“ወደፊት በቋሚነት ለሀገሬ መጫወት እፈልጋለሁ” ተስፈኛው ግብ ጠባቂ ጆርጅ ደስታ

ዘንድሮ በፕሪምየር ሊጉ በወልቂጤ ከተማ የሚገኘው ግብ ጠባቂው ጆርጅ ደስታ በዛሬው የተስፈኛ አምዳችን ላይ ተመልክተነዋል፡፡

ተወልዶ ያደገው ባቱ(ዝዋይ) ከተማ ነው፡፡ አሰልጣኝ እዮብ ሊፒ እና ራህመቶ በሚያሰለጥኑት ዝዋይ ፕሮጀክት ውስጥ ነበር በተከላካይነት እግርኳስን መጫወት የጀመረው። በዚህ ሁኔታ አንድ ቀን ላይ ከቡድናቸው መሐል ግብ ጠባቂ ሆኖ የሚጫወተው የፕሮጀክታቸው አባል በመቅረቱ ለዛች የልምምድ ወቅት ብቻ ግብ ጠባቂ ሆኖ ተጫወተ። በድንገት የገባበት ግብ ጠባቂነትም ለሱ መልካም ሆነለትና የጓደኞቹ ምክር ታክሎበት በግብ ጠባቂነቱ ፀንቶ ቀረ።

ያኔ የጀመረው የጆርጅ ደስታ የግብ ጠባቂነት ህይወት እያደገ እየመጣ ባሳየውም አስደናቂ ብቃት በተደጋጋሚ የትውልድ አካባቢውን እንዲሁም ደግሞ ኦሮሚያ ክልልን የመወከል አጋጣሚን አግኝቶም ተጫውቷል፡፡ ሙገር ቢ ከ2007 እስከ 2008 በታዳጊ እድሜው ቆይታን ያደረገ ሲሆን ታዳጊን በማፍራት የማይታማው የያኔው ሙገር ሲሚንቶም ለጆርጅ ትልቅ የትምህርት ማዕከልም ሆኖታል፡፡ በ2009 በሙገር ዋናው ቡደን የማደግ ዕድልን ቢያገኝም በቤተሰብ ናፍቆት የተነሳ ወደ ትውልድ ከተማው ተመልሶ ለባቱ ከነማ ጥቂት ጊዜን ብቻ ካሳለፈ በኃላ የገጠመው ጉዳት ለጥቂት ጊዜ በቤት ለማሳለፍ ተገደደ። ተስፋ ያልቆረጠው ወጣቱ ግብ ጠባቂ ግን ከህመሙ ካገገመ በኃላ በአርሲ ነገሌ እና ቡታጅራ ከተማ እንዲሁም አምና በ2011 በከፍተኛ ሊጉ መድን ሲጫወት ቆይቷል፡፡ በመድን ቆይታው የ2011 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ኮከብ ግብ ጠባቂ በመባል የተሸለመው ይህ ተስፈኛ ዘንድሮ በፕሪምየር ሊጉ ክለብ ወልቂጤ ከተማ እየተጫወተ የሚገኝ ሲሆን ምንም እንኳን የክለቡ ሦስተኛ ግብ ጠባቂ መሆን ቢችልም አልፎ አልፎ በቆሚነት ሲሰለፍ የሚያሳየው ብቃትም አስገራሚ ነው፡፡ ተጫዋቹም በዛሬው የተስፈኛ አምዳችን እንግዳ ነው።

“የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ በለጠ ወዳጆ እና ለኔ አርአያ የሆነኝን ተክለማርያም ሻንቆን ማመስገን እፈልጋለሁ። በለጠ ወዳጆ ይመክረኝ እና ያበረታታኝ ስለነበር ዕድገቴ እየፈጠነ መጥቷል። ተክለማርያም ሻንቆ ሲጫወት እሱን እያየሁ ልክ እንደሱ መሆን እፈልግ ነበር። ሲጫወት በጣም ደስ ይለኛል። እንደውም ብዙዎቹ እሱን አይቼ ነው እዚህ የደረስኩት ስላቸው አንተ የተክለማርያም (ጎሜዝ) ተተኪ ነህ ይሉኛል። እሱን በጣም አደንቀዋለሁ፡፡

” አምና መድን እያለው ነው ለጨዋታ ክልል ሄደን ነበር። ያሬድ የሚባል ግለሰብ ከፌዴሬሽን ደውሎ የከፍተኛ ሊግ ኮከብ ግብ ጠባቂ እጩ ውስጥ አለህ አለኝ። እኔ ግን እውነት አልመሰለኝም፤ አጥብቆ ሲነግረኝ ሽልማቱ ትልቅ ስለነበረ አሁንም ለእኔ እውነት አልመስል አለኝ። እሱም መልሶ ጆርጅ በትኩረት እየው ካፒታል ሆቴል ነው የሽልማት ዝግጅቱ አለኝ። እኔም ትልቅ ስሜት በሰአቱ ተሰማኝ። ሽልማቱንም ካገኘሁ በኃላ ከምነግርህ በላይ ውስጤ ላይ የተለየ ስሜት ተሰማኝ።

” በመድን አንድ ዓመት ብቻ ብቆይም ክለቡን በጣም ማመስገን እፈልጋለሁ። እኔ ልሸለም እንጂ መድን ፕሪምየር ሊግ ሳይገባ መቅረቱ ረብሾኝ ነበር። በጥቃቅን ስህተት ነው ያን እድል ያጣነው። አቻ ስንወጣ እንኳን እንናደድ ነበር። እስከ መጨረሻው ድረስ ሄደናል። ይሄ እግር ኳስ ነው፤ የእድልም ጉዳይ ነው፡፡

” አሁን ወልቂጤ ነኝ። ለሀገራቸው ጭምር የተጫወቱ ሁለት ልምድ ያላቸው ግብ ጠባቂዎች ከእኔ ጋር አሉ። ሜንሳህን ከዚህ በፊት ሀዋሳ ሲጫወት በአጋጣሚ አይቼዋለሁ። በጣም ጎበዝ ነው፤ ይድነቃቸውንም አይቸዋለሁ። እነሱ ለእኔ ወንድሞቼ እንጂ የስራ ጓደኞቼ አይደሉም። ይድነቃቸው እንደ ታላቅ ወንድም ይመክረኛል። አንድ ዓመት ከእነሱ ጋር በመሆኔ ደስተኛ ነኝ። ሁለቱም ትልቅ ቦታ እንድደርስ በጣም ያበረታቱኛል። የሚጎለኝን ከእነሱ እያየሁ ከፈጣሪ ጋር ለመሙላት እታገላለሁ፡፡

“በኦሊምፒክ እና ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ነበርኩ። ወደፊት በቋሚነት ተሰልፌ ለሀገሬ መጫወት ፈልጋለሁ። የፕሪምየር ሊጉ ኮከብ ለመሆንም ጠንክሬ እሰራለሁ። ከጎኔ እናት እና አባቴ አሉ፤ ግን እናቴ ሁሌም ከጎኔ በመኖሯ ነው ለዚህ የበቃሁት። ለኔ ትጨነቃለች፤ ለእኔ እዚህ መድረስ ትልቅ ቦታ አላት። ለዝዋይ ልጆች እና ወደ ውድድር እንድገባ ላደረገኝ ዳዊት ሀብታሙም ምስጋናዬ ይድረስልኝ”፡፡

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ