የነበረው ሌባኖቭስኪም የማስሎቭን ኗሪ ታሪክ ሊያስቀጥል ጥረቱን ቀጠለ፡፡ ቪክቶር ማስሎቭ የእግርኳስ አጨዋወት ላይ ያሳረፈው አሻራ ከጂሚ ሆጋን ጋር መሳ ለመሳ ባይሆንም ከዚያ ዘመን በኋላ የመጣ የትኛውም አሰልጣኝ የእርሱን ያህል ተጽዕኖ ፈጣሪ አልነበረም፡፡
ይቀጥላል...
ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡ ባለፉት አስራ ሦስት ዓመታትም አስር መፅሐፍትን ለህትመት አብቅቷል፡፡