የቢጫዎቹቹ ቁልፍ ተጫዋች ሳሙኤል ዮሐንስ የዛሬው የዘመናችን ኮከቦች እንግዳ ነው።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በሊጉ በግራ መስመር ተከላካይ ላይ ከታዩት ድንቅ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተከላካዮች አንዱ ነው። ሐረር ከተማ የተወለደውና በሐረር እና ባህርዳር ያደገው ሳሙኤል በልጅነቱ ያሳለፈው እጅግ አስቸጋሪ ጊዜ ሁኔታዎችን ፈታኝ ቢያደርግበትም እግርኳስ ተጫዋች ከመሆን አላገደውም። በ2007 ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተስፋ ቡድን በማምራት በቀጣዩ የውድድር ዘመን ወደ ዋናው ቡድን ማደግ የቻለ ሲሆን ክለቡ እስከፈረሰበት የ2009 መጨረሻ ድረስ በባንክ አሳልፏል። በመቀጠል ለአውሥኮድ አንድ የውድድር ዓመት ተጫውቶ በ2011 ወደ ድሬዳዋ በማቅናት ጥሩ የውድድር ጊዜ ያሳለፈ ሲሆን ለኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ቡድንም መጠራት ችሎ ነበር። ዘንድሮ በወልዋሎ በመጫወት የሚገኘው ሳሙኤል ዮሐንስ በቀጣዮቹ ዓመታት የብሔራዊ ቡድኑ ቀዳሚ ምርጫ ይሆናሉ ተብለው ከሚጠበቁ ተጫዋቾች አንዱ ነው።
ሳሙኤል ስላሳለፈው የልጅነት ጊዜ እና የእግርኳስ ሕይወት ከዚህ ቀደም ያደረግነውን ቆይታ ለማንበብ ፡- LINK
በዘንድሮው የወልዋሎ ቆይታው ጥቂት በማይባሉ ጨዋታዎች ቡድኑን በአምበልነት እየመራ በመሀል ተከላካይነት፣ በአማካይነት እና በተፈጥሯዊ ቦታው በመስመር ተከላካይነት ያገለገው ሁለገቡ ተጫዋች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረገው አዝናኝ ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
“ጊዜዬን የማሳልፈው…”
ሙሉ ጊዜዬን የማሳልፈው የህፃናት ማሳደጊያ ውስጥ ከወንድምና እህቶቼ ጋር ነው። በግሌ አንዳንድ ስፖርቶች በመስራት እና ህፃናቶቹንም በማሰራት እያሳለፍኩ ነው። እነሱ ከግቢ ስለማይወጡ አብዛኛው ጊዜዬ ከህፃናት ማሳደግያ ወንድም እና እህቶቼ ነው እያሳለፍኩ ያለሁት።
“እግር ኳስ ተጫዋች ባልሆን..”
የእግር ኳስ ተጫዋች ባልሆን የበጎ አድራጎት ላይ ወይም ደግሞ በቴክኒሻንነት እሰማራ ነበር። የበጎ አድራጎቱ እኔም በህፃናት ማሳደግያ ስላደግኩ እና የበጎ ሥራዎች ላይ መሳተፍ ስለሚያስደስተኝ ቅድሚያ በዛ ላይ ነበር የምሰማራው። ቴክኒሻንነት ደግሞ ከዚ ቀደም ሰርቼበታለው፤ በጣም ደስ የሚል ሙያ ነው።
“የማልረሳው ጎል ..”
የማልረሳው ጎሌ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እያለው አዲስ አበባ ከተማ ላይ ያስቆጠርኳት የማሸነፊያ ግብ ነች። በዛ ሰዓት ላለመውረድ ነበር የምንጫወተው። በዛ ላይ ተቀይሬ ስገባ አንድ ለአንድ ነበሩ። ልክ ተቀይሬ ስገባ በመጀመርያው ንክኪ ግብ አስቆጥሬ ቡድኔ አሸንፎ የወጣበት ጨዋታም ስለነበር ጎሏን አልረሳትም።
“በተቃራኒ ስገጥመው የሚያስቸግረኝ..”
ይህን ያክል በጣም የሚያስቸግረኝ እና የማስታውሰው ተጫዋች የለም። ሜዳ ላይ ያለኝን ነገር አውጥቼ ስለምጫወት ብዙም እንዲህ ያለ ነገር አይገጥመኝም። የግድ መናገር ካለብኝ ግን አማኑኤል ገብረሚካኤል ተቃራኒ ሆነህ ስትገጥመው የሚያስቸግር ተጫዋች ነው።
“አብሬያቸው ብጫወት ደስ የሚሉኝ..”
ከአጥቂዎች የአየር ኳስ የመጠቀም ልዩ አቅም ካላቸው ጋር ብጫወት ደስ ይለኛል። ለምሳሌ ጥቀስ ካልከኝ እንደነ ሰልሀዲን ሰዒድ እና ጌታነህ ከበደ ከአማካይ ደግሞ ቴዎድሮስ ታፈሰ እና ሱራፌል ዳኛቸው፤ ከተከላካዮች ያሬድ ባየህ፣ ፍቃዱ ደነቀ እና ገናናው ረጋሳ አይነት ተጫዋቾች ጋር ብጫወት ደስ ይለኛል።
“በእግር ኳስ የቅርብ ጓደኛዬ..”
በእግር ኳስ ቅርቡ እና ሁሉም ነገር የሚያማክረኝ ተጫዋች ሚኪያስ ዓለማየሁ ይባላል። አሁን
ገላን ከተማ ነው የሚጫወተው። አውሥኮድ በነበርኩበት ጊዜ አብሮኝ ተጫውቷል። በጣም የቅርብ ጓደኛዬ ነው፤ አስተዋይ ነው፤ በጣም ብዙ ነገር ነው የሚያማክረኝ።
“የተደሰትኩበት እና ያዘንኩበት አጋጣሚ ..”
ለኦሊምፒክ ብሔራዊ ቡድን የተጠራሁበት አጋጣሚ በእግርኳስ ሕይወቴ ውስጥ በጣም የተደሰትኩበት ጊዜ ነበር። በጣም ያዘንኩበት ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወረደበት ነው። ለወጣቶች ዕድል የሚሰጥ ቡድን ነበር። ቡድኑ ሲፈርስ ደግሞ የት ሄደን እንጫወታለን የሚል ጭንቀትም ስለነበር ቡድኑ ሲፈርስ ትልቅ ሀዘን ተሰምቶኝ ነበር።
“ብዙ ጊዜውን የማሳልፍበት ነገር …”
ከኳስ ውጭ የተፈጥሮ ነገር ደስ ይለኛል። ያለሁትም ባህርዳር ስለሆነ ሀይቅ ዳር በመቀመጥ ሙዚቃ በማዳመጥ እና የግል ስፖርት በመስራት ነው የማሳልፈው።
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ