የሀዋሳ ከተማ የቀድሞው ተጫዋቾች ማኅበር አቋቋሙ

“የሀዋሳ ከተማ የቀድሞ እግር ኳስ ክለብ ተጫዋቾች” በሚል መጠሪያ በጎ አላማን ያዘለ ማኅበር ዛሬ በሀዋሳ ሴንትራል ሆቴል በይፋ ተቋቋመ፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ሁለት ጊዜ እንዲሁም ደግሞ የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫን በ1997 ላይ ከፍ በማድረግ የሳመው ይህ አንጋፋ ክለብ በክለብ ደረጃ በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ እና ኮንፌድሬሽን ካፕ ላይ ኢትዮጵያን በመወከል የተወዳደረ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም በርካታ ተጫዋቾችን አበርክቷል ስመ ጥሮችንም አፍርቷል፡፡ ይሁንና ክለቡ የረዘመ ታሪክ ያለው ቢሆንም በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እያስመዘገበ ያለውን ደካማ የውጤት ደረጃን ለማሻሻል ከጎኑ ሆኖ በተለያዩ መልኩ ለመርዳት እንዲሁም የተቸገሩ የቀድሞ የክለቡ ተጫዋቾች ለመደገፍ እና ሌሎች ተጨማሪ በርካታ በጎ ተግባራትን ለማስፈፀም ይረዳ ዘንድ “የሀዋሳ ከተማ የቀድሞ ተጫዋቾች ማኅበር” በሚል ሥያሜ በይፋ ዛሬ ተመስርቷል፡፡

ማኅበሩ ዛሬ በሴንትራል ሀዋሳ ሆቴል በተደረገ ስነ-ስርአት ሲመሠረት በመክፈቻው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃሚ እና ከዚህ ቀደም ክለቡን በኃላፊነት መርተው የነበሩት አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ ለተጫዋቾቹ መመሪያ የሰጡ ሲሆን ይህ ማኅበርም ከከተማዋ አልፎም ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲደርስ ሁሉም የራሱን ድርሻ መወጣት አለበት በማለት የተናገሩ ሲሆን ይህ ታሪካዊ ተጫዋቾችን የያዘ ማኅበር መመስረቱ እጅግ እንዳስደሰታቸው ሶከር ኢትዮጵያ በስፍራው ተገኝታ መታዘብ ችላለች።

ይህ ማኅበር በአባልነት ከ1970ዎቹ ጀምሮ በሀዋሳ ከተማ ሲጫወቱ የነበሩ እና እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም የክለቡን መለያ በመልበስ መጫወት የቻሉትን በውስጡ አካቶ የያዘ ሲሆን እጅግ በርካታ በጎ አላማን በውስጡ የያዘ እንደሆነ ይህ ማኅበር እንዲመሠረት ያነሳሱት የቀድሞው የሀዋሳ ተጫዋቾች አንዱዓለም ነጋ (ቢጣ) እና ሚካኤል ወልደሩፋኤል ተናግረዋል፡፡ ይህ ማኅበር በቀጣይ ራሱን በሚገባ አጠናክሮ ይቀርብ ዘንድ ጊዜያዊ ኮሚቴን በመምረጥም ተጠናቋል፡፡ በዚህ መሠረት ሰብስቤ ደፋር፣ አዳነ ግርማ፣ ልዑልሰገድ፣ ሚካኤል ወልደሩፋኤል፣ አንዱአለም አረጋ (ጋጋ) ፡ አንዱዓለም ነጋ (ቢጣ)፣ ዘውዴ አበራ እና ወንድወሰን መሳ (ማሜ) በቀጣይ ሥራ አስፈፃሚ በቋሚነት እስኪመረጥ ድረስ ማኅበሩን ለማጠናከር ሀኃላፊነት የተሰጣቸው ተጫዋቾች ሆነዋል፡፡

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ