ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአዲስ አበባ አስተዳደር አመራሮች ጋር በወቅታዊ ሁኔታ ዙርያ ውይይት አካሄደ

(መረጃው የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን ነው።)

የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራ ሀላፊዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ ዛሬ በሸራተን አዲስ ሆቴል ውይይት አደረገ።

በዚህ ውይይት ላይ ከአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የሴቶች እና ወጣቶች ማህበራዊ ዘርፍ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ክብርት ወይዘሮ ሂሩት አፅብሀ ፣ የአዲስ አበባ ወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ሀላፊ አቶ አብርሀም ታደሰ እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አረጋይ ሲገኙ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል አቶ አብነት ገብረ መስቀል (የቦርድ ሰብሳቢ)፣ አቶ ነዋይ (ም/ሰብሳቢ) እና አቶ ዳዊት ተገኝተዋል።

በዓለም የተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በሀገራችን ብሎም በከተማችን ጥላውን በማጥላቱ በክለቡና በስፖርቱ ቤተሰቦች ያሳደራቸው የኢኮኖሚና ማህበራዊ ተፅእኖን ለመቋቋምና በቀጣይ ችግሩን ለመፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ነው ውይይትና ምክክር የተደረገው። በኮቪድ 19 ምክንያት ክለቡ በራሳችን ጥረት የምናገኛቸው ገቢዎችና የገቢ ምንጮቻችን ስለተቋረጡና ስለተስተጓጎሉ ይህን ችግር የምንታደግበት ስፖርተኞቻችንና መደበኛ ሠራተኞቻችንን የኢኮኖሚ ድጋፍ የምናደርግበት አቅጣጫ በምክክር ልንተገብረው ይገባል ሲሉ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር ያለበትን ሁኔታ በዝርዝር ያስረዱት አቶ አብነት ገብረመስቀል ” በሀገራችን የመጣው ወረርሽኝ እንሻገረዋለን ይህ የሚሆነው ሁላችንም በአንድነት ቆመን ስንደጋገፍ፣ ስንደማመጥ፣ ስንረዳዳ በመሆኑ ልናሰምርበት ይገባል ብለዋል። የከተማ አስተዳደር ላነሳነው ጥያቄ በአፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ይህን ውይይት አዘጋጅቶ እንድንወያይና እንድንመካከሩ በማድረጉ በክለቡና በቦርዱ ስም ምስጋናዬን አቀርባለው ብለዋል።

በተለይ የከተማችን ፈርጦች የሆኑት የቅዱስ ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ቡና ህዝባዊ ክለቦች ከአመሠራረታቸው ጀምሮ በከተማዋ ብሎም በሀገር አቀፍ ይበልጡንም በአህጉር ደረጃ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ክለቦች ሲሆኑ በራስ ገቢ በመተዳደርና በማንኛውም ሀገራዊ ጥሪ ከፊት የሚገኙ መሆናቸው ይታወቃል። በመሆኑም ክለቦቹን ለመታደግ በተዘጋጀው የመነሻ ሀሳብ ሠነድ ላይ የክለቦቹ አመራሮችና የከተማው ሦስቱ የመንግስት አካላት ለመፍትሔው በጋራ እንደሚሰሩ ተነጋግረዋል።

ክለቡ ከከተማው አስተዳደር አስቀድሞ ቃል የተገባለት ከ9000 ካሬ በላይ ለልምምድ እና ለተጫዋቾች ካምፕ መገንቢያ ቦታ የማረጋገጫ ሰነድ ተረክቧል።
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ