“የካዛብላንካው ድራማዊ ምሽት” ትውስታ በደሳለኝ ገብረጊዮርጊስ አንደበት

በቀደመ ዘመን ከሀገር ወጥቶ መጥፋት በተለመደበት የኢትዮጵያ እግርኳስ ለዓለም ዋንጫ ማጣርያ የምድብ ጨዋታውን ለማድረግ ወደ ሞሮኮ ተጉዞ ድራማዊ ክስተት ስላስተናገደው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን፣ ስለጠፉት ተጫዋቾች እንዲሁም በተጫዋቾች እጥረት ምክንያት አሰልጣኙ አጥቂ፣ ግብጠባቂው ደግሞ አማካይ ሆነው ስለተጫወቱበት አስገራሚ ክስተት በትውስታ አምዳችን ይዘን ቀርበናል።

ወቅቱ 1985፤ ውድድሩ ደግሞ በዩናይትድ ስቴትስ በሚስተናገደው 15ኛው የ1994 ዓለም ዋንጫ የሚያልፉ ሦስት የአፍሪካ ቡድኖችን ለመለየት የሚደረግ የማጣርያ ውድድር ነበር። ኢትዮጵያ በምድብ 6 ከሞሮኮ፣ ቱኒዚያ እና ቤኒን ጋር ተደልድላለች። የመጀመርያ ጨዋታዋም ከጠንካራዋ ሞሮኮ ጋር መሆኑን ተከትሎ 16 ተጫዋቾች፣ አሰልጣኝ፣ ቡድን መሪ እና የህክምና ባለሙያ ጨምሮ በድምሩ 20 አባላት በመያዝ ወደ ሞሮኮ ጉዞ ጀምሩ። በወቅቱ የቀጥታ በረራ ወደ ሞሮኮ ባለመኖሩ ለትራንዚት ጣልያን ሮም አርፈዋል። በዚህም ጠዋት ከእንቅልፋቸው ተነስተው ልምምዳቸውን በሚገባ ሠርተው፣ ቁርስ በልተው በቂ እረፍት አድርገው ለምሳ እንዲገናኙ ቀጠሮ ይዘው ወደ ማረፊያ ክፍላቸው ያመራሉ። የምሳ ሰዓት ደርሶ መሰባሰብ ሲጀምሩ ግን ከመካከላቸው ስድስት ተጫዋቾች ከሆቴሉ መጥፋታቸው ታወቀ።

በዚህ ሁኔታ ግራ የተጋቡት የቡድኑ አባላት አዲስ አበባ ለሚገኘው የፌዴሬሽኑ አባላት መልዕክት በፋክስ ሪፖርት ያደርጋሉ። ” ከአስራ ስድስት ተጫዋቾች መካከል ስድስቱ ጠፍተዋል፤ በቁጥር አንሰናል፤ ምን እናድርግ?” በማለት ይጠይቃሉ። ከፌዴሬሽኑ የደረሳቸው መልዕክት ግን “አይዟቹ በርቱ፣ ቀጥሉ…” የሚል አጭር መልዕክት ብቻ ነበር። ቡድኑም መልዕክቱን ተቀብሎ ወደ ሞሮኮ ትልቋ ከተማ ካዛብላንካ ገባ።

ጥቅምት 1 ቀን 1985 የጨዋታው ቀን ደርሰ። በተጫዋቾቹ መጥፋት ምክንያት መጫወት የሚችሉ ሁለት ግብ ጠባቂዎች እና ስምንት የሜዳ ላይ ተጫዋቾች ብቻ የያዘው ቡድን በተሟላ ሁኔታ ወደ ሜዳ የሚገባበትን መላ ዘየደ። በዚህም የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ካሣሁን ተካ አጥቂ፣ ግብጠባቂው ደሳለኝ ገ/ጊዮርጊስ ደግሞ አማካይ ሆነው እንዲጫወቱ ተወስኖ ወደ ሜዳ ገቡ። ወትሮውንም ጠንካራ የሆኑት ሞሮኮዎች ገና በሁለተኛው ደቂቃ በመሐመድ ቻውች ጎል መሪ ሆኑ፤ ቀጥሎም ሁለት .. ሦስት … እያለ ጎሎች መዝነብ ጀመሩ። የኢትዮጵያ ተጫዋቾችም ድራማዊ በሆነ ሁኔታ በጉዳት ቁጥራቸው እየቀነሰ 50ኛው ደቂቃ ላይ ደርሶ ሞሮኮ አምስተኛውን ጎል ካስቆጠረች በኋላ ሜዳ ላይ የሚገኙ ተጫዋቾች ቁጥር 7 ብቻ በመድረሱ ተቋረጠ። የዚህ ድራማዊ ክስተት አባል የነበረው ደሳለኝ ገብረ ጊዮርጊስ በዛሬው የትውስታ አምዳችን ወደ ኃላ 27 ዓመት መልሶን በወቅቱ የተፈጠረውን ሁኔታ እንዲህ አጋርቶናል።

“ሁሌም ይህን ነገር ወደ ኋላ ዞር ብዬ ሳስታውሰው ድህነታችን ነው ትዝ የሚለኝ። አቅም ቢኖረን በቁጥር በዛ ብለን በሄድን ነበር። አስታውሳለው ሁለት ግብጠባቂ እና 14 ተጫዋቾችን ይዘን ማክሰኞ ቀን ሮም ገባን። ረቡዕ ጠዋት ልምምድ ሠርተን ቁርስ በልተን ለእረፍት ወደ ክፍላችን ለመግባት ከተለያየን በኋላ ለምሳ ስንመጣ ስድስት ተጫዋቾች መጥፋታቸውን አረጋገጥን። ምን ይሻላል..? በዘጠኝ ተጫዋች ምን እናደርጋለን? ወደ ሀገር ቤት እንመለስ? ወይስ እንጫወት? እያልን ነው። ምክንያቱም ከቀረነው አስር ተጫዋቾች እኔ እና ይልማ ከበደ (ጃሬ) ግብጠባቂዎች ነን። ስለዚህ ሳንሟላ መጫወት አንችልም ብለን መልዕክት በፋክስ በቡድን መሪው አማካኝነት ወደ አዲስ አበባ ተላከ። አስታውሳለው የመልዕክቱ መልስ ሲመጣ አይቸዋለው “በርቱ አትመለሱ ቀጥሉ” የሚል ነበር። በየትኛውም መንገድ ተጨማሪ ተጫዋቾች ተልኮ ቡድኑን እንዲቀላቀሉ ማድረግ ስለማይቻል። በሁኔታው ተገርመን እየሳቅን ሐሙስ ሌሊት ሞሮኮ ካዛብላንካ ኤርፖርት ደረስን። አቀባበል ለማድረግ የመጡ የሞሮኮ ፌዴሬሽን አመራሮች “እንዴ? እናንተ ብቻ ናችሁ? ብለው ሲጠይቁን “አይ ፕሮፌሽናል ስለሆኑ ይመጣሉ።” ብለን ሆቴል ገባን። ቅዳሜ ከጨዋታው አስቀድሞ ጠዋት ቅድመ ስብሰባ እያደረግን ባለንበት ሰዓት አንድ ኢትዮጵያዊ በሞሮኮ የተባበሩት መንግስታት የሚሰሩ አባል 300 ኪሎ ሜትር አቋርጠው ጨዋታውን ለማየት ሆቴል ድረስ መጥተዋል። በስብሰባው ላይ የሚባለውንም ይሰማሉ። አሰልጣኝ ካሳሁን ተካ ቡድኑን እያበረታታ አሰላለፍ ያወጣል። “ግብ ጠባቂ ይልማ ከበደ (ጃሬ)…” እያለ ተሰላፊዎችን መናገር ጀመረ። “መሐል ላይ የቡድኑ ወሳኝ አማካይ ደሳለኝ ገ/ጊዮርጊስ፣ አጥቂ እኔ ራሴ ካሣሁን ተካ…” ሲል ሊደግፉ የመጡት ሰውዬ እንባቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው በሳቅ ሞቱ። “እንዴ ምንድነው እንደዚህ?” ብለው ሲጠይቁ ምክንያቱን እና ያጋጠመንን ችግር ያለውን ነገር አስረዳናቸው። እርሳቸውም በርቱ አሉን።

” ጨዋታው ደርሶ ወደ ሜዳ ገባን ነፍሱን ይማረው ተስፋዬ ኡርጌቾ የመስመር ተከላካይ ግራ ተከላካይ ኤርሚያስ ተፈሪ እነ ጠንክር አስናቀ፣ ሙሉጌታ ከበደ እኔ እና ካሳሁን ተካ ወደ ፊት ሆነን ግብጠባቂ ጃሬ ሆኖ ጨዋታው ተጀመረ። ሞሮኮዎች የጎል ዝናብ መዝነብ ጀመሩ በመጀመርያው አጋማሸ የተጎዳቹ መስላቹ ውጡ ሲባል ማቲያስ የሚባል ተጫዋች አንወጣም እንጫወት አለ። እሺ ብለን ቀጥለን አራት ጎል ገባ በዚህ ሰዓት ጃሬ ተጎዳው ብሎ ወጥቶ በዛው መልበሻ ክፍል ገብቶ ሳይመለስ በዛው ቀረ፣ በመቀጠል ካሣሁን ተካም በተመሳሳይ ተጎዳሁ ብሎ እርሱም ቀረ። ከእረፍት መልስ በዘጠኝ ተጫዋቾች ወደ ሜዳ ገባን። እኔ ግብጠባቂ እና ተከላካይ ሆኜ እየተጫወትኩ ቀጠልን። ጠንክር አስናቀ አዲስ አበባ እያለ ቡጉንጅ ወጥቶበት ነበር። ሆኖም ጨዋታው ላይ እንደተጎዳ አድርጎ ኡ ኡ ኡ እያለ እየጮህ ይወጣል፣ በዛውም ይቀራል፤ ስምንት ሆንን። አንድ ሰው ይቀራል ጨዋታው እንዲቋረጥ። ሆኖም ማትዮስ ተጎዳው ብሎ ሊወጣ ሲል ዳኛው ጨዋታውን አቋርጠን ልንወጣ እንደሆነ ስለተረዳ ተነስ ተጫወት እያለ የህክምና ቃሬዛ እንዳይገባ ይከለክላል። ቃሬዛ የያዙት ይገቡና ማትዮስን ይዘውት ይወጡና ደግሞ ይመልሱታል። ጨዋታው ሊቋረጥ ሲል እኔ ላይ እስካሁን ትገርመኛለች በጣም የምታስቅ አምስተኛ ጎል ገባብኝ። አስታውሳለው ዳኛው ፈረንሳይኛ ካልሆነ በቀር እንግሊዘኛ አይችልም። በቃ ሙሉጌታ ከበደ እየሄደ በምልክት ያወራው ነበር። በዚህ አጋጣሚ አንድ ተጫዋች ይጎዳል። ውስጥ የቀረነው ውጣ አትውጣ እያለን ከዳኛው ጋር ስንከራከር የህክምና ቃሬዛ ሁሉ ሜዳ ገብተዋል እኮ። እኔም ጎል ውስጥ የለሁም፤ መሐመድ ሳማዲ በቀጥታ ወደ ጎል መቶት አምስተኛ ጎል ሆኖ ተመዘገበ። ቀጥሎም ማቲያስ ተጎድቶ ስለወጣ ጨዋታው ከዚህ በኃላ በሰባት ተጫዋቾች መቀጠል ስለማይችል 5-0 በሆነ ውጤት ተሸንፈን ጨዋታው ሳያልቅ ተቋርጦ ለመጠናቀቅ ችሏል።

” በጣም የሚገርምህ በምድቡ ሌላ ጨዋታ ከቱኒዚያ ጋር ቱኒዝ ላይ ልንጫወት ሄደን የተፈጠረው ነገር በጣም የሚያስቅ ነበር። ጨዋታው ከእኛ ይልቅ ለቱኒዚያ በጣም አስፈላጊ ነበር። የመጨረሻውን ጨዋታ በሞሮኮ ጋር የሚያደርጉ በመሆኑ ብዙ ጎል በማግባት እነሱን መብለጥ ይፈልጋሉ። እኛ ደግሞ ወጥረን ያዝናቸው። አስበው እንዴት ሞሮኮ አምስት አግብታ እኛ ማግባት ያቅተናል ብለው ተናደው ባለበት ሰዓት ሙሉጌታ ከበደ የእኛ መልበሻ ክፍል የገባ መስሎት ለምን እነርሱ ክፍል አይገባም! አገኙታ… (እየሳቀ) መቀመጫውን ሁሉ ሳይቀር የሻሞ ደበደቡት ሙልጌታ ኡ ኡ ኡ እያለ ሲጮህ አይ ጉርምስና…( እየሳቀ) ይገርምሀል እሱን ለማዳን ወደ እሱ እየሮጥኩ “ሙሉጌታ ምን ሆንክ?” ስለው “መቱኝ፣ ደበደቡኝ” አለኝ። ስሮጥ ያደረኩት ብሎን ጫማ ነበር። ተንሸራትቼ እኔ ራሴ መልበሻ ክፍል ውስጥ ገባሁ (እየሳቀ)። እና እልሀለው ነገሩ ተረጋግቶ ጨዋታው የቀጠለበት ገጠመኝን አረሳውም።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ