የሴቶች ገፅ | ከተጫዋችነት እስከ ኢንስትራክተርነት…

በዛሬው የሴቶች ገፅ አምዳችን ከአማካይ ሥፍራ ተጫዋችነት እስከ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት አልፎም እስከ ኢንስትራክተርነት የተሻገረችው አሰልጣኝ ሠላም ዘርዓይን ይዘንላችሁ ቀርበናል።

ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ በተለምዶው 24 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው። በሠፈሯ እግር ኳስን ከወንዶች ዕኩል በመጫወት ካሳለፈች በኃላ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቆይታዋ የካ ቅዱስ ሚካኤል የተባለ የፕሮጀክት ቡድን ሲቋቋም ቡድኑን በመቀላቀል የእግር ኳስ ህይወቷን ጅማሮ አድርጋለች። 1994 ላይም የአዲስ አበባ የሴቶች ዲቪዚዮን ውድድር ላይ ከቡድኑ ጋር የዋንጫ አሸናፊ መሆን ችላ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የዚህ ቡድን አሰልጣኝ ወደ አሜሪካ በማቅናቱ ምክንያት ቡድኑ ብዙም ሳይቆይ ፈረሠ። ቀጥላም በቀድሞው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ረዳት አሰልጣኝ ሲሳይ ከበደ ወደሚሰለጥነው ሀይኮፍ (ኤግልስ) ወደተባለው ቡድን አመራች። ቡድኑ በወቅቱ አዲስ አበባ ውስጥ እጅጉን ጠንካራ ከሚባሉ ቡድኖች ውስጥ የሚጠቀስ ጠንካራ ተጫዋቾችን ያፈራ እንደነበረ ይገለፃል፡፡

በመቀጠል ሠላም 1998 እና 1999 በአሰልጣኝ ብዙአየው ዋዳ አማካኝነት በሚሰለጥነው ትውልድህን አገልግል ተብሎ ወደሚጠራው ቡድን አቅንታ ሁለት ዓመታትን ካሳለፈች በኃላ ወደ ደቡብ ክልል በመሄድ ወደ ሚሊኒየሙ መግቢያ አካባቢ ጌዲኦ ዞንን ወክላ ተጫውታለች። ባሳየችው እንቅሴቃሴም ለደቡብ ክልል ምርጥ ቡድን በአሁኑ የጌዲኦ ዲላ ሴቶች ቡድን አሰልጣኝ እንዳልካቸው ጫካ እና መለሰ አማካኝነት ተመርጣ በተከታታይ ለሁለት ዓመታት ለክልሉ ተጫውታለች። በዚህ ቡድን ውስጥ ከነህይወት ደንጊሶ፣ ሠናይት ባሩዳ እና ዓይናለም አሳምነው እንዲሁም ሌሎች ጠንካራ ተጫዋቾች ጋር በመሆን በዚህ ቡድን ውስጥ ውጤታማ ጊዜን አሳልፋለች፡፡ በቆይታዋም በኢትዮጵያ ወጣት ብሔራዊ ቡድን በአሰልጣኝ ሠውነት ቢሻው አማካኝነት ብትመረጥም ኢትዮጵያ በወቅቱ በፊፋ በተጣለባት ቅጣት የተነሳ ለሀገሯ የመጫወት ህልሟ ባይሳካላትም እግር ኳስን በአማካይነት እና አምበልነት ስትጫወት ከቆየች በኃላ 2001 ላይ እግር ኳስን በማቆም የአሰልጣኝነት ስልጠናን በመውሰድ ወደ ስልጠናው ዓለም ገብታለች፡፡

አሰልጣኝ ሠላም ዘርዓይ ስለአሰልጣኝነት ሙያ አጀማመሯ ይህን ትላለች። ” ወደ ሥልጠናው ዓለም የገባሁት 2002 ላይ ነው፤ ትውልድህን አገልግል የሚባል የከፍተኛ ዲቪዚዮን የወንዶች ቡድን በማሰልጠን። በጊዜው አንድ ስልጠና ወስጄ ነበር። በወቅቱ ቡድኑን ይዘውት የነበሩት አሰልጣኞች እና ተጫዋቾች ወደ ልደታ ክፍለከተማ ስለሄዱ ቡድኑ አሰልጣኝም ተጫዋችም አልነበረውም። የቡድኑ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ደግፌ ይባላል ፤ ለኔ ጥሪ አቀረበልኝ። መጀመሪያ ላይ አልተቀበልኩም ነበር ፡፡ አንድ ሁለቴ ግን ቀጥረው ካወሩኝ በኃላ አሳመኑኝ። ከዛ ምልመላ ጀመርኩኝ። የዛኔ በጣም ከባድ ነበር ፤ ተጫዋቾች በሙሉ ወጥተዋል። ቡድኑ ዋንጫ በልቶ ከአንደኛ ዲቪዚዮን ወደ ከፍተኛ ዲቪዚዮን አድጓል ግን በወቅቱ የነበሩ ተጫዋቾች በሙሉ ሄደዋል። ለኔም ሥልጠናን በከባድ እንድጀምር ነበር ያደረገኝ። ውድድሩም ሊጀምር ቅርብ ጊዜ ሆነ ፤ እኔም ተጫዋቾችን ማግኘት አልቻልኩም። ስለዚህ በተቻለኝ መጠን በየሠፈሩ እንደ መስቀል አደባባይ እና መሠል አካባቢዎች በመዞር በወጣት ተጫዋቾች ቡድኑን ሰራሁ። የመጀመሪያ ጨዋታዬም ተስፋ ለኢትዮጵያ ከሚባል ቡድን ጋር ነበር። ይህ ቡድን በአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ይሰለጥን ነበር። እሱ በአጋጣሚ ወደ አሜሪካ ስለሄደ ሌላ አሰልጣኝ ነበር ቡድኑን የያዘው። በጣም ፈርቼ ነበር ፤ በክለብ አሰልጣኝነት ህይወቴ የመጀመሪያዬ ስለነበር። አጋጣሚ ሆኖ ሁለት ለባዶ አሸነፍን ፤ በጣም የተለየ ደስታም ተሰማኝ። ቡድኑ በጥሎ ማለፍ ጨዋታ እና በዲቪዚዮን ውድድርም ጠንካራ ነበር።”

ሠላም ለአሰልጣኝነት በነበራት ጠንካራ ፍቅር እና የሥልጠና ሂደት የተነሳ በሠፈሯ ከ2003 ጀምሮ ታዳጊ ወጣቶችን በመሰብሰብ እያሰለጠነች ለተለያዩ ክለቦች እንዳበቃችም ብዙዎች ይመሰክሩላታል፡፡ በግሏ ያለምንም ክፍያ ታደጊዎችን ስታሰለጥን ከቆየች በኃላ 2004 ላይ በወቅቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተስፋ ቡድን አሰልጣኞች ፋሲል ተካልኝ እና ዘሪሁን ሸንገታን ወደ ዋናው ቡድን ረዳት አሰልጣኝነት ሲያድጉ የተስፋው ቡድን አሰልጣኝ የመሆን ዕድል አገኘች።

” ማስታወቂያ ሲወጣ ሳሰለጥን የሚያውቀኝ አንድ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ ነገረኝ። እሱን አዳመጥኩት መጀመሪያ ግን ችላ ብዬውም ነበር ፤ ጊዮርጊስን የሚያክል ክለብ ሴቶችን ይቀጥራል ብዬ ዕምነቱ ስላልነበረኝ። ከዛ በኃላ ግን እነፋሲልም ሌሎች ጓደኞቼም ተፅዕኖ ሲያሳድሩብኝ እስቲ ቆይ ሲቪዬን ላስገባ እና አቅሜን ልየው ብዬ አመለከትኩ። በወቅቱ ከፍተኛ ዲቪዚዮን እየሰራሁም ነበር። ከሁለት ወር በኃላ ተደወለልኝ። በወቅቱ የነበሩት የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ተረፈ አንበርብር ቢሮ ለኢንተርቪው እንደምፈለግ ገለፁልኝ። እኔ እና አሁን ካናዳ የሚገኘው አሰልጣኝ በላቸው ሁለታችንም ለክለቡ እንደተመረጥን ነገሩን። ከዛ እኔም ከ20 ዓመት በታች የክለቡ አሰልጣኝ ተደርጌ ማሰልጠን ጀመርኩ” በማለት ወደ ፈረሰኞቹ ቤት የተቀላቀለችበትን ጊዜ ታስታውሳለች።

አሰልጣኝ ሠላም ከ20 ዓመት ቡድኑ አሰልጣኝ ከሆነች በኃላ እንደ ናትናኤል ዘለቀ ፣ ዘካሪያስ ቱጂ ፣ ዓለምአየሁ ሙለታን የመሳሰሉ ተጫዋቾችን ለቅዱስ ጊዮርጊስ ዋናው ቡድን አበርክታለች፡፡ በተስፋ ቡድኑ አንድ ዓመት ከግማሽ ከቆየች በኃላ ጊዮርጊስ 2005 ግማሽ ላይ የሴቶች ቡድን ሲያቋቁም በቀጥታ ዋና አሰልጣኝ በመሆን ተመርጣ ማሰልጠን ጀመረች። በዚህ ቡድን ቆይታዋ አዳዲስ ወጣት ተጫዋቾችን አስተዋውቃለች። በመቀጠል በክለቡ ዋና አሰልጣኝ በመሆን ስትሰራ ከቆየች በኃላ 2007 ላይ የአሰልጣኝ በኃይሏ ዘለቀ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ረዳት አሰልጣኝ በመሆን ብሔራዊ ቡድን የማሰልጠን መንገድን በይፋ ጀመረች። የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድንን እያሰለጠነች ከቀጠለች በኃላ በ2010 ላይ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ በመሆንም ሠርታለች። ቡድኑንም ይዛ በማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ ባሳየችሁ ውጤታማ ጉዞ መነሻነት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ በማድረግ ቀጥሯታል፡፡ አሰልጣኟም በወቅቱ ዋናውን ብሔራዊ ቡድን ይዛ በሴካፋ ዋንጫ አዳዲስ ተጫዋቾችን በመያዝ ተሳታፊ የነበረች ሲሆን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ዩጋንዳን በደርሶ መልስ ረትታ በሁለተኛው ዙር ማጣሪያ በካሜሩን በደርሶ መልስ ከተሸነፈች (ባህር ዳር 1-1፣ ያውንዴ 0-0) በኃላ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ተለያይታለች፡፡

ከብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት በኃላ በተለያዩ ስልጠናዎች ራሷን እያሳደገች መጥታ በቅርቡ የኢንስትራክተርነት ደረጃን በመያዝ ለሴት አሰልጣኞች የ’ዲ’ ላይሰንስ ሥልጠናን ስትሰጥ የነበረችው ሠላም ኢንስትራክተርነቷን እንዴት እንዳገኘች እንዲህ ታስረዳለች። ” ኢንስትራክተር የሆንኩት አሁን አይደለም። በ2004 አካባቢ ካፍ በጊዮን ሆቴል የኢንስትራክተርነት ሥልጠና ሰጥቶ ነበር። በዛ ውስጥ ብዙ አፍሪካዊያን ሴቶች ነበሩ። ከዛ ውስጥ እንግዲህ አምስት የምንሆነው ኢትዮጵያዊያን ሴቶች ተካፍለናል ፤ እኔ መሠረት ማኔ ፣ ህይወት አረፋይኔ ፣ በኃይሏ ዘለቀ እንዲሁም ደግሞ አሁን በካፍ ውስጥ እየሰራች ያለችሁ መስከረም ታደሰ። ከ2004 በኃላ ግን እንደዚህ ዓይነት ዕድሎችን ማግኘት አልቻልኩም። አሁን ላይ ግን በነበረው የብሔራዊ ቡድናችን መሻሻል ምክንያት በፊፋም ብዙ ቁጥሮችን አሻሽለን ወደ ላይ ከፍ ብለን ስለነበር ካፍ ቀጥታ ጥሪ አቀረበልኝ ፤ ከዛም ኮርሱን መውሰድ ቻልኩኝ። ኢንስትራክተር ለመሆን በጣም መልፋት እና መስራት ያስፈልጋል ብዬ አስባለሁ። ውድድሩ ከዚህ በኃላ ይጀምራል ማለት ነው። በቀጣይ ተተኪ አሰልጣኞችን በምችለው ሁሉ ሰርቼ ከሌሎች ትልልቅ ኢንስትራክተሮች ጋር ለማፍራት እንጥራለን።”

‘እግር ኳሱ በሀገራችን ተስፋ ቢያስቆርጥም ለሚወደው ግን አስደሳች ነው’ ብላ የምታስበው አሰልጣኝ ሠላም ዘርአይ በፊፋ በተጋበዘችበት የፊፋ የዓለም ምርጥ ተጫዋቾች ምርጫ እና የዓለም ዋንጫን አስመልክቶም በተዘጋጀው ኮንፈረንስ ላይ ከዓለም ትላልቅ ከዋክብት ከነ ሜሲ ፣ ቫንዳይክ እና ሌሎች የእግር ኳሱ ስመጥሮች ጋር ያሳለፈችውን ጊዜ የማትረሳው እንደሆነ ትናገራለች። አሰልጣኟ በወንዶች ላይ የመስራት ዕቅድ እንዳላት የተናገረች ሲሆን ከሀገር ውጪ ወጥቶም ለማሰልጠን መንገድ ላይ ስለመገኘቷ ፍንጭ ሰጥታናለች። በቅርቡ ወደ ስፔን ባርሴሎና ለትምህርት እንደምታመራ የምትጠበቀው አሰልጣኝ ሠላም ዘርዓይ እዚህ እንድትደርስ የሠፈሬ ሰዎች ፣ ቤተሰቦቼ ፣ ባለቤቴ እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ትልቅ ድርሻ አላቸው ያለች ሲሆን ‘ከምንም በላይ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ለእኔ እዚህ ለመገኘት የመጀመሪያውን ቦታ ይይዛል’ ብላለች።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ