“ብቸኛዋ አፍሪካዊት እንስት…” ትውስታ በመሠረት ማኒ አንደበት

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቡድንን በመምራት የመጀመሪያዋ ሴት አሰልጣኝ በመሆን ታሪክ የሰራችው፣ በሴቶች እግርኳስ ከክለብ እስከ ብሔራዊ ቡድን ድረስ በመስራት ከፍተኛ ዝና እና ስም ያተረፈችው አሰልጣኝ መሠረት ማኒ በ2007 ክረምት ያሳካችው አይረሴ ታሪክን በትውስታ አምዳችን እንዲህ አጋርታናለች።

ሴት በእግርኳሱ እንድትጫወት በማይፈለግበት ዘመን ሰብራ በመውጣት ለብዙዎች ሴት ስፖርተኞች ምሳሌ መሆኗ የሚነገርላት መሠረት ማኒ ትውልዷ ድሬዳዋ ነው። የተለያዩ የስፖርት ዓይነቶችን ትሰራ የነበረችው መሠረት እግርኳስ ተጫዋች መሆን ጀምራ በኋላም በትምህርት ያልታገዘ ቢሆንም ከልምዷ በመነሳት በከፍተኛ ፍላጎት ድሬደዋ አሽዋ ሜዳ ላይ 1978 ድል በትግል የተሰኘ የወንድ ክለብ ማሰልጠን ጀምራለች።

የሙያ አቅሟን እያሳደገች በ1990 በተጀመረው ሀገር አቀፍ የታዳጊዎች ፕሮጀክት ስልጠና ላይ በኢትዮጵያ የመጀመርያዋ (ብቸኛዋ) ሴት አሰልጣኝ በመሆን የአሰልጣኝነትን ትምህርት ወስዳለች። ከ1991 ጀምሮ በድሬዳዋ ከተማ የወንድ ታዳጊ ቡድኖችን በማሰልጠን በተለያዩ የፕሮጀክት ምዘና ውድድር ላይ የድሬደዋን ምርጥ ቡድን አሰልጣኝ በመሆን ሰርታለች።

በ2003 የሉሲ ማቀጣጠያ ውድድር የሴት ቡድን በመያዝ ድሬዳዋን በመወከል ከተሳተፈች በኃላ 2004 የተቋቋመውን የድሬደዋ ከተማ የሴቶች ቡድን በማሰልጠን የመጀመርያዋ አሰልጣኝ ሆናለች። በአብዛኛው የኢትዮጵያ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በወንዶች እየተመራ ሴቶች በምክትል አሰልጣኝነት ያገለግሉበት የነበረውን ታሪክ ቀይራ በ2002 የመጀመርያዋ ሴት የሉሲዎች ዋና አሰልጣኝ በመሆን ተሹማለች። ከዚህ ባሻገር ሉሲዎቹን በም/አሰልጣኝ በመሆን አገልግላለች።

ድሬዳዋ ከተማ የወንዶቹን ቡድንን በቴክኒክ አማካሪነት እያገለገለች ባለችበት ወቅት በ2007 የዋናው ቡድን አሰልጣኝ በመሆን ቀዳሚዋ የድሬዳዋ ከተማ የወንዶች አሰልጣኝ በመሆን የማጠቃለያ ውድድሩን ሁሉንም ጨዋታዎች በማሸነፍ ድሬዳዋን ዳግመኛ ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲመለስ በማድረግ ስኬታማ ሆናለች። በዚህ ያላበቃው የመሠረት ስኬት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት አሰልጣኝ በመሆን አዲስ ታሪክ ፅፋለች። ይህም ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ የመጀመርያዋ በትልቅ ሊግ ውድድር ወንዶችን ያሰለጠነች ቀዳሚ ሴት አድርጓታል።

በርካታ የህይወት ውጣ ውረድ አልፋ በጥንካሬ የስኬት ጫፍ የደረሰችው መሠረት የካፍ ኢንስትራክተር በመሆን ሀገሯን እያገለገለች ትገኛለች። በክለብ ደረጃ አሁን ያለችበትን ኢትዮ ኤሌክትሪክን ጨምሮ የአዲስ አበበ የሴቶች ቡድንን አሰልጥናለች። ከልጅነት እስከ እውቀት ያሳለፈችውን የህይወት ጉዞ የሚያሳይ “መሠረት ማኒ – የብርታት ተምሳሌት” የተሰኘ መጽሐፍ ለአንባቢያን ማቅረቧ ይታወሳል። በዛሬው የትውስታ አምዳችን በ2007 መጨረሻ ድሬዳዋ ከተማን እያሰለጠነች ወደ ፕሪምየር ሊግ በማሳደግ ያገኘችውን ክብር ወደ ኋላ አስታውሳ ስለተሰማት ስሜት እንዲህ አጫውታናለች።

“አንተም እንደምታቀው በህይወትህ ውስጥ በየትኛውም ሙያ ውስጥ ብትሆንም ልታሳካ የምትፈልገው ህልም ይኖርሀል። ያን ጊዜ የተፈጠረውን ነገር ሳስታውስ እኔ ህልሜን አሳክቻለው ብዬ ነው የማስበው። የአፍሪካ ብቸኛ መሆኔን ደግሞ ሳስበው የተለየ ስሜት ይፈጥርብኛል። መጀመርያ ይህንን አስቤ አልነበረም የሰራሁት ግን ከሥራ በኋላ የመጣ ነገር ነው። ይህን ስታስበው ደግሞ የበለጠ እንድትሰራ የሚያነሳሳህ፣ የሚያበረታታህ ከእዚህ የተሻለ ብትሰራ ደግሞ የተሻለ እውቅና፣ ክብር ልታገኝ እንደምትችል እና በሰራኸው ሥራ ልትደሰት እንደምትችልየሚያሳይ ነው።

” 2007 የነበረው ነገር በእውነት በህይወቴ ትልቅ ቦታ የምሰጠው ነው። በእግርኳስ ውስጥ ረዥም ጊዜ አሳልያለው። በዚህ ያሳለፍኩት ህይወት ውስጥ የልፋቴን፣ የድካሜ ውጤት ያገኘሁበት ነው። በወቅቱ ብሔራዊ ሊግ ይባል ነበር ውድድሩ፣ ክለቡን ለማሰልጠን ተረክቤ ስራ ስጀምር መጀመርያ አካባቢ ውጤታችን ጥሩ አልነበረም። ሁለተኛው ዙር ግን መስራት የሚጠበቅብንን ነገሮች አስተካክለን አንደኛ ሆነን በመጨረስ ድሬደዋ ላይ ለተካሄደው የማጠቃለያ ውድድር በቅተናል። በውድድሩም ከምድብ ጨዋታ እስከ ፍፃሜ ድረስ ሁሉንም ጨዋታዎች በማሸነፍ ወደ ፕሪምየር ሊግ ልንገባ ችለናል። በወቅቱ የነበረው ድባብ፣ የክለቡ አመራሮች የነበረው ትጋት እና የተጫዋቾቼ የሚነገራቸውን የመቀበልና የመጫወት ፍላጎት ጨምሮ ስኬታማ አድርጎናል። በተለይ በተለያዩ ሁኔታዎች ከሜዳ ርቆ የነበረው የድሬዳዋ ስፖርት አፍቃሪ ዳግመኛ ወደ ሜዳ የተመለሰበት፣ ተዳክሞ የነበረው የድሬዳዋ እግርኳስ ዳግም የተነቃቃበት እጅግ የማይረሳ አስደሳች ጊዜ ነበር።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ