ሁለት የሀገራችን ኢንስትራክተሮች የተሳተፉበት የካፍ ኢንስትራክተሮች ስብሰባ በቪዲዮ ኮንፈረንስ ታግዞ ዛሬ ለሦስተኛ ጊዜ ተደርጎ ተጠናቀቀ፡፡
ኮቪድ 19 ወረርሺን በመላው የዓለም ሀገራት ከገባ በኃላ እግር ኳስን ለመከናወን እጅግ አዳጋች በመሆኑ በርካታ ሀገራት ሊጋቸውን ለመሰረዝ ተገደዋል፡፡ ይሁን እና ይህ አስከፊ በሽታ ቀጣይነቱ የማይታወቅ በመሆኑ የአፍሪካ ሀገራት እግር ኳስን ከዚህ አስከፊ በሽታ ጎን ለጎን በቀጣይ ጊዜያት በምን አይነት መልኩ ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው የሚሉ ሀሳቦችን እና በርካታ ጉዳዮችን የያዘ ስብሰባ ካፍ ለአባል ሀገራት ላሉ ወንድ እና ሴት ኢንስትራክተሮች ጋብዞ በዛሬው ዕለት ለሦስተኛ ጊዜ ውይይት በማድረግ አጠናቋል፡፡
ከሀምሳ በላይ የካፍ ኢንስትራክተሮች በሁለቱም ፆታ በተሳተፍበት የዛሬው ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ እና ኢንስትራስተር ሠላም ዘርዓይ ከኢትዮጵያ በቪዲዮ ኮንፈረንሱ ላይ ተሳታፊ መሆናቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡ ውድድሮች በኮሮና ስጋት በመቋረጣቸው ካፍ ውድድሮችን መልሶ ለማስጀመር እና ወደ ልምምድ በምን መልኩ ክለቦች እና ተጫዋቾች መግባት አለባቸው ለሚሉ ጉዳዮች ይረዳ ዘንድ በዋናነት ዶክመንትን ለማዘጋጀት ለግብዓት የሚሆኑ ፍሬያማ ሀሳቦችን ለማግኘት ታስቦ እንደተዘጋጀ ተሰምቷል፡፡ የካፍ ሜዲካል ኮሚቴ፣ ቴክኒክ እና ዴቨሎፕመንት ኮሚቴ እንዲሁም የኤሊት ወንድ እና ሴት ኢንስትራክተር ኮሚቴዎች በዋናነት የስብሰባው አካል እንደነበሩ ለማወቅ ችለናል፡፡
ውድድሮችን ለማስጀመር ውጥን ያለው ካፍ ቴክኒካል የሆኑ እና ጥልቅ የሆኑ መረጃዎችን በውይይቱ እንዳገኘም ጭምር ተሰምቷል፡፡ ከላይ ከጠቀስናቸው ጉዳዮች በተጨማሪ ደግሞ አሰልጣኞችስ በዚህ አስከፊ ጊዜ ልምምድ በምን መልኩ ማሰራት እንደሚችሉ እና ወደ ውድድር ለመግባትስ በምን አካሄድ መሄድ አለባቸው ሀገራትስ ሀገራትስ ምን ምን ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት እንዳለባቸው በቪዲዮ ኮንፈረንሱ ተነስቷል፡፡
ካፍ ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ በተመሳሳይ ውይይትን ከኢንስትራክተሮቹ ጋር ያደረገ ሲሆን ይህ የመጨረሻው እንደሆነ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡ ተሳታፊዎችም የራሳቸውን እና የወከሉትን ሀገራት በተመለከተ አስተያየት የሰጡ ሲሆን ኢንስትራክተር አብርሀም መብራቱ እና ሰላም ዘርአይም ሀሳባቸውን ለስብሰባው አካፍለዋል፡፡ በስፋት ቴክኒካዊ ነገሮች ላይ አተኩሮ የተደረገው ስብሰባ በዶክመንት መልክ ተዘጋጅቶ ሀገራት ተፈፃሚ እንዲያደርጓቸው በሰነድ መልክ እንደሚቀርብም ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ