የቤተሰብ አምድ | ከትንሽ ወረዳ ተነስተው ለስኬት የበቁት የሸመና ልጆች

አራት ወንድማማቾችን ያፈራው እና ሁለቱን ለስኬት ያበቃው የሸመና ቤተሰብ የዛሬ ትኩረታችን ነው።

መነሻቸው ጋሞ ጎፋ ዞን ጨንቻ እየተባለች በምትጠራ ትንሽ ወረዳ ውስጥ ነው፡፡ የቤተሰባቸው ቁጥር ዘጠኝ ይደርሳል፤ ሦስቱ ሴቶች ሲሆኑ የተቀሩት ደግሞ ወንዶች፡፡ ከቤተሰቡ ውስጥ አራቱ ከእግር ኳስ ጋር ንክኪ የነበራቸው ሲሆን የሁለቱ ትዝታ ግን ዛሬም ድረስ ላይረሳ በብዙዎች ልቦና ውስጥ ታትሞ ይገኛል፡፡ የቤቱ ታላቅ ደረጀ ሸመና ይባላል። እግር ኳስን ሀ ብሎ በመጀመር መንገዷን ለቤተሰቡ ያመቻቸ ጠንካራ ተከላካይ እንደነበር ወንድሞቹ ይመሰክሩለታል። በ1970ዎቹ ለባህር ትራዚንት ሲጫወት ከቆየ በኋላ ወደራሱ የግል ሙያ በመሰማራቱ ኳስን ለታናሹ ሰለሞን ሸመና አስተላልፎለታል። ሰለሞንም በኪራይ ቤቶች የእግር ኳስ ቡድን ውስጥ በአጥቂ ስፍራ ላይ ተጫውቶ አሳልፏል፡፡

ሦስተኛው ከእግር ኳስ ጋር የተዋወቀው መለሰ ሸመና ግን ታሪክ የማይዘነጋውን ትልቅ አሻራ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ አሳርፏል፡፡ እግር ኳስን የጀመረው በለጋ ዕድሜው ነው፤ ተማሪ እያለ በትውልድ ከተማው ጨንቻ እጅግ ጎበዝ ተማሪም ነው፡፡ ከትምህርቱ ጎን ለጎን እግር ኳሱን በሚገባ እያስኬደ ለትምህርት ቤት፣ በቀድሞው አጠራር ለጋሞ ጎፋ ዞን አውራጃ እና ለክልል ምርጥ በመሐል አማካይነት መጫወት ችሏል፡፡ በተጫዋችነት ዘመኑ በአርባምንጭ እርሻ ልማት እግር ኳስ ክለብ ውስጥ 1980ዎቹ አጋማሽ እየተጫወተ የስፖርት መምህርነትንም ጎን ለጎን ያስኬድ ነበር። በዚህ ወቅትም ቀጣዩን ተተኪ የያኔውን ተማሪ ገረሱ ሸመናን ኳስ ተጫዋች ሆኖ ለማየት በመፈለጉ እዚህ ቡድን ውስጥ ቀላቀለው ፤ ሁለቱ ወንድማማቾችም በአንድ ክለብ ውስጥ አብሮ የመጫወት አጋጣሚን አገኙ።

“የዛን ጊዜ የነበረው ድባብ ጥሩ ነበር። እኔ የመጣሁት ከገጠር ነበር ፤ ትንሽ ኳስን የመጫወት ችሎታውም ነበረኝ። ባሳየሁትም ብቃት አርባምንጭ እርሻ ልማት ተጫዋች አድርጎ ቀጠረኝ። የተቀጠርኩት ደግሞ በደመወዝ ሳይሆን በቤት ኪራይ ነው ፤ ክለቡ በየወሩ የቤት ኪራይ ይከፍልልኛል። ወንድሜ ገረሱ ደግሞ ተማሪ ነበር። እሱን ከጨንቻ ያመጣሁ አብሮኝ እንዲኖር ነበር። ግን ትምህርቱን እየተማረ አብሮኝ እንዲጫወት አደረኩ። እኔ እና እሱ አንድ ሜዳ ላይ ስንሆን በሚገባ ነበር የምንግባባው። በዋናነት ቦታዬ መሀል ላይ ቢሆንም ቡድኑ ሲቸገር አጥቂ ቦታ ላይም እገባለሁ ፤ ተከላካይም ሆኜ ተጫውቻለሁ። በዚህ ሁሉ ውስጥ ከወንድሜ ጋር ያሳለፍኩት የጨዋታ ጊዜ መልካም ነበር።” በማለት ሁለቱ ወንድማማቾች አብረው ስለተጫወቱበት ጊዜ አሰልጣኝ መለሰ ሸመና ይገልፃሉ፡፡

ኳስን ከመጫወት ጎን ለጎን እንደ ኳሱ የሚወደውን የስፖርት መምህርነትን ሙያን ሲሰራ የነበረው መለሰ አራት ተከታታይ ዓመታትን (1986-89) ለእርሻ ልማት በመጫወት ካሳለፈ በኋላ መጫወትን በማቆም ወደ ማሰልጠን ሙያው ፊቱን አዞረ፡፡ ኳስን ካቆመ በኋላ ታዳጊዎችን በመሰብሰብ አርባምንጭ ከተማ ላይ ማሰልጠን የጀመረው አሰልጣኝ መለሰ በፕሮጀክት ታዳጊዎችን እያሰለጠነ ሳለ 1991 ላይ አርባምንጭ ጨርቃ ጨርቅን በዋና አሰልጣኝነት ለመያዝ ዕድሉን አገኘ። አሰልጣኝ መለሰ ቡድኑን ከተረከበ በኃላ ግን ተጫዋች ከመመልመል ይልቅ በፕሮጀክቱ ስር ይሰለጥኑ የነበሩትን አስራ ሰምንት ተጫዋቾች በሙሉ በመያዝ ወደ ቡድኑ ቀላቀላቸው።

“ልጆቹ ከእኔ ጋር ያደጉ ስለነበሩ ብዙም የቸገረኝ ነገር የለም። ከእኔ ጋር ስለቆዩ ይግባባሉ፤ ያዳምጡኛልም። እኔም አቅሜ በሚችለው መልኩ ለማሰልጠን ጥረት አደርግ ነበር። ወደ ውድድር ስንገባ ትንሽ ልጆችም ስለነበሩ ድንጋጤ እንዳይኖር አስተምራቸው ነበር። በወቅቱም የአርባምንጭ ውሀ ኤኒስቲቲዩት ምሁራንም ይረዱኝ ነበር ፤ በሥነ ልቦናም ልጆቹን ያግዙልኝ ነበር። ከዛ ወደ ውድድር ገባን። በመጀመሪያው ዓመት የክልል ጥሎ ማለፍ ቻምፒዮን ሆንን። በሁለተኛው ዓመት ደግሞ ወደ ብሔራዊ ሊግ ለመግባት ክልሉን ወክለን በኢትዮጵያ ቻምፒዮና ላይ ተሳተፍን ሦስተኛ ሆነን ወደ ብሔራዊ ሊግ ገባን። ከልጆችም ጋር ቃል ተገባብተን ወደ ፕሪምየር ሊግ እንገባለን ተባብለን ነበር። ያም ተሳክቶ 1994 ላይ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ገባን። ” በማለት የክለብ አሰልጣኝነት ጅማሬያቸውን ዘርዘር በማድረግ ይገልፃሉ፡፡

በወጣቶች የተገነባው የወቅቱ አርባምንጭ ጨርቃ ጨርቅን አሰልጣኙ ወደ ፕሪምየር ሊጉ 1994 ላይ ካሳደጉት በኃላ ጠንካራ የክልል ቡድን እንዲሆንም አስችለውታል፡፡ በተለይ ወደ ሊጉ ካደገ ከአንድ ዓመት ቆይታ በኃላ 1995 ላይ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ከጫፍ ቢደርስም በመጨረሻው ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ ተነጠቀ እንጂ አሰልጣኝ መለሰ የሰሩት ጠጣር ቡድን የብዙዎችን ትኩረት እንዲስብ ሆኖ ነበር፡፡ በቀጣይ ዓመት ደግሞ የአሰልጣኝ መለሰ ሸመናው አርባምንጭ ጨርቃጨርቅ አጥቂ መሳይ ተፈሪ በኮከብ ግብ አግቢነት ከታፈሰ ተስፋዬ ጋር በጋራ ተሸልሟል፡፡ አሰልጣኙም ይህን ቡድን ከያዙ በኃላ በርካታ ተጫዋቾችን በማፍራት እስከ ብሔራዊ ቡድንም በማድረስ የጎላ ሚናን ተወጥተዋል፡፡ ደጉ ደበበ ፣ አበባው ቡታቆ ፣ አዱኛ ገላና ፣ መኮንን ገላና (ዊሀ) ፣ መሳይ ተፈሪ ፣ እዮብ ማለ ፣ ስለሺ ጌታቸው ፣ ዓለማየሁ አባይነህ (አሌኮ) እና በረከት እንዲሁም ሌሎች በርካታ ተጫዋቾችን በሀገራችን እግር ኳስ የተሻለ ደረጃ እንዲደርሱ አድርገዋል፡፡

አሰልጣኝ መለሰ ሸመና በአርባምንጭ ጨርቃጨርቅ ደማቅ ታሪክን ያፅፉ እንጂ በኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ውስጥም ዛሬ ላይ ሊደገም ያልቻለ ውጤትን አስመዝግበዋል። 1996 ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ለሴቶች ብሔራዊ ቡድን የአሰልጣኝነት ቅጥር ማስታወቂያ ሲያወጣ አሰልጣኙ ተወዳድረው በዋና አሰልጣኝነት ሲሾሙ የአሁኑ የአዳማ ከተማ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ደግሞ ረዳት በመሆን ቡድኑ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያውን እንዲያልፍ አድርገዋል፡፡ በወቅቱም ጠንካራ ሴት ተጫዋቾችን ያቀፈው ቡድኑ ወደ ደቡብ አፍሪካ ማምራት ችሏል።

“ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ አልፎ ወደ ደቡብ አፍሪካ አመራን። በቡድኑ ውስጥ ልጆቹ የምነግራቸውን መረዳታቸው ነው የጠቀመኝ። ሜዳ ላይ ሲገቡ ያልኳቸውን ተግባራዊ አድርገውልኛል። እኔ በተፈጥሮዬ ፈሪ ተጫዋች አላስተናግድም። ሴትም ሆነ ወንድ ተጫውተው ማሳየት እንዳለባቸው አምናለሁ። በዚህ ስሜት ሴቶቹን አበረታታሁ። እነሱም በጣም ነው የሚሰሙኝ ፤ እኔም ትኩረት ሰጥቻቸዋለሁ። እኔ ሁሌም ‘በዓለም ላይ መታወቅ አለባችሁ’ ብዬ እመክራቸው ነበር። ወደ ውድድሩ ሲገቡ ደግሞ ውድድሩን ለመዱት። የመጀመሪያው ቀን ላይ ማሸነፍ ጀመርን ደቡብ አፍሪካን በሜዳዋ አሸነፍን። ከጋና ጋር ደግሞ አቻ ተለያየን። ለዋንጫ ለማለፍ ከናይጄሪያ ነበር የገጠምነው። ሴቶቹን ማድነቅም አለብን አልቻልናቸውም ከዋንጫ ሽሚያ ወጣን እና ድጋሚ ለደረጃ ከጋና ጋር ተገናኘን በመለያ ምት ጋናዎች ሦስተኛ ሆኑ እኛ አራተኛ ሆንን። እስከ አሁንም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ በሴቶች ትልቁ ውጤትን ያመጣሁት እኔ ነኝ። አሁን ላይ ስማቸውን ረሳሁ እንጂ እንደ ብርቱካን ገብረክርስቶስ እና አዲስ ዘለቀን የመሳሰሉ ጠንካራ ልጆች ነበሩበት። ሁሉም ጥሩ ነበሩ። አዲስ ዘለቀም ጠንካራ እና ጥሩ ልጅ ነበረች ፤ የምታገኛቸውን ኳሶች ወደ ግብ የምትቀይር ነበረች። በዚህ ቡድን የነበረኝ ጊዜ ለኔ ትልቅ ነበር።” ሲሉ ያንን ጊዜ ያስታውሳሉ። ከሴቶች ብሔራዊ ቡድን የደቡብ አፍሪካ ጉዞ በኋላ አሰልጣኙ ወደ ሀገር ቤት ሲመለሱ የገነቡት የአርባምንጭ ጨርቃጨርቅ ቡድን ፈርሶ ነበር። ቢሆንም ወደ ሐረር ቢራ ቀጥሎም ወደ አየር ኃይል በማቅናት እያንዳዳቸውን ለሦስት ዓመታት ያህል አሰልጥነዋል።

አሰልጣኝ መለሰ የኢትዮጵያ ሚሊኒየም ሲገባ የሴካፋ ዋንጫ ላይ ከአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም እና ከማል አህመድ ጋር በመሆን የወንዶች ብሔራዊ ቡድኑንን ማሰልጠን ችለዋል። አሰልጣኙ ከብሔራዊ ቡድን ሲመለሱ ኒያላን ተረክበው እያሰለጠኑ ቆይተው ቡድኑን ወደ ፕሪምየር ሊግ ባሳደጉበት ቀን የመውደቅ አደጋ ደርሶባቸው በገጠማቸው የነርቭ ህመም ከእግር ኳስ አሰልጣኝነት ሊርቁ ችለዋል፡፡ ለእግር ኳሱ ጥልቅ የሆነ ፍቅር ያላቸው የሸመና ልጅ በቀኝ እግራቸው እና እጃቸው ላይ የነርቭ ህመም ቢኖርባቸውም አርባምንጭ ከተማን ከፕሪምየር ሊጉ እስከሚወርድበት ወቅት በአማካሪነት እና አሰልጣኝ ዓለማየሁ አባይነህ ሲሰናበት በጊዜያዊ አሰልጣኝነትም ጭምር አገልግለዋል። “ህመሙ አብዛኛውን እግሬ ላይ ነው ፤ ጭንቅላቴ ደህና ነው። መስራት የሚያቅተኝ ነገር የለም። ሰውነቴም አሁን ደህና ነው ተመልሷል ብዬ እገምታለሁ ፤ መስራት እችላለሁ። እኔ የማማክረው ስለስፖርት ነው። ግን ብዙ የተበላሹ ነገሮች ነበሩ። ከስፖርት ውጪ ያለውን እና የተበላሸውን ደግሞ እኔ አልችለውም። አርባምንጭ እዚህ ችግር ውስጥ የገባሁ ባለመግባባት ነው። በዚህ ምክንያት ነው ቡድኑ እንዲህ የተረበሸው። እኔም ለቅቄ ልወጣ ችያለሁ።”

የእግር ኳሳችን መሠረት ላይ ባለመሰራቱ የተነሳ ቁጭት ዛሬም ድረስ ያለባቸው አሰልጣኝ መለሰ አሁንም ከእግር ኳሱ አልተያዩም። ጋሞ ጨንቻ የተባለን ቡድን እያማከሩ ከብሔራዊ ሊግ ወደ ከፍተኛ ሊግ እንዲያድግ አበርክቶ ያደረጉ ሲሆን ”እያመመኝም ቢሆን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ይሄን ክለብ እናስገባዋለን” ሲሉ ዛሬም ያልተበገሩት የሸመና ልጅ በተስፋ ይናገራሉ፡፡

ሠላሳ ዓመታትን በእግር ኳሱ ያሳለፈው የመለሰ ሸመና ታናሽ ወንድም ገረሱ ሸመና ሌላው ስኬታማው የቤተሰቡ አባል ነው፡፡ ከጨንቻ በተነሳው የእግር ኳስ ህይወቱ በአርባምንጭ እርሻ ልማት ፣ ሀዋሳ ከተማ ፣ ትራንስ ኢትዮጵያ ፣ ደቡብ ፖሊስ እና ስልጤ ወራቤ አሳልፎ ከሁለት ዓመታት በፊት እግር ኳስን በይፋ አቁሟል፡፡ በሀዋሳ ከተማ እና ትራንስ ኢትዮጵያ ቆይታው በተለየ መልኩ ዛሬም ድረስ የሚነሳው ገረሱ በተከላካይ ቦታ ላይ ብልጠቱ እና የአየር ላይ ኳሶች በመግጨት ችሎታው በብዙዎች ዘንድ በተደጋጋሚ ይነሳል። ታላቁ መለሰ ሸመና ኳስን እንዲጫወት አብዝቶ ከመፈለጉ የተነሳ ለዛሬ ማንነቱ የወንድሙ እገዛ የጎላ እንደነበረ ወደ ኋላ ተመልሶ ያወሳል፡፡

” በትምህርቴ ጠንካራ እንድሆን ኳሱንም እንድገፋበት ያደርገኝ እሱ ነው። የሱን ፈለግ ተከትዬም ነው ወደ ኳሱ የገባሁት። አስተማሪ ሆኖ እያለ ነው ለኔም መንገድ የከፈተልኝ፡፡ ቤተሰቦቻችን በኢኮኖሚ ዝቅተኛ ስለነበሩ በእግር ኳሱ ትልቅ ቦታ እንድደርስ ይመክረኝ ነበር። ከዛም ተጫዋች እንድሆን አደረገኝ። አርባምንጭ እርሻ ልማት ገብቼ እንድጫወት አደረገኝ። እሱም እያስተማረ በቡድኑ ውስጥ አብሮኝ ይጫወታል። እኔ ግን በኳሱ ከፍ እያልኩ ስመጣ በቀጥታ ወደ ሀዋሳ ከተማ መጣሁ። ዛሬ እዚህ ለመድረሴ እሱ ያደረገልኝን አልረሳም በጣም አመሰግነዋለሁ።”

ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በተለያዩ ጊዜያት ተጠርቶ ሲጫወት የነበረው ገረሱ በትራንስ ኢትዮጵያ 1995 ላይ ሲጫወት በነበረበት ወቅት ወንድሙ መለሰ የአርባምንጭ ጨርቃጨርቅ አሰልጣኝ ሆነው ሳለ ስለሰሩት ቡድን ይናገራል፡፡

“ጥሩ ቡድን ነበር የገነባው። ቡድን ለመገንባት አልተቸገረም። 1994 ላይ የሱን ፕሮጀክት ነው ወደ ክለቡ ይዞ ያስገባው ጎን ለጎንም ፕሮጀክት ያሰራ ስለነበር አልከበደውም። በአጋጣሚ እኔ ትራንስ ነበርኩ። ለዋንጫ የሚጫወት ቡድን ሰርቶ ነበር ፤ ለዋንጫም ደርሶ ነው ለጥቂት ያጣው። እነሱ በላን ብለው ሲያስቡ ጊዮርጊስ አዲስ አበባ ላይ አንስቶ ለጥቂት ነው ያመለጣቸው እና በጣም ነበር ያሳዘነኝ ልፋቱ። አሁንም የጋሞ ጨንቻ ክለብን ከህመሙ ጋር እየታገለ እየሰራ የሚገኘው መለሰ ለእግር ኳሱ ካበረከተው አስተዋጽኦ አንፃር እግር ኳስ አልከፈለችውም።” ይላል የሱን ፈለግ ተከትሎ በእግር ኳሱ ለስኬት የበቃው ገረሱ ሸመና፡፡

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ