የሙሉዓለም ረጋሳ ምርጥ 11

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ከሚጠቀሱ አማካዮች አንዱ የሆነው ሙሉዓለም ረጋሳ ከ1989 አንስቶ እስከ አሁን በመጫወት ላይ ይገኛል። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ሰበታ ከተማ ፣ መድን ፣ ሃዋሳ ፣ ደቡብ ፖሊስ እና ስሑል ሽረ የተጫወተው ሙሉዓለም አብረውት ከተጫወቱት መካከል የእሱን ምርጥ 11 በዚህ መልኩ አጋርቶናል።

በዩቲዩብ ለመመልከት : LINK

ግብ ጠባቂ 

በለጠ ወዳጆ

(ብሔራዊ ቡድን)

በለጠ ግብጠባቂ ቢሆንም አማካይ በለው። ኳስን አቁሞ በደንብ መጫወት የሚችል እና በጣም ንቁ የሆነ ግብጠባቂ ነው። ያለው አቅም ከግብጠባቂ ባሻገር በእግሩ የሚጫወት በመሆኑ እርሱን ምርጫዬ አድርጌያለው።

ተከላካዮች

አንዋር ሲራጅ
(ቅዱስ ጊዮርጊስ/ብሔራዊ ቡድን)

ኳስ የመንጠቅ አቅሙ የተሻለ የሆነና ቆሞ ሁሉ መንጠቅ የሚችል ተከላካይ ነው። ከአማካይ ተጫዋቾች ጋር ያለው ግኑኝነት እንዲሁም ላሰበው ተጫዋች በትክክል ኳስ ተቀብሎ ማድረስ የሚችል ተጫዋች ነው።

ሳሙኤል ደምሴ
(ብሔራዊ ቡድን)

በሰውነቱ ደቃቃ ቢሆንም በአዕምሮ የሚጫወት ፈጣን እና ብልህ ተጫዋች ነው። ኳስን በሚገባ ተቆጣጥሮ በትክክል የሚያቀብል እና እኔ ላሰብኩት እንቅስቃሴ የሚሆን ታታሪ ተጫዋች ነው።

ዮሴፍ ሰለሞን
(ቅዱስ ጊዮርጊስ)

ከአማካይ ተጫዋቾች ጋር ያለው ግኑኝነት እንዲሁም ላሰበው ተጫዋች በትክክል ኳስ ተቀብሎ ማድረስ የሚችል እና ኳስ የመንጠቅ አቅሙ ከፍተኛ የሆነ ተጫዋች ነው።

አማካዮች

ገብረኪዳን ነጋሽ
(ብሔራዊ ቡድን)

መመላለስ የሚችልበት አቅም ያለው ፈጣን፣ ከአማካይ ተጫዋቾች ጋር ሆኖ ኳስን የሚያስቀጥልበት ችሎታው እርሱን እንድመርጥ አድርጎኛል።

ጌቱ ተሾመ
(ቅዱስ ጊዮርጊስ/ብሔራዊ ቡድን)

ከእኔ ጋር ብዙ ዓመት ተጫውቶ እንደማሳለፉ አቅሙን በሚገባ አቀዋለው። ኳስ የመቀማት፣ የመጫወት አቅሙ ከፍተኛ ነው። ሁለቱንም ነገሮችን አጣምሮ የያዘ በጣም ጥሩ ተጫዋች ነው።

አንዋር ያሲን
(ብሔራዊ ቡድን)

ስለ እርሱ ምንም አልናገርም፤ ሰው ሁሉ ስለ እርሱ አቅም እና ችሎታ ይናገራል። በጣም የማደንቀው እና የማከብረው ሁሉንም ነገር ያሟላ ተጫዋች ነው።

ዳዊት መብራህቱ
(ቅዱስ ጊዮርጊስ/ብሔራዊ ቡድን)

ዳዊት ሁሉ ነገር ያለው ተጫዋች ነው። ፈጣን፣ ጉልበተኛ፣ ከርቀት ጠንካራ ምት የሚመታ፣ ለአጥቂዎች ተገቢ ኳስ የሚያደርስ፣ ከተጫዋቾች ጋር ተረዳድቶ የሚጫወትና ሁሉን ማድረግ የሚችል ተጫዋች ነው።

አጥቂዎች

ዮርዳኖስ ዓባይ
(ብሔራዊ ቡድን)

ከአማካይ ጋር ተጫውቶ ወደ ሳጥን የመግባት አቅም ያለው በጣም ብልጥ አጥቂ ነው። ጎል የሚያስቆጥርበት መንገድ ከማንም የተሻለ ነው።

አሸናፊ ሲሳይ
(ቅዱስ ጊዮርጊስ/ብሔራዊ ቡድን)

ፈጣን፣ ጉልበተኛ እና ታታሪ አንድ አጥቂ ሊያሟላ የሚገባቸውን ነገሮች በሙሉ ያሟላ በድፍረት እና በፍጥነት ሁሉን ነገር ማድረግ የሚችልበት አቅሙ ያለው አጥቂ ነው።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ