“ልጁን ስሞ ወጥቶ ሲቀር ይከብዳል” የአሰግድ ተስፋዬ ባለቤት ወ/ሮ ገነት

ታላቁ እግርኳሰኛ አሰግድ ተስፋዬን በሞት ካጣነው ነገ ግንቦት 26 ሦስተኛ ዓመቱን የሚደፍን መሆኑን ተከትሎ ለተከታታይ ሦስት ቀናት እዘክረዋለን ባለነው መሠረት በቀዳሚነት የአሰግድ ተስፋዬ ባለቤት ወ/ሮ ገነት የደረሰባትን ሀዘን እና አሁን ከአብራካቸው ክፍይ አንድ ልጇ ጋር እያሳለፈች ስለምትገኘው ህይወቷ እንዲሁም ሌሎች ከአሰግድ ተስፋዬ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ዙርያ ለሶከር ኢትዮጵያ እንዲህ ነግራናለች።

በነገራችን ላይ የቀለም ሥሟ ፀሐይ ወርቅነህ ቢሆንም አሰግድ ባወጣልኝ “ገነት” ብላችሁ ጥሩኝ ባለችው መሠረት ገነት የሚለው መጠርያዋን ለመጠቀም ወደናል።

አሰግድ ለቤተሰቡ፣ ለአንቺ.. ምን ዓይነት ሰው ነበር ?

በመጀመርያ አስታውሳችሁ ስለደወላቹ አማሰግናለሁ። የእርሱንም ነፍስ ይማረው። አሰግድ እኔ ከምናገረው በላይ የኢትዮጵያ እግርኳስ ቤተሰብ ሰለ እርሱ የሚመሰክሩት ይሻላል። እጅግ መልካም፣ ለቤተሰቡ አሳቢ ትሁት ወንድሜ፣ ባለቤቴ እና አባቴ ነው ማለት እችላለው። እርሱ ለእኔ እና ለልጄ በጣም የሚያስፈልግ ሰው ነበር። ያው ሳናስበው አመለጠን እንጂ።

አሰግድ ሲጫወት ተመልክተሽዋል ?

ይገርምሀል አሰግድን ሲጫወት አንድም ቀን ተመልክቼው አላውቅም። ከተዋወቅን ከረጅም ዓመት በኃላ ነው እንደሚጫወት ያወኩት። ሆኖም ስለ እርሱ ችሎታ እና አቅም ጓደኞቹ እርሱም በህይወት እያለ ሲያወራኝ እና ሲነግሩኝ በጣም ደስ ይለኝ ነበር። ሲጫወት አልመልከተው እንጂ አሰግድ እጅግ ታላቅ ተጫዋችም እንደነበረ አውቃለው።

በድንገት ነው ሳናስበው ያጣነው፤ የመሞቱን ዜና ስትሰሚ ምን ተሰማሽ ጊዜውን አስታውሺኝ ?

(እያለቀሰች) በጣም ከባድ ነበር። እኔም ያላሰብኩት ነገር ነው። እርሱም ያላሰበው ነገር ነው። ልጁን ስሞ መወጥቶ ሲቀር ይከብዳል። በጣም መሪር ሐዘን ነው። እንዲህ ብለህ የምትገልፀው አይደለም።

ከአሰግድ ህልፈት በኃላ የኑሮ ሁኔታሸ እንዴት ነው?

እኔ እርሱን ካጣው ጊዜ ጀምሮ ውስጤን ሀዘን ጎድቶኛል እንጂ ከዛ ውጭ በሌላ ህይወቴ የጎደለብኝ ነገር የለም። አሰግድ እጅግ መልካም ሰዎች ጥሎልኝ ስላለፈ ጥሩ ሁኔታ ላይ ነው የምገኘው። አሰግድ የነበረው መልካም ባህሪ ለእኔ በጣም ጠቅሞኛል። የእሱን ጥሩነት እና ቀናነት ውጤት እኔ አግኝቸዋለው።

የሴት ልጃችሁ (ልያት አሰግድ) ሁኔታ እንዴት ነው ?

አዎ ደህና ናት። ያው እርሱ ሲሞት የአንድ ዓመት ከሰባት ወር ነበረች። አሁን አራት ዓመት ሞልቷታል፤ አድጋለች። ወደፊት የአባቷን ስም የበለጠ ታስጠራለች ብዬ ተስፋ አደርጋለው።

አሰግድ በኢትዮጵያ እግርኳስ ጥሎት እንዳለፈው አሻራ ህይወቱ ካለፈ በኃላ የሚገባውን ክብር አግኝቷል ትያለሽ ?

እውነቱን ለመናገር አዎ፤ በተለይ ከሞተ በኃላ እንደነገርኩህ ህዝቡ፣ ጓደኞቹ የሚሰጡት ክብር ትልቅ ነው። እኔ እራሴ አሁን ባለሁበት ሁኔታ፣ የሄድኩበት ቦታ ሁሉ የእርሱ ባለቤት መሆኔን አውቀው፣ ጉዳይ ለማስፈፀም የተለያዩ ቦታዎች ስሄድ የእርሱ ባለቤት ነኝ ካልኩኝ የሚሰጡኝ አክብሮት ከምነግርህ በላይ ነው። በትልቅ ክብር ነው የሚሸኙኝ። የአሰግድን ክብሩን አግኝቼዋለው።

የአሴጋ ፕሮጀክት አሁን በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል ?

አካዳሚው እርሱ በህይወት ካለፈ እስካሁን ድረስ አለ። እንደነገርኩሁ የእኔም የእርሱም ጓደኞች ከጎኔ ስለሆኑ አካዳሚው በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው ያለው። አሁን በተፈጠረው ወረርሽኝ ምክንያት ከቆመ ሦስት ወር ሆነው እንጂ ጥሩ እየሄደ ነው። ሻላ የሚባል የጤና ቡድን ማኀበር ከጎኔ ናቸው። እነርሱ የሚሰሩበት ሜዳ ፍቃድ እንዲሰጠኝ በማድረግ፣ የስፖርት ቁሳቁስ በማሟላት እያገዙኝ ነው። ተጠቃሚው ራሴ ነኝ፤ ግን በጣም ነው የሚያግዙኝ እና ፕሮጀክቱ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ይገኛል።

በመጨረሻ መልዕክ ካለሽ ?

ያው እንግዲህ አሰግድ ትልቅ ተጫዋች ነበር። እኔም ነገ እንደከዚህ በፊቱ ከጓደኞቹ ጋር ሰብሰብ ብለን ስናስበው ብንውል ደስ ይለኝ ነበር። ካለው የወቅቱ በሽታ አንፃር ለነዳያን በመስጠት እርሱን ለመዘከር አስቤያለው። እናተንም በዚህ አጋጣሚ በጣም ነው የማመሰግነው።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ