በዛሬው ይህን ያውቁ ኖሯል አምዳችን ትኩረታችንን በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች ዙሪያ በማድረግ ዕውነታዎችን እናነሳለን።
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በአዲስ መልክና መዋቅር የተጀመረው በ1990 ዓ/ም ነው። ልክ ውድድሩ ሲጀምር ስያሜው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሊግ ነበር። ከሁለት ዓመታት(1992) በኋላ ግን ሊጉ አሁን የሚጠራበትን ስያሜ አገኘ። ሊጉ ከተጀመረበት ከ1990 ዓ/ም ጀምሮ የተለያዩ እውነታዎች የተመዘገቡ ሲሆን ለዛሬ ግን በይህን ያውቁ ኖሯል? አምዳችን በዚህ የሀገሪቱ የመጀመሪያ የሊግ እርከን ላይ ስለተሳተፉ ክለቦች ያሉ እውነታዎችን እናነሳለን።
1 – የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በአዲስ መዋቅር በ1990 ከተጀመረ በኋላ እስካሁን 51 ክለቦች በውድድሩ ተሳትፈዋል።
2 – ሊጉ እንደ አዲስ ሲመሰረት የነበሩት ክለቦች ኢትዮጵያ ቡና፣ ፐልፕ እና ወረቀት፣ ጉና ንግድ፣ ኢትዮጵያ መድን፣ ሀዋሳ ከተማ፣ መብራት ኃይል፣ ኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ እና ድሬዳዋ ጨርቃጨርቅ ናቸው።
3 – በውድድሩ በርካታ አዳዲስ ክለቦች የተቀላቀሉበት ዓመት 2000 ነው። በኢትዮጵያ ሚሌኒየም በተደረገው በዚህ ውድድር ላይ በአጠቃላይ 25 ክለቦች በውድድሩ መሳተፋቸው አይዘነጋም። በ1999 በፌዴሬሽኑ እና ክለቦች መካከል በተነሳ ውዝግብ 10 ክለቦች ሊጉን ማቋረጣቸውን ተከትሎ በ2000 የወጡትን ቡድኖች ለመተካት በሚል ከብሔራዊ ሊጉ 7 ክለቦችን በመቀላቀል ውድድሩ ቢጀምርም በፌዴሬሽኑ ጊዜያዊ የአመራር ለውጥ ወቅት ከሊጉ የወጡት ክለቦች በመመለሳቸው በ25 ክለቦች መካከል ተካሂዷል። በዚህ ወቅት በቅድሚያ ያደጉት ደቡብ ፖሊስ እና እህል ንግድን ጨምሮ በውሳኔው ከተቀላቀሉት 7 ቡድኖች መካከል ስድስቱ (ኦሜድላ፣ ፊንጫ ስኳር፣ አአ ፖሊስ፣ ባህር ዳር ዩ፣ ፋሲል ከነማ እና ውሀ ስፖርት)ን ጨምሮ በአጠቃላይ 8 ቡድኖች በዚህ የሃገሪቱ ከፍተኛ የሊግ እርከን ሲሳተፉ የመጀመሪያቸው ነበር። ከ2000 በመቀጠል በ1991፣ 1992፣ 2002 እና 2010 የውድድር ዓመታት 3 ክለቦች በሊጉ መሳተፍ የጀመሩበት ሌሎች ዓመታት ናቸው።
4 – እስካሁን በሊጉ ላይ ከተሳተፉት አጠቃላይ 51 ክለቦች 20ዎቹ ከነአካቴው ከተሰናበትናቸው ሰንበትበት ብሏል። ፐልፕ እና ወረቀት፣ ኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ፣ ድሬዳዋ ጨርቃጨርቅ፣ ጉና ንግድ፣ ምድር ባቡር፣ ሙገር ሲሚንቶ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ትራንስ፣ ሐረር ከነማ፣ ወንጂ ስኳር፣ ኒያላ፣ አርባምንጭ ጨርቃጨርቅ፣ ብርሃንና ሠላም፣ አየር ኃይል፣ ጥቁር አባይ፣ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣ ፊንጫ ስኳር፣ እህል ንግድ፣ ሜታ አቦ እና ዳሽን ቢራ በሊጉ ተሳትፈው የፈረሱ ክለቦች ናቸው።
5 – እስካሁን 7 የተለያዩ ክለቦች ይህንን ሊግ በአሸናፊነት አጠናቀዋል። (መብራት ሃይል፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ሃዋሳ ከተማ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ደደቢት፣ ጅማ አባጅፋር እና መቐለ 70 እንደርታ)።
6 – ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ2006-09 ባሉት አራት ዓመታት በተከታታይ ዓመታት ዋንጫ በማንሳት ቀዳሚው ክለብ ነው። ፈረሰኞቹ ከ2000-02 ድረስ ዋንጫ በተከታታይ ለ3 ዓመታት በማንሳትም ሁለተኛውን ሪከርድ ይዘዋል።
7 – በ22 ዓመታት የሊጉ ጉዞ ከፍተኛ ነጥብ በማምጣት የሊጉ አሸናፊ የሆነው ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው። በ2002 የውድድር ዓመት 84 ነጥቦችን በማስመዝገብ። በየጨዋታው በሚመዘገብ አማካይ ነጥብም ቅዱስ ጊዮርጊሶች በሊጉ ጥሩ የማሸነፍ ንፃሬን (2.6) በመያዝ ቀዳሚዎቹ ናቸው (2006 – በ26 ጨዋታ 68 ነጥብ)።
8 – በአማካይ ዝቅተኛ ነጥብ የሊጉን ዋንጫ የራሱ ያደረገ ክለብ ሃዋሳ ከተማ ነው። ቡድኑ በ1996 ዋንጫውን ሲያነሳ በ26 48 ነጥቦችን ብቻ ነበር የሰበሰበው። ይህ ነጥብ በጨዋታ ሲሰላ ቡድኑ በየጨዋታው የሚሰበስበውን አማካይ ነጥብ 1.8 ያደርገዋል።
9 – በሊጉ ዝቅተኛ ነጥብ ያስመዘገበው ክለብ ፐልፕ እና ወረቀት ነው። ሊጉ እንደ አዲስ ሲመሰረት የነበረው ነገር ግን በዛኑ ዓመት የወረደው ይህ ክለብ በ1990 የውድድር ዓመት 5 ነጥቦችን ብቻ በ14 ጨዋታ በመሰብሰብ በሊጉ ዝቅተኛ ነጥብ ያመጣ ክለብ ሆኗል።
10 – በአማካይ በጨዋታ ትንሽ ነጥብ የሰበሰበው ክለብ ደግሞ አርባምንጭ ጨርቃጨርቅ ነው። ይህ ክለብ በ1997 ካደረጋቸው 26 ጨዋታዎች 0.26 ነጥብ ብቻ በጨዋታ ያስመዘግብ ነበር። በዚህ ዓመት ከፍተኛ ችግር ውስጥ የነበረው ቡድኑ በሁለተኛ ዙር የሊጉ ጨዋታዎች ካደረጋቸው 13 ግጥሚያዎች በአንዱ ብቻ ነው ሦስት ነጥብ ያገኘው። ይህም የተገኘው ደግሞ በፎርፌ ነበር። ሁለተኛው በጨዋታ ትንሽ ነጥብ ያስመዘገበው ክለብ ሀዲያ ሆሳዕና ነው። በ2008 ከሊጉ በመውረድ ዘንድሮ ዳግም የተመለሰው ይህ ክለብ የዛኔ 0.3 ነጥብ በጨዋታ ያስመዘግብ ነበር።
11 – ዝቅተኛ ሽንፈት በማስተናገድ ቀዳሚው ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው። ክለቡ በ2000 አንድም ጨዋታ ሳይሸነፍ ዋንጫ በማንሳት ብቸኛው ባለታሪክ ነው።
12 – በሊጉ ብዙ ነጥቦችን እስካሁን የሰበሰበ ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው። ቡድኑ ከ1991 ዓ/ም ጀምሮ ባደረጋቸው 565 ጨዋታዎች 1184 ነጥቦችን በማግኘት የሊጉ የእስካሁን ዓመታት የደረጃ ሰንጠረዥ መሪ ነው። (የ2012 የሊጉ ጨዋታዎች እና ውጤቶች ስለተሰረዙ በዚህ እውነታ ውስጥ አልተካተቱም)
13 – በእስካሁኑ የሊጉ ታሪክ ብዙ ጎሎችን ተጋጣሚ ላይ በማስቆጠር ቀዳሚ የሆነው ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው። ክለቡ በ565 ጨዋታዎች 950 ግቦችን ተጋጣሚ ላይ አስቆጥሯል።
14 – ከ1990 ጀምሮ ብዙ ዋንጫዎችን ያነሳ ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው። ቡድኑ 14 ዋንጫዎችን ከተሳተፈባቸው 21 ዓመታት ሰብስቧል። ከቅዱስ ጊዮርጊስ በመቀጠል መብራት ኃይል እና ሀዋሳ ከተማ 2 ጊዜ ዋንጫዎች በማንሳት ይከተላሉ።
15 – በሊጉ በርካታ ጨዋታዎችን የተጫወቱት ክለቦች ኢትዮጵያ ቡና እና ሀዋሳ ከተማ ናቸው። እነዚህ ሁለት ክለቦች ከ1990 ጀምሮ 580 ጨዋታዎችን በሊጉ አድርገዋል። ከዚህ በተጨማሪም ሁለቱ ክለቦች ሊጉ ከተጀመረ በኋላ ያልወረዱ ብቸኞቹ ክለቦች ናቸው።
* በዚህ አምድ ቀጣይ ክፍል ተጨማሪ የሊጉ ዕውነታዎችን አጠናቅረን በቀጣይ ሳምንት ይዘን የምንቀርብ መሆኑን ከወዲሁ እንገልፃለን።
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ