አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ከፕሪምየር ሊግ አሰልጣኞች ጋር ተወያዩ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ እና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም በሚል ርዕስ በተጨማሪም ሌሎች ሀሳቦችን ያዘለ የቪዲዮ ኮንፈረንስ በአሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ አማካኝነት ከፕሪምየር ሊግ አሰልጣኞች ጋር ዛሬ ረፋድ ውይይት ተደርጓል፡፡

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ የሚገኙ ሁሉም አሰልጣኞችን ተሳታፊ ባደረገው የዛሬው ውይይት ላይ እንደ ብሔራዊ ቡድን ውይይቱን የመሩት አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ሲሆኑ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ቴክኒክ ዳይሬክተሩ አቶ መኮንን ኩሩም የውይይቱ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ በስፋት በውይይቱ ላይ አሰልጣኞች ራሳቸውን በቴክኖሎጂ ማሳደግ እንዳለባቸው እና ኮሮና ጥላ ያጠላበትን የኢትዮጵያ እግርኳስ በቀጣይ በምን መልኩ ማስኬድ አለባቸው በሚሉ ጉዳዮች ላይ በዋናነት ያጠነጠነ ውይይት ነበር፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በአሰልጣኞቹ መሀል የተደረገው ውይይት ላይ አሜሪካ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ከሰዓት መዛባት ጋር በተገናኘ ዘግይቶ ውይይቱን የተቀላቀለ ሲሆን የስሑል ሽረው አሰልጣኝ ሲሳይ አብርሀም ደግሞ በኔትወርክ ችግር ምክንያት ውይይቱን በተወሰነ መልኩ እንዳቋረጡ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡

አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ በሀገራችን ያሉ አሰልጣኞች በተለይ የፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ የሆኑ ዓለም እያደገ በቴክኖሎጂም ራሱን እያጎለበተ በመምጣቱ ሁሉም ይሄን መከተል እንዲችሉ ከቴክኖሎጂ ጋር በተገናኘ ያለውን ሀሳብ በማብራሪያ መልክ አቅርበዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የኮሮና ወረርሽን በፈጠረው ስጋት በሀገራችን ያሉ የሊግ ውድድሮች በመቋረጣቸው እግር ኳሳችን የቆመ ሲሆን አሰልጣኞች የኢትዮጵያን እግር ኳስ ዕጣ ፈንታ እያሰቡ ለቀጣይ በምን መልኩ ራሳቸውን ማዘጋጀት እንዳለባቸውም በውይይቱ ተነስቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አዳዲስ ሀሳቦችን አሰልጣኞች ቤት ውስጥ ባሉበት ጊዜ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ይበጃል የሚሉትን በምን መልኩ ይዘው መቅረብ አለባቸው በሚሉት ጉዳዮችም ላይ በጥልቀት የፕሪምየር ሊጉ አሰልጣኞች አንስተው ተነጋግረውበታል፡፡ በተነሱት ሀሳቦች ላይም ሁሉም አሰልጣኞች የራሳቸውን ምልከታ በማስቀመጥ ሀሳቦችን አንሸራሽረዋል፡፡

የሲዳማ ቡናው አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ፣ የስሑል ሽረው ሲሳይ አብረሀም እና የሀዲያ ሆሳዕናው አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት ይህ በጎ ጅምር ሊለመድ እንደሚገባው እና አሰልጣኞች ለሀገራችን እግር ኳስ ዕድገት በዚህ አስከፊ ጊዜ ሀሳብ ማንሸራሸራቸው እጅግ አስመስጋኝ መሆኑን ገልፀውልናል፡፡ አሰልጣኞችም አብርሀም መብራቱ የፈጠሩላቸውን መልካም የግንኙነት መንገድ በማድነቅም አመሰግነዋል፡፡

አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ እንደገለፁት ከሆነ የፊታችን ዕሮብ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተገናኘ ከእግር ኳስ አሰልጣኞች ምን ይጠበቃል በሚል ጉዳዮች ላይ ምሽቱን የቪዲዮ ስብሰባ ይደረጋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በፕሪምየር ሊግ አሰልጣኞች መካከል የጀመረው ይህ ውይይት ወደፊት በሴቶች ፕሪምየር ሊግ በከፍተኛ ሊግ እንዲሁም በአንደኛ ሊግ ላይ ያሉ አሰልጣኞች መካከል እንደሚደረግም ሰምተናል፡፡

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ